ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ሦስቱ ዕጩዎች እነማን ናቸው?

አቶ ቶኪቻ አለማየሁ፣ ኢሳያስ ጂራ፣ መላኩ ፈንታ

የፎቶው ባለመብት, YouTube/BBC/Bereket

የምስሉ መግለጫ, አቶ ቶኪቻ አለማየሁ፣ ኢሳያስ ጂራ፣ መላኩ ፈንታ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ እና ነገ ጠቅላላ ጉባዔውን በማካሄድ የሚመራውን ፕሬዝዳንት ምርጫ እንደሚያካሄድ የወጣው መረጃ ያሳያል።

ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በዕጩነት ሦስት ሰዎች ቀርበዋል።

እነዚህም በአሁን ወቅት በፕሬዝዳንትነት ፌዴሬሽኑን እያገለገሉ ያሉት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ አቶ ቶኪቻ አለማየሁ እንዲሁም አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው።

ከፕሬዝዳንት ምርጫ ውጪ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን 32 ዕጩዎች ቀርበዋል።

እነዚህ ዕጩዎች በምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ መታየታቸው ተግልጿል።

የሚመረጠው ፕሬዝዳንት ስፖርቱን ማሳደግ፣ ማዘመን እንዲሁም ብሔራዊ ቡድኑ ደረጃውን የጠበቀ መጫወቻ ሜዳ እንዲኖረው ማድረግ ከሚጠበቁበት ዐበይት ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ይህ ጠቅላላ ጉባኤ መጀመሪያ ጎንደር ከተማ እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጓል።

ሦስቱ ለፕሬዳንትነት የቀረቡ ዕጩዎች ሁለት ክልልን እና አንድ የከተማ አስተደደርን ወክለው ይወዳደራሉ። ስለዕጩዎቹ ከምናውቀው በጥቂቱ . . .

አቶ ኢሳያስ ጂራ

አቶ ኢሳያስ ጂራ

አቶ ኢሳያስ ጅራ ላለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንት የመሩ ሲሆን፣ ለቀጣይ አራት ዓመታት በአመራርነት ለመቀጠል እየተወዳደሩ ይገኛሉ።

ከፌደሬሽኑ ውጪ የሴካፋ፣ የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ውድድር ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

አቶ ኢሳያስ የኦሮሚያ ክልልን ወክለው ነው የሚወዳደሩት።

ከአራት ዓመት በፊት በ2010 ዓ.ም፣ የጂማ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ሥራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ ባለበት ወቅት ነው ተወዳድረው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት የሆኑት።

ከ20 ዓመታት በላይ በስፖርት አመራርነት የቆዩት አቶ ኢሳያስ፣ በጂማ እና በሰበታ እግር ኳስ ቡድኖች በአመራርነት ሠርተዋል።

ባለፉት ዓመታት “ደረት የሚያስነፋም ባይሆን አንገት የማያስደፋ ሥራ” መስራታቸውን ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት ተናግረው ነበር።

“ተጨባጭና በአይን የሚታይ ሥራ ሰርተናል” የሚሉት አቶ ኢሳያስ ዳግም ቢመረጡ የጀመሯቸውን መልካም ነገሮች ማስቀጠል፣ ሊሰሯቸው አቅደው በተለያየ ምክንያት ያልተሳኩትን ደግሞ ማከናወን እቅዳቸው ነው።

ከእቅዳቸው መካከል ዐቢይ የሆነው “የክለቦች አደረጃጀት ላይ መሥራት” መሆኑን ይናገራሉ።

አቶ ቶኪቻ አለማየሁ

የፎቶው ባለመብት, YouTube

አቶ ቶኪቻ አለማየሁ

ከሦስቱ ዕጩዎች መካከል በዕድሜ ትንሹ አቶ ቶኪቻ፣ 39 ዓመታቸው ነው።

በ1975 ዓ.ም በኢሉ አባ ቦራ በጎሬ ከተማ የተወለዱት ቶኪቻ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን በመወከል ነው የቀረቡት።

በእንግሊዝ አገር፣ ሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ በሲቪል ምህንድስና የተመረቁት አቶ ቶኪቻ፣ በሥራ ፈጠራ ስማቸውን የተከሉ ናቸው።

በግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሠሩ ሲሆን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

የድሬ ዳዋ ከነማ እግር ኳስ ቡድንን በገንዘብ የሚደግፉት አቶ ቶኪቻ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ያምናሉ ።

የስፖርት ተቋማት ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ቡድኖች (ክለቦች) ድረስ በጥምረት መስራት አለባቸው ይላሉ።

ቀጣይ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ፌዴሬሽኑን በፋይናንስ ማጠንከር፣ እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሚሰማሩ ገልፀዋል።

በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል ውስጥ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በአመራርነት እንዲሳተፉ ማድረግ ከእቅዶቻቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።

አቶ መላኩ ፈንታ

የፎቶው ባለመብት, AMC

የምስሉ መግለጫ, አቶ መላኩ ፈንታ

አቶ መላኩ ፈንታ

አቶ መላኩ ፈንታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚወዳደሩት የአማራ ክልልን ወክለው ነው።

አቶ መላኩ ኢኮኖሚክስ እና ቢዝነስ አስተዳደር ያጠኑ ሲሆን በገቢ እና ጉምሩክ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። በሠራተኛ እና ማኅበራዊ ሚኒስቴር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሠርተዋል።

አቶ መላኩ የቀድሞ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስትር ሆነው ለበርካታ ዓመታት አገለግለዋል።

አቶ መላኩ ፈንታ ፖለቲካዊ ነው በሚሉት በከፍተኛ ሙስና ክስ ከሥልጣናቸው ተነስተው ለአምስት ዓመታት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ነው የተፈቱት።

ባለፉት አራት ዓመታት በአማራ ልማት ማኅበር ከዚያም በቅርቡ ተመስርቶ ሥራ በጀመረው የአማራ ባንክ ውስጥ በግንባር ቀደምትሲሰሩ ቆእተዋል።

በእግር ኳስ ዘርፍም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ካሉ ጠንካራ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብን በቦርድ አባልነት ያገለግላሉ።

ከተመረጡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ውስጥ ያላትን ተሰሚነት ለመጨመር እንደሚሰሩ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

በተጨማሪም የተመረጡ ስታዲየሞች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው “ስደተኛው የእግር ኳስ ቡድናችን በሜዳው እንዲጫወት እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

“እግር ኳሳችን ትንሳዔ ያስፈልገዋል” ያሉት አቶ መላኩ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።