ሰመራ ዩኒቨርስቲ የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍሉን በታዋቂው ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ስም ሰየመ

ሰመራ ዩኒቨርስቲ የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Samara University

የምስሉ መግለጫ, ሰመራ ዩኒቨርስቲ ከዚህ ቀደም የሉሲን ቅሪተ አካል ባገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰን ስም የትምህርት ክፍል ሰይሟል

በአፋር ክልል የሚገኘው ሰመራ ዩኒቨርስቲ የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍሉን በቅርቡ ሕይወታቸው ባለፉት አሜሪካዊ ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ስም ሰይሟል።

ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን ያተረፉ እና በችሎታቸው ውስጥ በሚያሳዩት ርኅራሄ "መልካሙ ዳኛ" የሚል ስም የተሰጣቸው ነበሩ።

ከሁለት ሳምንታት በፊት በ88 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው ዳኛው የሰመራ ዩኒቨርስቲ ሴኔት ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም. በስማቸው ትምሕርት ክፍል ሰይሞላቸዋል።

ዩኒቨርስቲው በማኅበራዊ የትስስር ገፁ 'ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ የሕግ እና አስተዳደር ትምህርት ቤት' ሲል ለዳኛው መታሰቢያ እንዲሆን ትልቅ ውሳኔ መወሰኑን አስታውቋል።

የዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሐመድ አሕመድ ምክንያቱን ሲናገሩ "ዩኒቨርስቲ እና ፍትኅ ዓለም አቀፍ በመሆናቸው ነው" ብለዋል።

"ምንም እንኳ እሳቸው አሜሪካ እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ብንሆንም በተለይ የእርሳቸው ህያው ሥራ፤ የእሳቸው ርኅራሄያዊ ፍትኅ ለዩኒቨርስቲያችን፤ ለተማሪዎቻችን፤ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለን ነው" ሲሉ ለስያሜው ምክንያት አቅርበዋል።

ከዚህ ባሻገርም ዩኒቨርስቲው በታዋቂው ዳኛ የትምህርት ክፍል መሰየሙ ለዝናው እንዲሁም ለቀጣይ ትብብሮች በር ይከፍታል የሚል እምነትንም ሰንቋል።

የሰመራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መሐመድ ኡስማን "የዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ የሕይወት ዘመን ሥራ በተማሪዎቻችን ለመቅረፅ የምንጥረው የፍትኅ፣ ክብር እና አገልግሎት እሴት ተምሳሌት ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰመራ ዩኒቨርስቲ ከዚህ ቀደም የሉሲን ቅሪተ አካል ባገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰን ስም የማኅበረሰባዊ እና ሰብዓዊነት ትምሕርት ክፍልን መሰየሙን ገልጿል።

የሰሞነኛ የሴኔቱ ውሳኔ ዩኒቨርስቲው በታዋቂ ሰዎች ወይም ተመራማሪዎች የትምህርት ክፍል ሲሰይም ለሁለተኛ ጊዜው ያደርገዋል።

እንዲያም ሆኖ ሁለተኛው ትውልድ የሆነው ሰመራ ዩኒቨርስቲ ከታዋቂው ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ጋር ምን አገናኛቸው? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው።

የትምህርት ክፍል ስያሜውን መበሰርን በሚመለከት "'በአቅማችሁ ልክ ቢሆን ጥሩ ነው፤ ያለአቅማችሁ ነው"' የሚሉ አስተያየት እንደደረሷቸው ያልደበቁት አቶ መሐመድ፤ የአፋር ማኅበረሰብ ባህላዊ የፍትኅ እና ዳኝነት ሥርዓት ከዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ የርኅራሄ ፍትኅ ጋር ተቀራራቢ እሳቤ መሆኑ ለእርምጃው አስተሳሳሪ ገመድ አድርገው አንስተዋል።

'መድኣ' የተባለው የአፋር ማኅበረሰብ የፍትኅ እና ዳኝነት ሥርዓት ትዕግሥትን እና ሁለተኛ እድልን የሚሰጥ እንዲሁም ሁሉን ገዢ ሥርዓት መሆኑን በመግለፅ፤ ይህ ሥርዓት ሕይወታቸው ካለፉት ዳኛ እሳቤ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ለሰመራ ዩኒቨርስቲ ውሳኔ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

"የአፋር የዳኝነት ሥርዓት በጣም ርኅራሄ ያለው፤ ሌሎች ችግሮች እንዳይስፋፉ በተለይ ወደ ከፋ ችግር እንዳይሄድ፤ ወደ በቀል እንዳይሄድ፤ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሮችን የሚፈታ፤ በተለይ በእዝነት ላይ፤ በርኅራሄ ላይ፤ ሁለቱንም ወገኖች በሚያስማማ ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ የሚጠቀሙበት አይነት ሥርዓት [የአፋር ማኅበረሰብ] በባህላዊ መንገድ ይጠቀማሉ" በማለት አብራርተዋል።

ሰመራ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛው ትውልድ ከሚባሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን በ1999 ዓ.ም. የተቋቋመ ዩኒቨርስቲ ነው።

ዩኒቨርስቲው በቅርቡ በተደረገው የትምህርት መስክ የትኩረት ልየታ መሰረት ወደ 'አፕላይድ ዩኒቨርስቲ' እየተሻገገረ ያለ ሲሆን፤ ትኩረቱም ቱሪዝም፣ ሥነ-ምድር ጥናት እንዲሁም ቆላማ ግብርና ትምህርቶች ናቸው።