ከናዚ ጭፍጨፋ የተረፉ የኦሽዊትዝን 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ለማክበር በማጎሪያ ካምፑ ተገኙ

ከናዚው የሞት ጣብያ ኦሽዊትዝ-ቤርከናው በሕይወት የተረፉ 50 ያህል ሰዎች ከማጎሪያ ካምፑ ነጻ የወጡበትን ዕለት ለማሰብ ሰኞ፣ ጥር 19/ 1937 ወደ ስፍራው ተመልሰዋል።
ንጉስ ቻርለስን እና ሌሎች የአውሮፓ ንጉሳውያን ቤተሰቦችን ጨምሮ የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየር ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
ንጉስ ቻርለስን እና ሌሎች የአውሮፓ ንጉሳውያን ቤተሰቦችን ጨምሮ የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየር ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
አብዛኛዎቹ በ80ዎቹ እና 90ዎቹ ዕድሜያቸው መጨረሻ ላይ የሚገኙት እና 1.1 ሚሊዮን ሰዎች ከተገደሉበት ካምፕ በሕይወት የተረፉት መልዕክት አስተላልፈዋል።
መልዕክታቸውም በካምፑ የሆነውን ነገር ለዓለም ለመንገር እና ዳግም እንዳይከሰት ለማሳሰብ ነው።
የ94 ዓመቷ እና ከመንታ እህቶቿ ጋር በአውሮፓውያኑ 1944 በአይሁዳውያን ማጎሪያ ስፍራው የደረሱት ጆና ላክስ "በዚህች ምድር ላይ ያለች ነፍስ ሁሉ የመኖር መብት አላት" ብለዋል።
"ኦሽዊትዝ ሰዎችን ለመግደል ቤተ ሙከራ ነበር ይህንንም አረጋግጧል። ከኦሽዊትዝ የተረፉት ጥቂቶች ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Claims Conference
ምንም እንኳን ባለፉት ጥቂት ቀናት የቀኑ ቅዝቃዜ እየቀነሰ እና አብዛኛው በረዶ እየቀለጠ ቢሆንም፣ በመታሰቢያ ዝግጅት ላይ ለመታደም ከተገኙ 50 ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በዕድሜ ምክንያት ለረዥም ሰዓት በዝግጅቱ ስፍራ ለመቀመጥ አይችሉም።
ይልቁንም የበርከናው መግቢያ በሚታወቅበት "በሞት በር" ላይ ትልቅና የሚሞቅ ድንኳን ተተክሏል።
በህይወት የተረፉት ሰዎች እና የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድሬዝ ዱዳ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖላንድ እስረኞች ፣ አይሁዶች እና የሶቪየት ጦር እስረኞች በተገደሉበት በመጀመሪያው የኦሽዊትዝ ካምፕ "የሞት ግድግዳ" ላይ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ቀኑ ይጀምራል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር በቅርቡ የአበባ ጉንጉን በቦታው ያስቀመጡ ሲሆን አበባው አሁንም በቦታው አለ።
ዝግጅቱ በኋላ ላይ ኦሽዊትዝ II ወደ በሚባለው በበርከናው የሞት ካምፕ ይከናወናል።
ካምፑ በሶቪየት ወታደሮች ነጻ የወጣበትን እያንዳንዱ ዓመታዊ በዓል የተለያየ ነው።
ከሠላሳ ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው ትኩረት በጣም አናሳ ነበር። በወቅቱ ታዋቂው ጸሐፊ ኤሊ ዊሰል በርካታ በህይወት የተረፉት ሰዎችን እና ዘመዶቻቸውን ናዚዎች ከመሸሻቸው በፊት ባፈነዱት አንደኛው የአስከሬን ማቃጠያ የማስታወሻ ዝግጅት ነበራቸው።

የፎቶው ባለመብት, US States Holocaust Memorial Museum
ጀርመናዊቷ የታሪክ ምሁር ሱዛን ዊለምስ ለበርካታ አስርት ዓመታት ስላገኟቸው በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ጉዳይ በፍቅር ይናገራሉ። "ብዙዎቹ እንደምወዳቸው አያቶቼ ነበሩ። በእርግጥ ብዙዎቹን ብናጣም የእነሱን ምስክር መሆን የእኔ ግዴታ ነው" ብለዋል።
ምንም እንኳን ካምፑ ነጻ የወጣው በሩሲያ 60ኛው የዩክሬን ጦር ሰራዊት ቢሆንም ከሦስት ዓመታት በፊት በዩክሬን ላይ በተከፈተው መጠነ ሰፊ ጦርነት ምክንያት የሩስያ ተወካዮች አይገኙም።
ቭላድሚር ፑቲን በ 60ኛው ክብረ በዓል ላይ ቢገኙም ዘንድሮ ግን እንዲሳተፉ አይደረግም።
ናዚዎች የአውሮፓን አይሁዶች ለማጥፋት የወሰዱት ውሳኔ በ1942 መተግበር ጀመረ። ስድስቱ የአይሁዳውያን ማጎሪያ ካምፖች በፖላንድ በቼልምኖ፣ ቤልዜክ፣ ሶቢቦር፣ ትሬብሊንካ፣ ማጅዳኔክ እና ኦሽዊትዝ-በርከናው ተገንብተዋል።
ትሬብሊንካ ከኦሽዊትዝ በጣም ያነሰ ቢሆንም ግን 800 ሺህ እስከ 850 ሺህ አይሁዶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገድለውበታል።
የአስፈሪው ኤስኤስ ዋና አዛዥ ሃይንሪች ሂምለር እና የካምፑ አዛዥ ሩዶልፍ ሆስ የኦሽዊትዝ ማስፋፊያን እየተቆጣጠሩ በበርከናዉ ሁለተኛ የግድያ ካምፕ ለመገንባት ችለዋል።
እአአ በ1942 መገባደጃ ላይ አራት የተለያዩ በጋዝ የመግደያ ክፍሎች እና የአስከሬን ማቃጠያዎች ነበሩ።

አይሁዶች ለመጀመሪያ ጊዜ በጅምላ ወደ በርከናዉ የተወሰዱት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 1942 ሲሆን ከስሎቫኪያ እና ከፈረንሳይ ነበር። በሐምሌ ደግሞ ከኔዘርላንድስ እና ቤልጂየም ተወስደው በአሽዊትዝ ሥራችሁ ነጻ ያወጣችኋል በሚለው በታዋቂው ምልክት በኩል አልፈው ወደ አዲሱ የመገደያ ካምፕ አቅንተዋል።
ብዙም ሳይቆይ ባቡሮች በልዩ ሁኔታ በተሠራው መስመር በርከናዉ መድረስ ጀመሩ። ከሁለት ጋዝ ክፍሎች ትንሽ የሚርቅ ሲሆን በአንድ ወቅት 12 ሺህ አይሁዶች በጋዝ እየተገደሉ አካላቸው በየቀኑ እንዲቃጠል ተደርጓል።
ዮና ላክስ ወላጆቿን በቼልሞ ከማጣቷም በላይ እአአ በ1944 ከመንታ እህቷ ሚርያም እና ታላቅ እህቷ ቻና ጋር በቦታው ደረሱ።
"እኔ ወደ ግራ እንድሄድ ታዝዤ ነበር። ይህም ማለት አስከሬን ማቃጠያ ማለት ነው። መንታ እህቴ ግን ወደ ቀኝ ተላከች። ይህ የሆነው ግን ግለሰቡ በመሳለቸቱ ምክንያት ሰዉን እንኳን ሳይመለከት 'ግራ፣ ቀኝ፣ ግራ፣ ቀኝ' እያለ መደበ። ግራው ሞት ማለት እንደሆነ ባላውቅም ግን ጥሩ እንዳልሆነ አውቄ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Jona Laks
ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ አዲስ መጤዎች እንዲገደሉ የተላኩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ለጉልበት ብዝበዛ የተመረጡ ናቸው።
"ወደ በሩ በጣም ተጠግቼ ነበር። የእሳት ፍንጣሪዎች፣ ከጭስ ማውጫው ውስጥ እሳት ሲወጣ ተመልክቻለሁ። የተቃጠለ የሥጋ ሽታ ይሸተኛል።"
ዮናስ ላክስ የዳነችው ታላቅ እህቷ ከመንታዋ መለየት እንደሌለባት በመናገሯ ብቻ ነበር። መልዕከቷ የናዚው "የሞት መልአክ" ከሚባለው ጆሴፍ መንገሌ ጋር ይደርሳል። ጆሴፍ የበርከናውን የተወሰነ ክፍል መንታ ልጆች በህይወት እያሉ የተለያዩ አሰቃቂ የህክምና ሙከራዎችን ያደርግባቸው ነበር።
ሴቶች እና ህፃናት፤ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች በፍጥነት ወደ ጋዝ መግደያዎቹ ተልከዋል።
የቢቢሲው ዘጋቢ ፖል ኪርቢ አያት ከኔዘርላንድ ወደ ስፈራው ካቀኑት መጀመሪያዎቹ መካከል ሲሆኑ ከአንድ ወር በላይ በባሪያ ጉልበት ሲሠሩ እስከ አውሮፓውያኑ 1942 ድረስ ቆይተዋል።
እህታቸው ጌርትጄ ቫን ሃሰልት፣ የትምህርት ቤቷ ርዕሰ መምህር ባል ሳይመን እና ሁለቱ ሴት ልጆቻቸው የ14 ዓመቷ ሄርሚ እና የዘጠኝ ዓመቷ ሶፊያ በየካቲት 12 ቀን 1943 እንደደረሱ ተገደሉ።

ከ1941 እስከ 1945 ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ አውሮፓውያን አይሁዳውያን ተገድለዋል። ከሟቾቹ መካከል 70 ሺህ የሚያህሉ የፖላንድ እስረኞች፣ 21 ሺህ ሮማዎችና 15 ሺህ የሶቪየት የጦር ምርኮኞች እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ወንዶች ይገኙበታል።
ኦሽዊትዝ ባለፈው ዓመት 1.83 ሚሊዮን ጎብኝዎችን አስተናግዷል። ለመታሰቢያው በዓል የተዘጋ ቢሆንም በሳምንቱ መጨረሻ ብዙ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎች የሙዚየሙን ዙሪያ ተመልክተዋል።
የካምፑ መጠን በጣም አስፈሪ ነው። የብዙዎቹ ቅሪቶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተጠብቀዋል። ናዚዎች ማስረጃውን ለማጥፋት በመፈለጋቸው ያቃጠሏቸው ሁለት የጋዝ መግደያ ክፍሎች እና የአስከሬ ማቀጣያዎች ፍርስራሾች አሁንም አሉ።
ከላንካሻየር ከጓደኞቿ ጋር የመጣችው የ18 ዓመት ወጣት "እዚህ መሆንህ እንድትጨነቅ ያደርግሃል። እስክታየው ድረስ ምን ያህል እንደምታዝን አታውቅም" ብላለች።

"ስለ ጉዳዩ በደንብ ብትማርም ግን ቦታውን ማየት ግን አስገራሚ ስሜት ይፈጥራል" ብላለች ጓደኛዋ። "አንዳንድ ሰዎች ያለ እውነት አይደለም ብለው ማሰባቸው እብደት ነው።"
የቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በብዙ የአውሮፓ አገራት ትልቅ ድል እያስመዘገቡ ነው። የጀርመኑ ኤኤፍዲ በሚቀጥለው ወር ከሚካሄደው ምርጫ በፊት በተደረጉ የህዝብ አስተያየቶች ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ለዓመታት ጎብኚዎችን ወደ ኦሽዊትዝ የወሰዱት የታሪክ ምሁሯ ሱዛን ዊሌምስ፤ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የናዚ እንቅስቃሴ መነሳሳት እና የትኛውም ወታደራዊ የስልጣን ተዋረድ እንዴት ወደ አምባገነንነት የመሸጋገር አደጋ እንዳለው ለማስረዳት የፖሊስ አባላትን ከበርሊን ወደ ኦሽዊትዝ ወስደዋል።
"ይህን እየሠራሁ ያለሁት እነዚህ ሰዎች የፖሊስ እርምጃ ገደብ ምን መሆን እንዳለበት ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስረዳት ነው። ማንኛውም ነገር እንዲያደርጉ ቢጠየቁ መታዘዝ ወይም አለመታዘዝ የራሳቸው ውሳኔ እንደሆነ እና ከእነሱ ግንዛቤ በመነሳት ሰብአዊ መብቶችን የሚጻረር ማንኛውንም ነገር ያለመቀበል መብት አላቸው።"
በኦሽዊትዝ ከሚከበረው መታሰቢያ በዓል በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር በዩናይትድ ኪንግደም የሆሎኮስት (የአይሁዳውያን ጭፍጨፋ) ትምህርትን "እውነተኛ አገራዊ ጥረት" ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
"ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደሚያስተምሩት እናረጋግጣለን። እያንዳንዱ ተማሪ በህይወት የተረፉ ምስክርነቶችን እንዲሰማ ዕድል ለመስጠት እንጥራለን። ምክንያቱም ከተረፉ ሰዎች በመማር ለሌሎች ያለውን ርህራሄ እና ለጋራ ሰብአዊነታችን አድናቆት ማዳበር እንችላለን። ይህም የልዩነት ጥላቻን ለማሸነፍ የመጨረሻው መንገድ ነው።"

ለመታሰቢያው በዓል በፖላንድ ካልተገኙት መካከል በጣሊያ ታዋቂ ሆኑት እና ከኦሽዊትዝ በሕይወት የተረፉት የ94 ዓመቷ ሊሊያና ሴግሬ፤ በሮም በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ ይሳተፋሉ።
የዕድሜ ልክ ሴናተር የሆኑት ሴግሬ በዚህ ወር በህይወታቸው ዙሪያ ዘጋቢ ፊልም ተሠርቶ መለቀቁን ተከትሎ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተስፋፋው የፀረ ሴማዊ ጥቃት ምክንያት የፖሊስ ጥበቃ ይደረግላቸዋል።
አባታቸው እና አያቶቶቻቸው በሙሉ በበርከናዉ ተገድለዋል። ልክ እንደ ጆና ላክስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ በራቨንስብሩክ ማጎሪያ ካምፕ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ማልቾው ቢያቀኑም ከናዚዎች ሞት ተርፈዋል።












