አሜሪካ የፍርድ ቤት ውሳኔንን ወደ ጎን ብላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቬንዙዌላዊያንን ከአገር አባረረች

ስደተኞች ሲባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በዋይት ሀውስ የወሮበላ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ከ200 በላይ ቬንዙዌላዊያን ከአሜሪካ ኤል ሳቫዶር ወደ ሚገኝ ከፍተኛ ጥበቃ እስር ቤት ተወሰዱ።

የኤል ሳቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡክሌ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ትሬን ዲ አሩጋ የተባለ የቬንዙዌላ ወሮበላ ቡድን አባል የሆኑ 238 ሰዎች እና 23 የኤም-13 ወንበዴ ቡድን አባላት እሁድ ጠዋት ማዕከላዊ አሜሪካ መድረሳቸውን አሳውቀዋል።

የአሜሪካ መንግሥትም ይሁን ኤል ሳቫዶር ስለ እስረኞቹ ማንነትም ሆነ ስለ ወንጀላቸው አሊያም ከወንበዴ ቡድኖች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የአሜሪካ የፌደራል ዳኛ በጦርነት ጊዜ የሚተገበረውን እና ለክፍለ ዘመናት የዘለቀውን ከአገር የማስወጣት ሕግ የትራምፕ አስተዳደር እንዳይተገብር እግድ ቢጥሉም በረራዎቹ ቀድመው መነሳታቸው ተነግሯል።

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሊቪት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ስለመጣሱ አስተባብለዋል።

"አስተዳደሩ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አላከብርም አላለም" ብለዋል።

"ሕጋዊ መሰረት የሌለው ትዕዛዙ የሽብርተኛው ቲዲኤ [ትሬን ዲ አሩጋ] አባላት ከአሜሪካ ግዛት እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ነው የወጣው" በማለት አስተባብለዋል።

የኤል ሳቫዶር ፕሬዝዳንት ባሰራጩት ተንቀሳቃሽ ምስል እግር እና እጃቸው በካቴና የታሰሩ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ታጅበው ከአውሮፕላን ሲወርዱ ይታያሉ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ ግዛት ወረራ ለመፈፀም ቢሞከር እና ስጋት በመደቀን የከሰሷቸውን ትሬን ዲ አሩጋ የተባለው ወሮበሎችን ለማባረር መመሪያ አፅድቀዋል።

የወሮበሎች ቡድን "መደበኛ ባልሆነ ጦርነት" በመሳተፋቸው ከ227 ዓመታት በፊት በወጣው እና ለመጨረሻ ጊዜ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓናዊ አሜሪካዊያን ላይ የተፈጸመውን ሕግ በመጠቀም እንደሚያባርሩ ተናግረው ነበር።

ቅዳሜ ምሽት የአሜሪካ ዳኛ ጄምስ ቦስበርህ የትራምፕ መመሪያ እንዳይፈፀም የ14 ቀናት እግድ ጥለዋል።

የሕግ ባለሞያዎች የሚባረሩ ሰዎችን ያሳፈሩ አውሮፕላኖች መነሳታቸውን ሲያሳውቋቸው ዳኛው በረራዎቹ እንዲመለሱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

የወሮበላ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉትን ስደተኞች የያዙ በረራዎች ስንት ሰዓት ላይ እንደተነሱ እስካሁን ግልፅ አይደለም።

የፍትሕ ሚኒስቴር ጠበቆች ስደተኞቹ ከአሜሪካ ግዛት ከወጡ በኋላ እግዱ በመተላለፉ ገቢራዊ እንዳልሆነ ተናግረው፤ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለመቀልበስ ይግባኝ ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ሹም የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ እሁድ ዕለት 261 ሰዎች ከአገር እንዲወጡ መደረጉን ገልፀው፤ 137ቱ ከወሮበላ ቡድን ጋር በተያያዘ የተባረሩ ናቸው ብለዋል።

ቬንዙዌላ የትራምፕን እርምጃ የቬንዙዌላን ስደተኞችን "ያለአግባብ ወንጀለኛ ያደረገ" በሚል ትችት ያቀረበች ሲሆን፤ ከባሪያ ንግድ እስከ ናዚ የማጎሪያ ካምፖች ድረስ የሰብዓዊነት ጥቁር ታሪክ ክፍል እንደገና ያነሳ ነው ብላለች።

የመብት ተሟጋቾች የትራምፕን ውሳኔ በማውገዝ 227 ዓመት እድሜ ያለውን ሕግ መጠቀማቸውን ወቅሰዋል።