ከ30 የሚበልጡ ሰዎች የፊት ቆዳ መሸብሸብን ለማስወገድ በወሰዱት ሕክምና ተመረዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንግሊዝ ውስጥ ባለፉት ሳምንታት የፊት ቆዳ መሸብሸብን ለመከላከል በተሰጠ የቦቶክስ የውበት ሕክምና ጥቅም ላይ በዋለ ሐሰተኛ መድኃኒት ምክንያት ከሰላሳ በላይ ሰዎች የመመረዝ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነገረ።
በፊት ቆዳ ላይ የሚያጋጥም መሸብሸብ እና መጨማደድን ለማስተካከል ለሚሰጠው በዚህ የቦቶክስ ሕክምና አገልግሎት ላይ የሚውለው ንጥረ ነገር ትክክለኛ ካልሆነ እና ካልተመጠነ በተጠቃሚዎቹ ላይ ለጤና ብሎም ለሕይወት አስጊ የሆነ መመረዝን ሊያስከትል ይችላል።
የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ደኅንነት ተቋም እንዳስታወቀው ባለፉት ስድስት ሳምንታት በተለያዩ የእንግሊዝ ክፍሎች ውስጥ ይህ ፈቃድ ያላገኘ ንጥረ ነገር የተሰጣቸው 38 ሰዎች የመመረዝ አደጋ ገጥሟቸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ ሕክምናውን የሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎቱን የሚሰጡት ባለሙያዎች ብቁ መሆናቸውን እና ጥቅም ላይ የሚያውሉት መድኃኒትም ፈቃድ ያለው መሆኑን እንዲያረጋግጡ መክሯል።
በመርፌ የሚሰጠው የቦቶክስ ሕክምና በፊት ላይ የሚወጡ መስመሮችን እና የቆዳ መጨማደድን ለመቀነስ በስፋት የሚተገበር ነው።
ለዚህ ሕክምና ጥቅም ላይ የሚውለው ምርት ቦቱሊኒየም ከሚባለው መርዛማ ንጥረ ነገር የተጣራ ዝቅተኛ መጠን ያለው ቅመም ነው። በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ ከዋለ መመረዝን እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የጤና ደኅንነት ተቋሙ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የመመረዝ ጉዳት ያጋጠመባቸው ሁኔታዎች ትክክለኛውን በሚመስሉ ነገር ግን ፈቃድ ባላገኙ መድኃኒቶች አማካይነት ነው።
በቅርቡ ባጋጠሙት የመመረዝ ችግሮች ምክንያት መድኃኒቶቹን የተጠቀሙ ሰዎች ላይ ለመተንፈስ፣ ምግብ ለመዋጥ እና ለመናገር የመቸገር ሁኔታዎች ያጋጠማቸው ሲሆን፣ ለመተንፈስ የመሳሪያ ድጋፍም አስፈልጓቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በመመረዙ ምክንያት ሰዎች የዓይን ሽፋናቸውን ለመቆጣጠር መቸገር፣ ብዥያለ ዕይታ እና የፊት ጡንቻዎች ደካማ መሆን ያጋጥማቸዋል።
የዩኬ የጤና ደኅንነት ተቋም ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጋውሪ ጋድልቦል በእንዲህ ያለው የሕክምና ሂደት ውስጥ የሚገጥመውን የመመረዝ ምልክቶቹን ለማየት አስከ አራት ሳምንት ሊቆይ ስለሚችል ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች በቶሎ የሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ መክረዋል።
ለፊት እና ለዓይን አካባቢ ቆዳ መሸብሸብ ቦቶክስን በዘፈቀደ መጠቀም እንደማያስፈልግ ያሳሰቡት ባለሙያዋ ከዶክተሮች ወይም ከነርሶች ጋር በሚደረግ ምክክር የሚታዘዝ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ሕክምናውም በብቁ ባለሙያ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ለቦቶክስ አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች ይዘት እና ዓይነት የሚታወቁ እና በሚመለከተው አካል ፈቃድ ያገኙ ካልሆኑ፣ ደኅንነታቸው ያልተጠበቀ እና ለአደጋ የሚያጋልጡ ይሆናሉ ተብሏል።















