ቫይረሶች ለአልዛይመር የመጋለጥ አደጋን ሊጨምሩ እንዲሁም መድኃኒት ሊሆኑ ይችላሉ?

በእድሜ የገፉ ሰው ተቀምተው ምርኩዛቸው ላይ ጭንቅላታቸውን አሳርፈው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አልዛይመር እድሜያቸው ከ65 በላይ በሆናቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት የመርሳት ሕመም ነው

ፕሮፌሰር ሩት ኢትዝሃኪ ለአስርት ዓመታት የአልዛይመር በሽታ መንስኤዎችን እና ሕክምናን ሲያጠኑ ቆይተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 57 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በሚያጠቃው በዚህ በሽታ ውስጥ አንድ ግኝትን በመፈለግ ዓመታትን አሳልፈዋል።

ይህ በሸታ የአእምሮ ሕመም፣ የመርሳት ሕመም፣ የግለሰቦችን ትውስታ እንዲሁም ቀስ በቀስ ማንነታቸውን ይሰርቃል።

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከሚገኘው የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ፕሮፌሰር ኢትዛኪ የተለመዱ ቫይረሶች በአልዛይመር በሽታ እድገት ውስጥ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ከተጠራጠሩ እና ካሳዩ የመጀመሪያዎቹ የነርቭ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ነበሩ።

ነገር ግን ፈታኝ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ኢትዛኪ "ሳይንሳዊ ጽሑፎቻችን ተቀባይነት አግኝተው በአካዳሚክ መጽሔቶች ላይ እንዲታተሙ ማድረግ አልቻልንም። በዚህም የተነሳ ለአዲስ ምርምር የገንዘብ ድጋፍ አላገኘንም። በቂ ገንዘብ ከሌለ ደግሞ ጥናታችንን ለመቀጠል አስቸጋሪ ነበር" ብለዋል ።

ፕሮፌሰር ኢትዛኪ በዚያን ጊዜ የእርሷ እና የሌሎች ተመራማሪዎች ሥራ የበለጠ ትኩረት ቢያገኙ ኖሮ ስለ የመርሳት በሽታ መንስዔዎች እና ዛሬ እሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የተሻሉ መንገዶች ላይ የበለጠ ሰፊ ግንዛቤ ሊኖር ይችል እንደነበር ያምናሉ።

ፍጥነቱ እየተቀየረ ቢሆንም ባለፉት አራት ዓመታት አልዛይመርን ለመከላከል የሚያስችሉ ምርምሮች ተጀምረዋል።

የመጀመሪያው የክትባት ሙከራ እንዲሁም በተለምዶ የቫይረስ ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚውሉ የፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች ላይ ጥናቶች እየተደረጉ ነው።

በአንጎል ውስጥ የሚከሰት እብጠት ሚና

ከሠላሳ ዓመታት በፊት 'አሚሎይድ ካስኬድ' የተባለው መላምት ለአልዛይመርስ እንደ ዋና ማብራሪያ በመሆን ትኩረት መሳብ ጀመረ።

በአንጎል ውስጥ የሚከሰት እብጠት ቤታ-አሚሎይድ የተባለ ፕሮቲን እንዲከማች ያደርጋል።

ይህ ጭጋጋማ ፈሳሽ ክምችት ይፈጥራል፤ በማስከተልም እዚያ ባሉ የነርቭ ሴሎች ግንኙነት ውስጥ ጣልቃ መግባት ይጀምራል።

በአንጎል ውስጥ የሚገኘው ሌላው የፕሮቲን ዓይነት 'ታው' በተጨማሪም በዚህ ክምችት የተነሳ ሥራውን በአግባቡ መከወን ስለማይችል በነርቭ ሴሎች ውስጥ መቀላቀል ይጀምራል።

የታው ፕሮቲን በተለምዶ የነርቭ ሴሎች መልዕክቶችን በብቃት ለማጓጓዝ እና እርስ በርስ እንዲግባቡ ቅርጻቸውን እንዲጠብቁ ይረዳል።

በጥቅሉ የደመናማው ንጣፍ ክምችት እና የተጠላለፈው የታው ፕሮቲን የነርቭ ሕዋሳትን እና የአንጎልን ተግባርን ይጎዳል።

ይህ የነርቭ ሕዋሳት እንዲሞቱ ያደርጋል። ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የማስታወስ ችሎታ መቀነስ፣ የማመዛዘን ችግር፣ የስሜት መለዋወጥ እና ሌሎች የአልዛይመርስ ምልክቶችን ያስከትላል።

የሳኦ ፓውሎ የሕክምና ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት ሮቤርታ ዲሄል ሮድሪጌዝ የተባሉ የነርቭ ሐኪም "እነዚህን ሁለት ፕሮቲኖች በአንጎል ውስጥ እንዲቀመጡ የሚያደርገው ምን እንደሆነ እስካሁን አናውቅም" ብለዋል።

በከንፈሩ ላይ ኣለበትን ቁስል በጣቱ የሚጠቁም ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሀርፒስ ሲምፕሌክስ ቫይረስ ዓይነት 1 ቁስለት የሚያስከትል ቫይረስ ነው

ቫይረሶች የመርሳት በሽታን ሊያስከትሉ ይችላሉ?

በሕክምናው ዓለም ዛሬ ቫይረሶች ዳግም ከመነቃቃታቸው በፊት በሰውነት ውስጥ አንቀላፍተው እንደሚቆዩ ይታወቃል።

ከአርባ ዓመታት በፊት ፕሮፌሰር ኢትዛኪ በሰው አእምሮ ውስጥ ስላለው የሄርፐስ ሲምፕሌክስ ቫይረስ ዓይነት 1 (herpes simplex virus type 1) የዘረ መል ስብጥር የመጀመሪያ ጥናቶችን ማካሄድ ጀመሩ።

ይህ በጣም የተለመደ ቫይረስ ሲሆን ቁስሎችን ያስከትላል፤ እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆነውን የዓለማችንን ሕዝብም ይጎዳል።

በዚህ ፈር ቀዳጅ ጥናት ነው ቫይረሱን በአንጎል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት። እስከዚያ ድረስ ግን ማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓት ከእነዚህ ቫይረሶች የተጠበቀ እንደሆነ ይታመን ነበር።

"ከዚያም በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ሄርፐስ እንደገና እንዲያንሰራራ መደረጉ በነርቭ ሥርዓት ሕዋሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመጨረሻም ወደ [ሕዋሳት] ሞት የሚያመሩ ተከታታይ ክስተቶችን ይቀሰቅሳል ብለን መገመት ጀመርን" ብለዋል ፕሮፌሰር ኢትዛኪ።

በዚያን ጊዜ ተመራማሪዎች ሄርፐስ በአልዛይመርስ በተያዙት ሰዎች እና በሕይወት ዘመናቸው በበሽታው ያልተያዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ መገኘቱ አስገርሟቸዋል።

ይህም ሳይንቲስቶች በቫይረሱ ​​​​የተያዙ አንዳንድ ሰዎች የመርሳት በሽታ ያጋጠማቸው እና ሌሎች ለምን እንዳላጋጠማቸው የሚያብራሩ እንደ ዘረመል ያሉ ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ ይገባል ብለው እንዲደመድሙ አድርጓቸዋል።

በአእምሮ ውስጥየሚገኙ ኒውሮኖችን ንድፍ

የፎቶው ባለመብት, Artur Plawgo/Science Photo Library/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአንጎላችን ውስጥ ኒውሮኖች ሲሞቱ የማስታወስ ችሎታ ይጠፋል

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በፕሮፌሰር ኢትዛኪ የተመራ ቡድን በቤተ ሙከራ የሚገኙ አይጦች ሄርፐስ የተባለው የአባላዘር በሽታ ቫይረስ በአንጎላቸው ክፍል ተከማችቶ እንደሚገኝ መለየት ችሏል።

ይህም አዲስ ፅንሰ ሐሳብ እንዲፈልቅ አደረገ። ይህ ፕሮቲን ቫይረሱን ለመቆጣጠር እና ለማክሸፍ በማለም ለመከላከያ ሲባል የነርቭ ሥርዓት ያመረተው ይሆን?

እነዚህ ሞሎኪሎች ተለጣፊ ባህሪ እንዳላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ሰፋ ያለ በሽታ የመከላከል እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ቫይረሱ እንዳይራባ ሊያደርግ ይችላል።

ይሁን እንጂ የሄርፐስ ቫይረስ ተደብቆ መቆየት የሚችል እና በሕይወት ዘመን እርሱን በመግለጥ በአንጎል ላይ ተደጋጋሚ እብጠት እንዲከሰት በማድረግ እና ቤታ አንፕሎይድ በተደጋጋሚ እንዲመረት ያደርጋል።

ከጊዜ በኋላ የመከላከያ መንገድ ሆኖ ያገለገለው ፕሮቲን፣ የነርቭ ሕዋሳትን በመጉዳት ችግር ይሆናል። በኋላም ላይ የሕዋሳትን ሞት ያስከትላል።

የክትባቶች ሚና

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስለዚህ ይህን ለመከላከል ምን ማድረግ አለብን?

እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 የዌልስ መንግሥት የሽንግልስ ክትባት ዘመቻ ሲጀምር በጣም ግልፅ መመሪያዎችን ነበር ያስቀመጠው።

ሽንግልስ 'ቫርሲላ-ዞስተር' የተባለ ቫይረስ እንደገና ሲመጣ የሚከሰት እና በቆዳ ላይ በጣም ሕመም ያለው የማሳከክ ስሜት በማድረስ ይታወቃል።

በአውሮፓውያኑ ከመስከረም 2/1933 እስከ መስከረም1/1934 የተወለዱ ሰዎች ብቻ ናቸው ክትባቱን መመውሰድ የሚችሉት።

በአሜሪካ ስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል የኢፒዲሞሎጂ እና ሥነ ሕዝብ ጤና ፕሮፌሰር የሆኑት ፓስካል ግለድስተዘር "በክሊኒክ ውስጥ በነበረው ሙከራ ወቅት ከገጠመን ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሞናል። ሁለት ቡድኖች በብዙ መልኩ በጣም ተመሳሳይ ሁኔታ ያላቸው ሲሆኑ፤ ልዩነታቸው የሽንግልስን ክትባት ለመውሰድ ብቁ ነበሩ" ይላሉ።

የትንተናው ውጤት ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች መካከል በቀጣይ ሰባት ዓመታት ውስጥ ከዕድሜ ብዛት በሚከሰተው የመርሳት በሽታ (ዲሜንሺያ) የመያዝ ዕድላቸው ከአማካዩ ያነሰ 3.5 በመቶ ነው።

ይህ ምጣኔ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል።

"ጥናታችን እንደሚያሳየው አሁን ያለውን የመርሳት በሽታ የሚከላከሉ መድኃኒቶች በላቀ ደረጃ የመከላከያ ተፅዕኖ አለው" ይላሉ።

ነገር ግን ለውጡ ምን ተብሎ ይብራራል?

"እየተጠናከረ ያለ ማስረጃ የሚጠቁመው በነርቭ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ቫይረሶች በአብዛኛው በሕይወት ዘመን የሚቆዩ ከሆነ የመርሳት በሽታ እንዲዳብር ሊያደርጉ ይችላሉ" ይላሉ ፕሮፌሰር ግለድስተዘር።

በዚህ ረገድ የሽንግልስ ክትባት ቫይረሱ ድጋሚ እንዳያገረሽ ያደርገዋል። እናም እብጠት የሚያስከትለው እና 'ቤታ-አምሎይድ' እንዳይቀሰቀስ ተላላፊው የቫይረስ ወኪል ይከላከላል።

ፕሮፌሰር ግለድስተዘር አክለውም "የክትባቶች ተፅዕኖ በበሽታ መከላከል ሥርዓት ውስጥ ለአንድ በሽታ አምጭ አካል መከላከያ ከመሆን የሰፋ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉን። እናም ይህ ሰፊ ተፅዕኖ በሽታዎችን ለመከላከል ጥቅም ይኖረዋል።"

በአዲሱ ጥናት ላይ የተሳተፉ አሁን የተለመደው የክሊኒካል ሙከራ ማድረግ ይፈልጋሉ። ይህም ፈቃደኞችን መመልመል፣ በቡድን መከፋፈል እና ክትባቱ ለመርሳት በሽታ የሚኖረውን ተፅዕኖ መገምገምን ያካትታል።

"የሽንግልስ ክትባት የመርሳት በሽታን መከላከል ወይም ማዘግየት የሚችል ከሆነ፤ በጣም ትልቅ ግኝት ነው የሚሆነው" ይላሉ።