መርሳት ፡ የሰው ስም መርሳት በሽታ ነው? መፍትሄስ አለው?

የፎቶው ባለመብት, Alamy
አንድ አባት ከእርጅና ምን ጠሉ? ምንስ ወደዱ ተባሉ።
"ነገር መርሳትን ወደድኩት፣ ስም መርሳትን ጠላሁት" አሉ።
የስም መርሳት በእሳቸው ዕድሜ ባስ ይበል እንጂ የጎልማሶችም፣ የወጣቶችም ችግር ነው። ሳይንቲስቶች ግን ሊያሳስብ አይገባም፤ መፍትሄ አለው ይላሉ።
የሰው መልክን የማይረሱ ሰዎች ስሞቻቸውን ማስታወስ ግን በአያሌው ሲከብዳቸው ይታያል።
የምናውቀው የሰው ስም ወይም ቃል፣ "ምላሴ ላይ እኮ ነው ያለው" እንላለን። ግን ማስታወሱ ስቃይ ይሆንብናል።
ባስ ሲልም እናት ያሳደገቻቸው የልጆቿን ስም በቅጽበት ማስታወስ ምጥ ሊሆንባት ይችላል። ማስታወስ ከወሊድ በኋላ ትንሽ እየባሰም ይሄዳል ይባላል።
ሳይንቲስቶች ግን ስምን አለማስታወስ ከማስታወስ ችሎታ መላሸቅ ጋር ላይያያዝ ይችላል ይላሉ።
ድሮ ከምናውቃቸው ሰዎች አንድን ሰው ፊቱን፣ ድርጊቱን፣ አለባበሱን ጭምር እያስታወስን ስሙ ግን በፍጹም አልመጣ ይለናል።
አብረውን ያሉ ሰዎች ለረሳነው ሰው ሦስት የስም ምርጫ ቢሰጡን ግን ወዲያውኑ እናስታውሰዋለን። ታዲያ የዚያ ሰው ስም ለምን ጠፋን?
ችግሩ ያለው ስሙንና ምሥሉን ከማስተሳሰር እንጂ የማስታወስ ችግር ብቻ አይደለም የሚባለው ለዚሁ ነው።
ይህ አባዜ ከሰው ስም ጋር ብቻ የሚተሳሰር አይደለም። አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ የድርጊት ቃሎችም ብን ብለው ሊጠፉብን ይችላሉ። "ምንድነው እንኳ የሚባለው? አስታውሰኝማ…!" እያልን ፍዳችንን ልንበላ እንችላለን።
ቃል ብን ብሎ የሚጠፋው ነገር ከዕድሜ ጋር በተደጋጋሚ የሚያያዝ ተደርጎ ይታሰባል። ለዚህም ነው የሰው ስም ሲጠፋን "አይይ… አረጀሁ መሰለኝ" የምንለው።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት መጀመሪያ ከትዝታ ቋት ውስጥ እየከሰሙ የሚመጡት የቃላት ክምችቶች የተጸውዖ ስሞች (Proper Nouns) እና የቁሳቁስ ስሞች ናቸው።
ስሞቹ ከማስታወሻ ቋታችን ስልብ ብለው የሚጠፉበት የጊዜ ርዝማኔ ከሰከንዶች ሽርፍራፊ እስከ ሰዓታት ሊዘልቅ ይችላል፤ እንደየሰው ማለት ነው።
ነገሩ ደግሞ አሳሳቢ የሚሆነው አእምሯችን እየከዳን ነው ስንል ይበልጥ እየከዳን መምጣቱ ነው።
"የምንነግረውን ነገር ያምናል፤ ያመነውን ይፈጽማል። ይህ አስደናቂ የአእምሮ ባህሪ ነው" ይላሉ ሳይንቲስቶች።
የሚደንቀው ደግሞ በፍጹም እንረሳቸዋለን ብለን ያልጠበቅናቸው ዕለታዊ ተራና ተዘውታሪ ቃላት ድንገት ሳናስበውና ሳንገምተው ጭልጥ ብለው የመጥፋታቸው ነገር ነው።
ይህ የነገርና የሰው ስምን የመርሳት አባዜ እየተሻሻለ ሳይሆን እየባሰበት ነው የሚሄደው።
ደግሞም የሚጠፉብን ቃላት ምላሳችን ድንበር ላይ ቁጭ ብለው እየደነሱ ይታዩናል። እየሳቁብን እናያቸዋለን። እያሾፉብን፣ ምላሳቸውን እያወጡብን ነው። ግን አናስታውሳቸውም። የሚያበሳጩንም ለዚሁ ነው። በእንግሊዝኛ (at the tip-of-the-tongue) የሚባለው ለዚሁ ይሆን?
አሁን ነገር ማርዘሙን ትተን መፍትሄ ላይ እናውራ።
የቋንቋና ሥነ ልቡና ተመራማሪዎች በምሥል ማሰብ የሚሉት አባባል አለ። አንድን ነገር አእምሮ የሚያውቀው በምሥል ቀርጾ ሲያስቀምጠው ነው። እያንዳንዱን ቃል በቋት በቋት ስናስቀምጠው ባናውቀውም የሆነ ምሥል እየሰጠን ነው።
ያ ምሥል ከቃሉ ጋር ተጠፍንጎ አእምሯችን ላይ ሲታሰር መፈናፈኛ አይኖረውም። የምንፈልገው ቃል ያለ ምንም ትግል የሚታዘዝልንም ከምሥል ጋር ስለሳልነው ሊሆን ይችላል።
ሌላው መፍትሄ "እረሳለሁ" እያሉ አእምሮን አለመንገር ነው። "እንዴት ይሄ ይጠፋብኛል?" ብለን ስለ መርሳታችን ስንብሰለሰል ይብሱኑ ቃሉን የሚወክልልን ነገር/የሰው ምስል እናከስመዋለን።
አእምሮ ድንቅ ነገር ቢሆንም ካሳነፍነው የመስነፍ ባህሪ አለው።
የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን እንሰሳትም ነገርን የሚያስታውሱት በምሥል ነው። ከመንጋቸው ውስጥ ማን የትኛው ነው? ማን ምንድነው የሚለውን በይበልጥ ምሥል ነው የሚገልጥላቸው።
ቦርሳዬ ውስጥ ትንሽዬ ድመት ይዣለሁ ብዬ ብናገር ሁላችሁም ድመቷ በእዝነ አእምሯችሁ ተከስታለች።
"ወይንሸት የምትባለው ጓደኛዬ አንድ ጊዜ ምን አለችኝ…" እያልኩ ባወራ ወይንሸት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከአእምሯችን ጓዳ ተፍቃለች። ምክንያቱ ደግሞ ወይንሸትን የሚወክልልን ምሥል አእምሯችን ከቋት ፈልጎ ሊያገኝ አለመቻሉ ነው።
ለስም መርሳት ሌሎች ምክንያቶችም ይኖራሉ። አንዱ የድግግሞሽ ማጣት ነው። አንድን ቃል እጅግ አልፎ አልፎ ወይም በተወሰነ አውድ ብቻ የምንጠቀምበት ከሆነ አእምሮ ጓዳ ወስዶ ያስቀምጠዋል። ቃሉን ስንፈልገው አእምሮ የሚለግመውም ለዚሁ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር ተዋውቀን ስማቸውን ይነግሩንና ወዲያውኑ እንረሳዋለን። በሌላ ጊዜ ስናገኛቸው ሀፍረት ይይዘናል። ደግሞ መጠየቅም ነውር ሆኖ ይሸብበናል። ለምን ስማቸውን ረሳነው?
ቀጥተኛው መልስ ስንተዋወቃቸው ለአእምሯችን የነገርነው "ይህን ስም ቋት ውስጥ አታስቀምጠው፤ ጭንቅላትን ማጣበብ ነው" ብለን ነው።
ወይም በልቦናችን እንደዚያ አስበናል። ስለዚህ የስም መርሳቱ ለነገሩ ከሰጠነው ዝቅ ያለ ግምት ሊመነጭ ይችላል።
ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እንርሳ ብለን ሳይሆን አንረሳም ያልናቸውን ስሞችን እንረሳለን።
የአእምሮ ጠበብቶች እንደሚሉት ከተለመዱ ስሞች ይልቅ አእምሯችን ያልተለመዱ ስሞችን የመያዝ ዝግጁነት አለው።
ይህም የሚሆነው የተለመዱ ስሞች ብዙ ምሥሎችን (ሰዎችን) ስለወከልንባቸው በቀላሉ ሊሰወሩ ስለሚችሉ ነው።
የተለየ ስም ስንሰማ ግን አዲስ የአእምሮ መሳቢያ (ፎልደር) ውስጥ ነው የምናስቀምጠው፤ ከዚያም ምሥል ከተን።
"ትዝታ" የምትባል ልጅ የምትወክለው አንድ ፊት ላይሆን ይችላል። ብዙ ትዝታዎችን የምናውቅ ከሆነ አእምሮ ስሙን ከእሷ ጋር ብቻ ለማስተሳሰር ትንሽ ሊደነቃቀፍ ይችላል።
"ፍካት" የምትባል ልጅ ብንተዋወቅ ግን ምናልባት ይህ ስም ብዙም ያልተመደ ከመሆኑ ጋር፣ አልያም ልጅቱ ስትተዋወቀን ፍክትክት ብላ መታየቷ ስምና ምሥል ጥምረታቸው ዘላቂ ሆኖ በአእምሯችን ይቀመጣል።
ሌላው መፍትሄ ይላሉ ሳይንቲስቶች፣ ስሞችን ከሌላ ተጨማሪ ቅጽል ስም ጋር ማስተሳሰር ፍቱን መድኃኒት ነው።
ለምሳሌ ስሞች በጥምረት ሲመጡ በቀላሉ የሚታወሱ ይሆናሉ።
አበበ የሚለው ስም ካልተጣመረ ብዙም ለትዝታ ቅርብ አይሆንም። አበበ ቢቂላ፣ አበበ ግደይ፣ አበበ በለው… አበበ ባልቻ… የሚሉ ጥምረቶች የሚመጡልን አንድም ድግግሞሹ አንድም አእምሮ ተጣማሪ ስም ማስታወስ በመቻሉ ነው።
ለዚህም ነው አዲስ ስም ስንተዋወቅ ያንን ስም ከሰውየው አንድ ልዩ ገጽታ ጋር ማያያዝ ለአእምሮ ጠቃሚ የሚሆነው።
ትዝታ የሚረሳ ስም ነው። ጠይሟን ትዝታን ከቆዳ ቀለሟ ጋር አስተሳስረን ለአእምሮ ብንነግረው ግን ላይረሳ ይችላል።
ሌላው መፍትሄ ሰዎችን ከተዋወቅን በኋላ ያሉትን ደቂቃዎች በምንለዋወጠው ወሬ የተዋወቅነውን ሰው ስሙን ደግሞ መጥራት በጣም ተቃሚ ይሆናል።
"እሺ ትዝታ…እና አሁን የት ነው ያለሽው?" ብሎ እንደመጠየቅ።
ይህ ሂደት አእምሮ ስሙን ጥሩ ቦታ አስቀምጥልኝ፣ ወደፊት ስፈልገው ትነግረኛለህ ብሎ የመንገር ያህል ነው።
በዋናነት ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎ አለመሳል ነው። አእምሯችን በምንፈልገው መልኩ ማሰልጠን እንችላለን። ስም መርሳታችን ሊያስጨንቀን አይገባም።
ምክንያቱ ደግሞ ይህን ሁሉ የሚመክሩን የዘርፉ ባለሙያዎችም ጭምር ስማችንን ብንነግራቸው በሚቀጥለው ደቂቃ ይረሱታል።















