ፕሬዚዳንት ፑቲን የመከላከያ ሚኒስትራቸውን ወደ ሌላ ኃላፊነት ሊያዛውሩ ነው

 የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለረዥም ጊዜ በመከላከያ ሚኒስትርነት ያገለገሉትን ሰርጌይ ሾይጉን ወደ ሌላ ኃላፊነት ሊያዛውሩ መሆኑን የክሬምሊን ቤተ መንግሥት አስታወቀ።

ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ በመከላከያ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ሰርጌይ በቀጣይም የሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ጸሐፊ ሆነው ይሾማሉ።

የ68 ዓመቱን መከላከያ ሚኒስትር ተክተው የሚሾሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድሬ ቤሎሶቭ እንደሚሆኑም ከሩሲያ ፓርላማ የላይኛው ምክር ቤት የወጣው ሪፖርት አረጋግጧል።

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት መከላከያ ሚኒስትሩ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ይታመናል።

ከሩሲያ መንግሥት የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው መከላከያ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ስልጣን ያለውን የጸጥታ ምክር ቤት ኃላፊነትን አሁን ካሉት ጸሐፊ ኒኮላይ ፓትሩሼቭ እንዲረከቡ ፑቲን ይፈልጋሉ።

ኒኮላይ ፓትሩሼቭ በቀጣዩ በምን ኃላፊነት እንደሚቀመጡ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ሰርጌይ ሾይጉ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን በርካታ ጊዜም ፕሬዚዳንቱን ወደ ትውልድ ቀያቸው ሳይቤሪያ አሳ ለማጥመድ ወስደዋቸዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ወታደራዊ ታሪክ የላቸውም እንዲያውም በሙያቸው ሲቪል መሐንዲስ ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ የአደጋ እና የእርዳታ ሚኒስቴር የነበሩት ሰርጌይ በዚያ ኃላፊነታቸውም ወቅት ስመ ጥር ለመሆን በቅተዋል።

በተለይም ሩሲያ ከሁለት ዓመት በፊት ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ልምድ እንደሚጎድላቸው አሳብቆ ነበር ሲል የቢቢሲ አውሮፓ ተንታኝ ዳኒ አበርሃርድ ያስረዳል።

ባለፈው ዓመትም የመከላከያ ሚኒስትሩ በጦርነቱ አቅጣጫ ምክንያት ከሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር ኃላፊ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከፍተኛ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ነበር።

በሩሲያ ላይ በአጭሩ የተቀጨ ዓመጽ አስነስቶ የነበረው ፕሪጎዢን መከላከያ ሚኒስትሩን “ቆሻሻ”፣ “ከዕድሜው የቀለለ” በሚል አዋርዷቸዋል።

ፕሪጎዢን ከሴይንት ፒተርስበርግ ወደ ሞስኮ እየበረረ ባለበት ወቅት በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ህይወቱ አልፏል።

ክሬምሊን አደጋውን አላደረስኩም ሲል አስተባብሏል።

ሰርጌይን የሚተኩት አንድሬ ቤሌሶቭ ብዙም የውትድርና ልምድ የሌላቸው የምጣኔ ኃብት ባለሙያ ናቸው።

ሹመታቸው ለአንዳንዶች አስገራሚ ይሆናል ተብሏል። ነገር ግን አንዳንድ ተንታኞች በበኩላቸው ይህ አርምጃ ፕሬዚዳንት ፑቲን የሩሲያን ምጣኔ ኃብት ከጦርነቱ ጋር በቅርበት ለማስተሳሰር እንደሚፈልጉ አመላካች ነው ይላሉ።