የአሳማ ኩላሊት በንቅለ ተከላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለገሰው ግለሰብ ህይወቱ አለፈ

የ62 ዓመቱ ሪቻርድ "ሪክ" ስላይማን የመጀመሪያውን የአሳማ ኩላሊት ተሰጥቶት ነበር

የፎቶው ባለመብት, Massachusetts General Hospital

በዘረመል ምህንድስና የተሻሻለ የአሳማ ኩላሊት በንቅለ ተከላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለገሰው ግለሰብ ከህክምናው ሁለት ወራት በኋላ ህይወቱ ማለፉን ሆስፒታሉ አስታወቀ።

የ62 ዓመቱ ሪቻርድ "ሪክ" ስላይማን ቀዶ ህክምናውን በመጋቢት ወር ከማድረጉ በፊት በከፋ የኩላሊት ህመም ይሰቃይ ነበር።

ህይወቱ ያለፈው በንቅለ ተከላው ምክንያት ስለመሆኑ ምንም ምልክት የለም ሲል የማሳቹሴትስ አጠቃላይ ሆስፒታል (ኤምጂኤች) እሑድ ዕለት አስታውቋል።

በዘረመል ምህንድስና ከተሻሻሉ አሳማዎች የተገኙ ክፍሎችን ሌሎች የመተካት ሙከራ ቀደም ሲል አልተሳካም ነበር። የስላይማን ቀዶ ህክምና ግን ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ተብሎ ተወድሷል።

ከኩላሊት ህመም በተጨማሪ ስላይማን የስኳር በሽታ እና የደም ግፊት ነበረበት።

እአአ በ 2018 የሰው ኩላሊት ንቅለ ተከላ ቢያከናውንም ከአምስት ዓመታት በኋላ መሥራት ማቆሙ ተነግሯል።

የአሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላውን ተከትሎ፤ አዲሱ ኩላሊቱ በጥሩ ሁኔታ እየሠራ በመሆኑ የኩላሊት እጥበት (ዳያሊሲስ) እንደማያስፈልገው ዶክተሮቹ አረጋግጠው ነበር።

"ስላይማን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ህሙማን የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ ሆኖ ይታያል። ‘የዜኖትራንስፕላንቴሽን’ መስክን ወደፊት እንዲራመድ ላሳየው እምነት እና ፍቃደኝነት በጣም እናመሰግናለን" ሲል ሆስፒታሉ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ዜኖትራንስፕላንቴሽን ህይወት ያላቸው ሴሎችን ወይም የአካል ክፍሎችን ከአንድ ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ መተካት ነው።

በድንገተኛው ሞት “በጣም አዝነናል” ያለው ሆስፒታሉ ለቤተሰቡ መጽናናትን ተመኝቷል።

የስላይማን ዘመዶች በበኩላቸው የሱ ታሪክ ለብዙዎች ብርታትን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

"ሪክ ይህን ህክምናውን ከፈቀደባቸው ምክንያቶች አንዱ በሕይወት ለመትረፍ ንቅለ ተከላ ለሚያስፈልጋቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋ ለመስጠት ነው" ብለዋል።

"ሪክ ግቡን ከማሳካቱም በላይ ተስፋው እና እምነቱ ለዘላለም ይኖራል።”

"ለእኛ ሪክ ደግ ልብ ያለው፣ አስተዋይ፣ ቀልድ አዋቂ፣ ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹ እና የሥራ ባልደረቦቹ የሚጨነቅ ሰው ነበር" ሲሉ አክለዋል።

ስላይማን የመጀመሪያውን ለሰው የተሰጠ የአሳማ ኩላሊት ቢቀበልም፤ በንቅለ ተከላ ታሪክ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለ የመጀመሪያው የአሳማ አካል ግን አይደለም።

ሁለት ታካሚዎች የአሳማ የልብ ንቅለ ተከላዎችን አከናውነዋል። ሁለቱም ግን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ህይወታቸው በማለፉ ሂደቶች አልተሳኩም።

የአንደኛው ታካሚ የበሽታ መከላከያ ስርዓት የአሳማውን ልብ አለመቀበሉን የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ። ይህም በንቅለ ተከላ ውስጥ የሚያጋጥም ነገር ነው።