የአሳማ ኩላሊት በንቀለ ተከላ የተሰጠው ግለሰብ ከሆስፒታል ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Massachussets General Hospital
በሳይንሳዊ መንገድ የተሻሻለ የአሳማ ኩላሊት በንቅለ ተከላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ግለሰብ ከሆስፒታል ወጣ።
የ62 ዓመቱ አዛውንት በማሳቹሴትስ ጠቅላላ ሆስፒታል ከሁለት ሳምንት በፊት የቀዶ ጥገናው ከተደረገለት በኋላ ረቡዕ ወደ ቤት ተልኳል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በዘረመል ምህንድስና (ጄነቲካሊ ሞዲፋይድ) የተሻሻሉ የአሳማ የሰውነት ክፍሎችን ለሰዎች ለመስጠት የተደረጉት ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል።
የአሁኑ ንቅለ ተከላ ስኬት በሳይንስ ሊቃውንት ዘንድ ታሪካዊ ምዕራፍ በሚል እየተወደሰ ይገኛል።
በአሜሪካ ቦስተን ከተማ የሚገኘው የሃርቫርድ ሜዲካል ትምህርት ቤት ዜናውን ረቡዕ ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አጋርቷል።
ሆስፒታሉ በመግለጫው እንዳስታወቀው ከሆነ የማሳቹሴትስ ነዋሪ የሆነው ሪቻርድ “ሪክ” ስላይማን በመጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ የኩላሊት በሽታ ጋር እየታገለ የነበር እና ንቅለ ተከላም ያስፈልገው እንደነበር ገልጿል።
ዶክተሮቹ አራት ሰዓታትን በፈጀ ቀዶ ህክምና በዘረ መል ምህንድስና የተስተካከለ የአሳማ ኩላሊት በተሳካ ሁኔታ ተክተውለታል።
የስላይማን ኩላሊት በጥሩ ሁኔታ እየሠራ በመሆኑ ዳያሊሲስ እያከናወነ አይደለም ሲልም መግለጫው አክሏል።
ከሆስፒታል መውጣት እና ወደ ቤት መሄድ መቻል በህይወቱ “በጣም አስደሳች ከሆኑ ጊዜያቶች አንዱ” መሆኑን ስላይማን ተናግሯል።
"ለብዙ ዓመታት ጥራት ያለው ህይወት እንዳልመራ ተጽዕኖ ካሳደረብኝ የዳያሊስስ ሸክም ነፃ በመሆን ከቤተሰቦቼ፣ ከጓደኞቼ እና ከምወዳቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ለማሳለፍን በመቻሌ ደስተኛ ነኝ" ሲል አክሏል።
እአአ በ 2018 በህይወት ከሌለ ለጋሽ ግለሰብ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ቢደረግለትም ባለፈው ዓመት ጀምሮ ሕመሙ ማገርሸቱ ታውቋል። በዚህ ወቅት ነው የሕክምና ባለሙያዎች የአሳማ የኩላሊት መተካት ሐሳብን ያመጡት
"እኔን ለመርዳት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ለመትረፍ ንቅለ ተከላ ለሚያስፈልጋቸው በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋ የሚሰጥ አማራጭ አድርጌ ቆጥሬዋለሁ" ብሏል።
የተተካለትን አዲሱን የአሳማ ኩላሊት መቀመጫውን በካምብሪጅ ያደረገው ኢጀነኒስ የተባለ የፋርማሲዩቲካል ኩባንያ "ጎጂ የሆኑ የአሳማ ጂኖችን በማስወገድ እና ከሰዎች ጋር እንዲዋሃድ ለማድረግ የተወሰኑ ዘረ መሎችን በመጨመር" አሻሽሏል።

የፎቶው ባለመብት, Massachussets General Hospital
ንቅለ ተከላው በአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር ፈቃድ ተሰጥቶታል።
ንቅለ ተከላው ቡድን በተለይም ለንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸውን የሰውነት አካል ማግኘት ለማይችሉ ሕክምናው ታሪካዊ እርምጃ ነው ሲል አሞካሽቶታል።
መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው እና ለትርፍ ያልተቋቋመው ዩናይትድ ኔትወርክ ፎር ኦርጋን ሼሪንግ ባወጣው መረጃ መሠረት ከ100 ሺህ በላይ አሜሪካውያን ሕይወት አድን የአካል ንቅለ ተከላ ያስፈልጋቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2023 ያለው የለጋሾች ቁጥር ከ23 ሺህ 500 በታች ነበር።
አሜሪካ ውስጥ በየቀኑ 17 ሰዎች የአካል ንቅለ ተከላ እየጠበቁ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ተገልጿል። ኩላሊት ደግሞ ለንቅለ ተከላ በይበልጥ የሚፈለገው የሰውነት አካል ነው።
ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰው የተተከለ የአሳማ ኩላሊት ቢሆንም፣ በንቅለ ተከላ ለሰው የተሰጠ የመጀመሪያው የአሳማ አካል ግን አይደለም።
ሁለት ታካሚዎች የአሳማ የልብ ንቅለ ተከላዎችን አከናውነዋል። ሁለቱም ግን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ህይወታቸው በማለፉ ሂደቶች አልተሳኩም።
የአንደኛው ታካሚ የበሽታ መከላከያ ስርዓት የአሳማውን ልብ አለመቀበሉን የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ። ይህም በንቅለ ተከላ ውስጥ የሚያጋጥም ነገር ነው።












