ተበዳሪዎችን በፍርሃት የሚያርበደብዱት የ83 ዓመቷ እንግሊዛዊት 'አራጣ አበዳሪ'

ታቢራ ሪቻርድሰን

የፎቶው ባለመብት, Cardiff council

የምስሉ መግለጫ, ታቢራ ሪቻርድሰን ተበዳሪዎችን በማስፈራራት ይታወቃሉ

ተግባራቸው ለአንቱታ ባያበቃቸውም ታቢታ ሪቻርድሰን ይባላሉ።

በዚህ ዕድሜ ያሉ ሴት ቢሆን-ቢሆን ይመንናሉ። እሳቸው ግን ተበዳሪን በቁም ያስባንናሉ። ለዓለም ዜና የበቁትም ለዚሁ ነው-ከሰሞኑ-በዩኬ።

ሴትዮዋ ሲያበድሩ ዐይን የላቸውም። የፋይንስ ቀውስ ውስጥ የገባ ቤተሰብ ሲያዩ ደስ ይሰኛሉ።

ለተቸገረ ደራሽ-ለተራበ አጉራሽ ሆነው ይቀርባሉ። የሚያበድሩት ገንዘብ ሁሉ የአራጣ መልክ አለው።

በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ነው የሚያበድሩት፤ ያበድሩና እያሳደዱ ይቀበላሉ።

የሚያስከፍሉት ወለድ አናት ይፈልጣል፤ ኪስ ያራቁታል።ወሽመጥም ወገብም ይበጥሳል።

ለምሳሌ ለአንድ ሺህ ፓውንድ 400 ፓውንድ ወለድ ይጭናሉ። ከዚህ በላይ ጭካኔ ከየት አለ?

አንድም የማበደር ፍቃድ የላቸውም ታዲያ። በሕገ ወጥ ነው የሚሠሩት።

ካርዲፍ ክራውን የተባለው የዌልስና አካባቢዋ ፍርድ ቤት ሴትዮዋ 173ሺህ ፓውንድ እንዲከፍሉ ወስኖባቸዋል። ገንዘብ በጥሬው ከሌላቸው እንኳ ቤታቸውን ሽጠውም ቢሆን ይክፈሉ ሲል በቀጭኑ አዟል።

የርሳቸውን ዜና ተከትሎ በመላው ዩኬ በብድር የሚሰቃዩ ዜጎች ድምጽ በስፋት መሰማት ጀምሯል።

አራጣ አበዳሪዎችን ለማስቆም የሚሠራው ግብረ ሰናይ ድርጅት (Stop Loan Sharks Wales) እንዳለው የኚህን ሴትዮ ቅሌት ለአደባባይ ከበቃ በኋላ ድረሱልን የሚል ጩኸት ከሊቨርፑል እስከ ኖቲንጋም በርክቷል።

አራጣ አበዳሪዋን ይበልጥ ዝነኛ ያደረጋቸው ታዲያ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ያሉ ተበዳሪዎቻቸውን የሚያስፈራሩበት መንገድ ነው።

‘’ብድርህን ያልከፈልክ እንደሁ ንብረትንህን እቀማሃለሁ!’’ ይላሉ።

“እዘለዝልህ!” እያሉ አካላዊ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ያስፈራራሉ። አንዳንዴም "አሳግትሃለሁ" እንደሚሉ በምርመራ ተደርሶበታል።

ብዙዎቹ ተበዳሪዎች ከተመሳሳይ ማኅበረሰብ ክፍሎች (ኮሚኒቲስ) እንደሆኑ ተደርሶበታል።

በጭንቅ ላይ ያሉ የተበዳሪ ቤተሰቦች በጠቆሙት መሠረት ነው ይህ አራጣ አበዳሪዎችን በማደን የሚሠራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነገሩን የደረሰበት።

እኚህ የኒውፖርት፣ ዌልስ ነዋሪ ታዲያ ታሪካቸው ሲጠና ብዙ ጉድ አብሮ ተመዘዘ።

ታቢታ ሪቻርድሰን፣ በፊት አንድ ቡና ቤት (Pub) ነበራቸው። ከዚያ በኋላ ለአንድ ሕጋዊ የአበዳሪ ድርጅት መሥራት ጀመሩ።

በዚያ ድርጅት ውስጥ ለብዙ ዓመታት ከሠሩ በኋላ ቀጣሪ ድርጅቱ ሥራ ሲያቆም እርሳቸው በማበደሩ ገፉበት።

“እኔ ሄጄ ሳይሆን እነርሱ እየመጡብኝ ነው” የሚሉት ሴትዮዋ ለሠሩት ክፉ ሥራ ብዙም ጸጸት ሳይሰማቸው ቆይቷል።

ፍርድ ቤት ሁለት ዓመት በእግድ ገደብ እንዲታሠሩ ከወሰነ በኋላ ግን ቢቢሲ ሴትዮዋ ከፍርድ ቤት ሲወጡ ከደጅ ጠብቆ “ጸጸት ይሰማዎታል?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር።

“አዎና! እንዴት አይሰማኝ?” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤትም ይህን መጸጸታቸውን በማየት ነው እስሩን በገደብ ያደረገላቸው።

አራጣ አበዳሪዋ ታቢታ ሪቻርድሰን ይህን ተግባር ምናልባትም ለ20 ዓመታት ሳይሠሩት አልቀረም።

ታዲያ ተበዳሪዎቻቸው በብዙ ስቃይ አልፈዋል። አንዳንዶቹ ብድራቸውን ለመክፈል ከርሳቸው ድጋሚ ብድር ለመበደር ተገደዋል።

በዌልስ የምትገኝ ትንሽ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዌልስ የሚኖሩ ትንንሽ ማኅበረሰቦች ለአራጣ አብዳሪዎች የተጋለጡ ናቸው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሮጊቷ አበዳሪ ታዲያ የዋዛ አይደሉም። ብድሩ ሲዘገይ ማስፈራራትን ያውቁበታል።

አቃቢ ሕግ እንዳለው “የት እንዳለሽ አውቃለሁ መጣሁልሽ” እያሉ ያስፈራሩበት ጊዜ ነበር።

“መጥቼ ከማንቅህ መጥተህ ብትከፍል አይሻልም” የሚል የጽሑፍ መልእክትም ይልካሉ።

ተበዳሪዎቹ ታዲያ የወርሃዊ ገቢያቸው ትልቁ ወጪ ለኚህ አራጣ አበዳሪ መክፈል ስለሆነ ከብድር እሽክርክሪት ሳይወጡ ለዓመታት ተሰቃይተዋል።

የብድር አዙሪት ክፉ ነው። ነፍስ ያሸጣል። ብዙዎቹ በኚህ ሴትዮ አማካኝነት ሕይወታቸው ተመሰቃቅሏል።

የብድራቸው የወለድ ምጣኔ እስከ 40% የሚደርስበት አጋጣሚ አለ ሲባል ከዚህ አይበልጥም ማለት ግን አይደለም።

አንዳንድ ተበዳሪዎች ሲናገሩ ሴትዮዋን አይፈሯቸው ይሆናል። ነገር ግን የሚያውቁት ጉልበተኛ ባለሥልጣን ሳይኖር አይቀርም ብለው ይፈራሉ።

አንዳንዶቹ ተበዳሪዎች ገቢያቸው በሳምንት መቶ ፓውንድ አይሞላም። ከዚያቸው ታዲያ ለሴትዮዋ የሚከፍሉት ይበልጣል።

ሌሎች ደግሞ ምግብ የሚበሉት ሳይኖራቸው፣ በውርጭ ጊዜ ቤታቸውን ለማሞቅ እንኳ ሳይችሉ የሴትዮዋን ብድር ለመክፈል አፈር ድሜ በልተዋል።

ብዙዎቹ ተበዳሪዎች ባለ ትንንሽ ገቢ ይሁኑ እንጂ ሴትዮዋ እስከ 80ሺ ፓውንድ አበድረው ያውቃሉ።

አንድ ተበዳሪ 31ሺህ ፓውንድ ከርሳቸው መበደሩን አምኗል። ታዲያ ወለዱ ብቻ 12 ሺህ 400 ኖሮ። ይህንኑ ከፍሏል።

ሌላ ተበዳሪ ደግሞ 46ሺህ ተበድሮ ለዚህ በድምሩ 18ሺህ ፓውንድ ወለድ ከፍሏል።

አንድ ተበዳሪ ያሳለፈውን ሕይወት ሲገልጽ “የሴትዮዋን ብድር ለመክፈል ከርሳቸው ተጨማሪ ብድር መውሰድ ነበረብኝ።” ብሏል።

ሴትዮዋ በ20 ዓመት ከተበዳሪዎች ስቃይ ያጋበሱትን ገንዘብ አሁን እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።

በተለይ ስድስት ተበዳሪዎች 35ሺህ 285 ካሳ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳልፏል።

ይህን ገንዘብ ሴትዮዋ በሦስት ወር ካልከፈሉ፥ ዳኛው እንዳዘዙት፣ በዚህ ዕድሜ ዘብጥያ ይወርዳሉ።