ለ43 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩት የ80 ዓመቱ ፕሬዝዳንት በምርጫ ይወዳደራሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ለበርካታ ዓመታት በፕሬዝዳንትነት በሥልጣን ላይ በመቆየት በዓለም ላይ ቀዳሚው የሆኑት የኢኳቶሪያል ጊኒው መሪ በመንበራቸው ላይ ለመቆየት ዛሬ በሚደረገው ምርጫ ላይ ይሳተፋሉ።
እሁድ በሚደረገው የኢኳቶሪያል ጊኒ ምርጫ ለመሳተፍ ከ300,000 በላይ ሕዝብ በመራጭነት ተመዝግቧል።
የ80 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ንጉዌማ ምባሶንግ ኢኳቶሪያል ጊኒን ለ43 ዓመታት ቢመሩም አሁንም ሥልጣናቸውን መልቀቅ አልፈለጉም።
ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝዳንት ቴዎዶር፣ አገዛዛቸው በዜጎቻቸው ላይ ስቃይ መፈጸም እና ደብዛን ማጥፋትን ጨምሮ ተለያዩ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ይከሰሳል።
በሚደረገው ምርጫ የአንዳንድ ተቃዋሚዎች ዕጩዎች የሚሳተፉ ቢሆንም፣ ያሸንፋሉ ተብሎ ግን አይጠበቅም።
በነዳጅ ሃብቷ በበለጸገችው በኢኳቶሪያን ጊኒ የመንግሥት ሥልጣን ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ኃላፊነቶችን በቤተሰቦቻቸው የተቆጣጠሩት ፕሬዝዳንቱ፣ ለዓመታት በአገሪቱ ላይ ጠንካራ የበላይነትን ለመገንባት ችለዋል።
ዘናጩ የፕሬዝዳንቱ ልጅ ቴዎዶሮ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆን፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ቅንጡ ሕይወትን የሚመራ ነው። የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ከፍተኛ ዋጋ እንዳወጣ የሚነገረውን በውድ ማዕድናት የተንቀጠቆጠውን የማይክል ጃክሰንን የእጅ ጓንት መግዛቱን ይናገራሉ።
በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ለቢቢሲ የተናገሩት ፕሮፌሰር አና ሎሺያ ሳ “ምርጫው እንዲሁ ማስመሰያ ነው” ብለዋል።
“ምንም የሚለወጥ ነገር አይኖርም” የሚሉት በሊዝበን ዩኒቨርስቲ በአፍሪካ ፖለቲካ እና ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች ላይ ጥናት የሚያደርጉት ፕሮፌሰሯ “ኦቢያንግ ከ95 በመቶ በላይ ድምጽ አግኝተው እንደሚመረጡ እርግጥ ነው” ብለዋል።
እሁድ በሚደረገው ምርጫ ሕዝቡ መንግሥት የሚፈልገውን ድምጽ ይሰጣል የሚለው ደግሞ ማኅበረሰብ አንቂው ቱቱ አሊካንቴ ነው። “ተቃዋሚዎች ምንም ዕድል የላቸውም፣ ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ላለመልቀቅ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያደርጋሉ” ሲል ቱቱ ለሮይተርስ ገልጿል።
በአገሪቱ ውስጥ መንግሥት የፖለቲካዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዲደረግ አይፈቅድም፣ ነጻ ፕሬስ በአገሪቱ ውስጥ አይታወቅም፣ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን በመንግሥት ወይም በመንግሥት ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
ይህን ምርጫ ቀደም ሲል ስማቸው በበሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በምርጫ ማጭበርበር የጠፋው ፕሬዝዳንት ቲዎዶር ኦቢያንግ፣ ዝናቸውን ለማደስ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል። ባለፈው መስከረም መንግሥታቸው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አድናቆትን ያስገኘለትን የሞት ቅጣት እንዲቀር ማድረጉ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ በነዳጅ ሃብቷ ወደምትታወቀው አገር የመሪነት ሥልጣን የመጡት በአውሮፓውያኑ 1979 በተደረገ መፈንቅለ መንግሥት ነበር። ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ አንዳንድ ለውጦችን ቢያደርጉም አገሪቱንና ሃብቷን በሙሉ ቁጥጥራቸው ሥር አስገብተው ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከአርባ ዓመታት በላይ በሥልጣን እና በሃብት ውስጥ ሲቆዩ ተቃውሞዎች ሲገጥማቸው ነበር። በተጨማሪም ከበርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችም ተረፈዋል።
ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ አገሪቱን በፍጹማዊ ቁጥጥራቸው ስር አድርገው ለረጅም ጊዜ ለመምራት አመቺ ሁኔታን እንደፈጠሩ ፕሮፌሰር አና ሎሺያ ሳ ይናገራሉ። ለዚህም የአገሪቱ “የምርጫ ሕግ ቴዎዶር ኦቢያንግ ፈጽሞ እንዳይሸነፉ ለማድረግ ተብሎ የተቀረጸ ነው” ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 2002 በተደረገው ምርጫ ተቃዋሚዎች ሕገ ወጥ ድርጊቶችና ማጭበርበር ተፈጽሟል ብለው ከምርጫው እራሳቸውን ሲያገሉ፣ ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ 97 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ታወጇል። በ2009 እና በ2016 በተደረጉትም ምርጫዎች ተመሳሳይ ውጤት በማግኘት አሸንፈዋል።
የፕሬዝዳንት ኦቢያንግ አስተዳደር ከሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪ በሙስናም ይከሰሳል። ልጃቸው ቴዎዶሮ የሕዝብን ሃብት ለግላዊ ቅንጡ ኑሮ በመጠቀም በሚል የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ቅጣት ጥሎበት ነበር። በዚህም ፈረንሳይ ውስጥ ያሉ ንብረቶቹ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርጓል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ኦቢያንግም ሆነ ፕሬዝዳንት ሆኑት አባቱ የሚቀርብውን የሙስና ክስ ትክክል አይደለም ሲሉ አይቀበሉትም።
በዩናይትድ ኪንግደም የፀረ ሙስና ሕግ እገዳ የተጣለበት የኢኳቶሪያል ጊኒ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነው የፕሬዝዳንቱ ልጅ፣ የአባቱን ሥልጣን ይወርሳል ተብሎ ይጠበቃል።












