ኤሎን መስክ የዶናልድ ትራምፕን የትዊተር እገዳ አነሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አዲሱ የትዊተር ባለቤት ኤሎን መስክ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የትዊተር እገዳ እንዲነሳ አደረገ።
ትራምፕ ወደ ትዊተር እንዲመለሱ የተደረገው የሕዝብ አስተያየት ከተሰበሰበ በኋላ መሆኑን የተናገረው መስክ፣ የትዊተር ተጠቃሚዎች እርምጃውን ደግፈውታል ብሏል።
“ሕዝብ ወስኗል” በማለት በትዊተር ገጹ ላይ ያሰፈረው መስክ ከ15 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት የትዊተር ተጠቃሚዎች ውስጥ 51.8 በመቶ የሚሆኑት የትራምፕ እገዳ እንዲነሳ ድምጽ መስጠታቸውን አስታውቋል።
ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ወደ ማልበራዊ ሚዲያው ለመመለስ “ምንም ምክንያት አይታየኝም” ማለታቸው ወደ ትዊተር ላይመለሱ ይችላል የሚለው ጠቋሚ ነው ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የትዊተር ገጻቸው የታገደው ባለፈው ዓመት ሲሆን ይህም ግጭትን እና ሁከትን በማነሳሳት በሚል ነበር።
የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ካፒቶል ሂል ጥሰው ከገቡ ከቀናት በኋላ የትዊተር የቀድሞ አስተዳደር እርምጃ ወስዷል።
የአሜሪካ ኮንግረስ ጆ ባይደን በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ለማወጅ ሲሞክርም ነበር በመቶዎች የሚቆጠሩ የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሂልን ጥሰው በመግባት አመጽና ሁከት እንዲነሳ ያደረጉት።
ይህም ነውጥ ለአራት ሰላማዊ ሰዎች እና ለአንድ የፖሊስ አባል ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።
ሁከቱ ከተፈጠረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የዶናልድ ትራምፕ የፌስቡክ፣ የኢንስታግራም እና የዩቲዩብ አካውንቶች እንዲታገዱ ውሳኔ ተላልፏል።
ትራምፕ በእነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ድረገጾች በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ነበሯቸው።
ከበርካታ ወራት በኋላ ትራምፕ 'ትሩዝ ሶሻል' የተሰኘ የራሳቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ከፍተዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሪፐብሊካን ፓርቲው ፖለቲከኛ በአውሮፓውያኑ 2024 ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኤሎን መስክ ታዋቂውን የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረክ የሆነውን ትዊተርን የገዛው በ44 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ነው።
ትዊተርን ከተቆጣጠረ በኋላ ስር ነቀል ለውጦችን እያደረገ ያለው ኤሎን መስክ፣ የጥላቻ ንግግሮችና የተሳሳቱ መረጃዎች ላይ ያሉ የትዊተር መመሪያዎች ሊላሉ ይችላሉ የሚልም ስጋትን ፈጥሯል።












