ናሳ በዚህ አስር ዓመት ውስጥ ሰዎች ጨረቃ ላይ መኖር ይጀምራሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, NASA
በዚህ አስር ዓመት ውስጥ የሰው ልጅ በጨረቃ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት እንደሚችል የናሳ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ለተቋሙ የኦሪዮን የጨረቃ የጠፈር መንኮራኩር ፕሮግራምን በመምራት ላይ የሚገኙት ሃዋርድ ሁ፣ በጨረቃ ላይ የሚደረጉ ሳይንሳዊ ተልዕኮዎችን ለመደገፍ መኖሪያዎች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ 'ሰንደይ ዊዝ ላውራ ኩዌንስበርግ' ከተሰኘው የቢቢሲ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኦርዮንን የሚሸከመው የአርቴሚስ ሮኬት ረቡዕ ዕለት መወንጨፉ “ለሰዎች የጠፈር በረራ ታሪካዊ ዕለት ነው” ብለዋል።
ኦሪዮን በአሁኑ ወቅት ከጨረቃ በ134 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
100 ሜትር ከፍታ ያለው አርቴሚስ ሮኬት ከኬኒዲ የጠፈር ማዕከል የተወነጨፈው የጠፈር ተመራማሪዎችን ወደ ምድር ሳተላይት የመመለስ ተልዕኮን አንግቦ ነው።
ይህ ሮኬት ለመጀመሪያ ተልዕኮው ሰው ያልተሳፈረበት ሲሆን፣ ሰው የሚመስል አሻንጉሊት ተገጥሞለትም በረራው በሰው አካል ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ ይመዘግባል።
ረቡዕ የተደረገው የሮኬት ማስወንጨፍ ቢሳካም ከዚህ ቀደም በነሐሴ እና በመስከረም ላይ ሁለት ሙከራዎች በቴክኒክ ችግር ምክንያት መቋረጣቸው ይታወሳል።
ሃዋርድ ሁ የአርቴሚስ መወንጨፍ የማይታመን ስሜት እንደፈጠረባቸው እና ህልም እንደመሰላቸውም ተናግረዋል።
“የረዥም ጊዜ ጥልቅ የጠፈር ምርምር ለማድረግ የምንወስደው የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ይህ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ነው” ብለዋል።
አክለውም “ይህ ለናሳ ታሪካዊ ቀን ነው ብዬ አስባለሁ፤ ነገር ግን የሰው ልጅን የጠፈር በረራ እና ጥልቅ የጠፈር ምርምርን ለሚወዱ ሰዎች ሁሉ ታሪካዊ ቀን ነው” ብለዋል።
ሃዋርድ ይህንን ሲያስረዱ “ወደ ጨረቃ እየተመለስን ነው። ቀጣይነትና ዘላቂነት ያለው ፕሮግራም ነው እየሰራን ያለነው። ይህም መንኮራኩር ነው ሰዎችን ተሸክሞ ጨረቃ ላይ የሚያደርው” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የተደረገው የአርቴሚስ በራራ ስኬታማ ከሆነ የሚቀጥለው እርምጃም ሠራተኞችን ይዞ የሚወነጨፍ ሲሆን፣ በመጨረሻም ጠፈርተኞች ጨረቃ ላይ እንደሚያርፉ ተናግረዋል። ይህም ከሃምሳ ዓመት በፊት ከአፖሎ 17 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሆን አብራርተዋል።
አሁን ያለው ተልዕኮ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ሃዋርድ ሁ፣ ወደ ጨረቃ የመመለሱም ተስፋ ከፍተኛ ደስታ እንዳሳደረባቸው አሳውቀዋል።












