ለውበት በሚደረግ ቀዶ ሕክምና የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር በመጨመሩ ዩኬ እና ቱርክ ሊነጋገሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, NATASHA KERR
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለውበት ሲባል በቱርክ በሚደረግ የቀዶ ሕክምና የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር በመጨመሩ ከቱርክ መንግሥት ጋር ሊነጋገር ነው።
ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ዜጎች የመቀመጫ መጠን ከፍ ለማስደረግ በቱርክ ቀዶ ሕክምና ካደረጉ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።
ይህን ተከትሎ የዩኬ ባለሥልጣናት የሕክምና እና የኮስሞቲክስ (ውበት) ቀዶ ሕክምና ቱሪዝም መመሪያዎች እና ደንቦችን በተመለከተ ከቱርክ አቻዎቻቸው ጋር እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።
የ31 ዓመቷ ሜሊሳ ኬር እአአ 2019 ኢስታንቡል ከተማ በሚገኝ ሜዲካና ሃዝኔዳር በተባለ የግል ሆስፒታል የመቀመጫ መጠንን ከፍ ለማስደረግ ቀዶ ሕክምና ካደረገች በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
የሜሊሳ ኬር ሞትን የመረመረው የዩኬ መንግሥት አካል የ31 ዓመቷ ሴት ወደ ቱርክ አቅንታ የውበት ቀዶ ሕክማናውን ከማድረጓ በፊት ቀዶ ሕክምናው ሊያስከትለው ስለሚችለው ጉዳት በቂ መረጃ አልተሰጣም ብሏል።
የዩኬ የጤና ሚኒስትር ማሪያ ካውልፊልድ መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።
ካውልፊልድ የጤና ሚኒስቴር እና ማኅበራዊ አገልግሎት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ከቱርክ አቻዎቻቸው ጋር ለመምክር በቅርቡ ወደ ቱርክ ያመራሉ ብለዋል።
የሜሊሳ ኬር ሞትን የመረመረው አካል ለውበት ተብለው ከሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች በሙሉ የመቀመጫ መጠንን ከፍ ለማድረግ የሚደረገው አደገኛ ነው ያለ ሲሆን፤ ለወጣቷ ሞት ምክንያትም በቀዶ ሕክምና ወቅት የረጋ ደም ወደ ሳምባዋ በመግባቱ ነው ብሏል።
የዩኬ መንግሥት ዜጎቹ በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ለውበት ሲባል የሚደረግ የቀዶ ሕክምና ለማድረግ ከአገር ውጭ መጓዛቸውን ቀጥለዋል ይላል።
እአአ 2020 ላይ የሦስት ልጆች እናት የነበረች ሴት ስብ ከሰውነቷ ለማስመጠጥ ባመራችበት ቱርክ ሕይወቷ አልፏል። ከዚህ በተጨማሪም ክብደት ለመቀነስ ቀዶ ሕክምና ያደረጉ 7 እንግሊዛውያን በቱርክ ሕይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።
ሚኒስትሯ የአንዳንድ አገራት የጤና አሰጣጥ መመሪያ እና ደንብ ከዩናትድ ኪንግደም ደረጃ ጋር እንደማይስተካከል መንግሥት ያውቃል ያሉ ሲሆን፣ ወደፊት የታካሚዎችን ለአደጋ የመጋለጥ ዕድል ለመቀነስ “ግልጽነት ያለው አሰራር እና ደረጃ ማውጣት ያስፈልጋል” ብለዋል።
ሴቶች የመቀመጫቸውን መጠን ከፍ ለማድረግ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ከመወሰናቸው በፊት ሕክምናው ሊያስከትለው የሚችለው የጎንዮሽ ጉዳት በተመለከተ ሙሉ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
በተለይ ለውበት ተብለው ከሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች መካከል የመቀመጫ መጠንን ከፍ ለማድረግ ተብሎ የሚከናወነው ቀዶ ሕክምና 10 እጥፍ የሞት አደጋን ይደቅናል ብለዋል።












