ከኢትዮጵያ ግዙፍ ግድቦች አንዱ የሆነው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ለምን ዘገየ?

የኮይሻ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, SM

በኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወይም 57 ሚሊዮን ሕዝብ አሊያም ከአጠቃላይ ሕዝቡ 51 በመቶ የሚሆነው ምንም አይነት የኤሌክትሪክ አቅርቦት የለውም ይላል - የዓለም ባንክ መረጃ።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ባለፉት አስርት ዓመታት ከፍ እያለ ቢሄድም አገሪቱ ከሰሀራ በታች የኤሌክትሪክ እጥረት ካለባቸው አገራት በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

በአሁኑ ወቅት የሕዳሴ ግድብ ሁለት ዩኒቶችን ጨምሮ ኢትዮጵያ ካላት የኃይል ማመንጫዎች 5250 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ እንደምታመርት የኢትዮጵያ ኤሌክሪክ ኃይል ይገልጻል።

ይህንን ቁጥር በማሳደግ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለመጨመር በኢትዮጵያ አምስት የኃይል ማመንጫዎች እየተገነቡ ይገኛሉ።

ኮይሻ በግንባታ ላይ ካሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።

ስለኮይሻ ቁጥሮች ምን ይላሉ?

ከአዲስ አበባ በ540 ኪሎ ሜትር ርቆ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮይሻ ወረዳ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የኮይሻ ግድብ የኦሞ ወንዝን መሠረት አድርጓል። ይህ ግድብ ጊቤ ሦስት ከተገነባበት ስፍራ በ120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ከባሕር ጠለል በላይ 783 ሜትር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ 201 ሜትር ከፍታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሞገስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በየካቲት ወር 2008 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ኮይሻ 1800 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።

ግድቡ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ ባሻገር አሁንም ግንባታ ላይ ነው። ግንባታው እየሄደበት ያለው ፍጥነትም አዝጋሚ ነው።

“ከብድር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ፕሮጀክቱን በሚፈለገው መጠን እና ፍጥነት አላስኬዱትም” ይላሉ አቶ ሞገስ።

ስድስት ዩኒቶች የሚኖሩት የኮይሻ ግድብ 100 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና 6.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ የሚችል ማጠራቀሚያ (reservoir) ይኖረዋል።

እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፣ ይህ ግድብ አነስተኛ የውሃ ማጠራቀሚያ ያለው ቢሆንም ባለው ከፍታ ምክንያት ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት የሚችል ነው።

ግድቡ ቀደም ሲል 2100 ሜጋዋት እንደሚያመነጭ ተገልጾ ነበር። ይህም ኮይሻን ከሕዳሴ ግድብ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛው ከፍተኛ የኃይል ማመንጫ እንደሚያደርገው ተጠብቆ ነበር።

ሆኖም ግን ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል ቀድሞ ከታቀደው በ300 መቶ ሜጋዋት ቀንሷል። ይህም 1870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ካለው የጊቤ ሦስት ግድብ ጋር የተቀራረበ የኃይል ምርት እንዲኖረው ያደርገዋል።

ለመሆኑ የግድቡ የማመንጨት አቅም ለምን እንዲቀንስ ተደረገ?

“የሚያዋጣውን መምረጥ የተቋሙ [የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል] ድርሻ ነው የሚሆነው” የሚሉት አቶ ሞገስ፣ ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን እና ከፍታ ላይ “ምንም አይነት ለውጥ” ሳይደረግ ዩኒቶቹን መቀነስ ግድቡን “ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል” ሲሉ ያብራራሉ።

“ስለዚህ ተቋሙ በስድስትም በስምንትም ዩኒቶች ተመሳሳይ ዓመታዊ ኃይልን በአማካኝ የሚያገኝበት ሳይንሳዊ ምክንያት ካለው አስር ዩኒት መትከል አስፈላጊ አይደለም ማለት ነው” ሲሉም አክለዋል።

የኮይሻ ግድብ እውነታዎች

የኮይሻ የገንዘብ ምንጭ

አቶ ሞገስ ለቢቢሲ እንዳጋሩት መረጃ የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አሁን ላይ 61 በመቶ ደርሷል።

ግንባታው እዚህ ደረጃ ሲደርስ ሁለት የፋይናንስ ምንጮች አሉት።

የኮይሻ ጅማሮ ላይ ሳቼ የተባለ የጣልያን ባንክ ለግንባታው ብድር አቅርቧል።

ሆኖም ባንኩ “ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልገውን ብድር እንደሚያቀርብ ከተስማማ በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ ብድር ሰጥቶ ሌላውን በስምምነቱ መሠረት ማቅረብ አልቻለም” ሲሉ አቶ ሞገስ ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ ግንባታው ተስተጓጉሎ የነበረ ሲሆን፣ ግድቡ ከዘገየባቸው ምክንያቶች ቀዳሚው ተደርጎ ይጠቀሳል።

“በወቅቱ ሌላም አበዳሪ ሊገኝ ስላልቻለ መንግሥት በውጭ ምንዛሬ መከፈል የነበረበትን በመሸፈን ፕሮጀክቱ እንዲቀጥል አድርጓል” የሚሉት ኃላፊው ግንባታው ከመነሻው የገንዘብ ምንጩ ብድር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ወደ መንግሥት ካዝና መዞሩን ጠቅሰዋል።

ግድቡ ሲጀመር 2.4 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚፈጅ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ወጪው ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ይታመናል።

ወጪውን ሊጨምሩ ከሚችሉ ምክንያቶች አንዱ ግንባታው በተስተጓጎለበት ወቅት ተቋራጩ ያለሥራ የቆየበትን ካሳ በመጠየቁ ነው።

ግድቡ አሁን ባለው የፋይናንስ አቅርቦት ከቀጠለ ለመጠናቀቅ እስከ አራት ዓመታት እንደሚፈጅ የሚናገሩት አቶ ሞገስ፣ ሌላ የተሻለ የፋይናንስ መንገድ ከተገኘ ግን “ከዚህም ባጠረ ጊዜ” ሊጠናቀቅ ይችላል።

የኮይሻ ግድብ ሲጠናቀቅ ምን ጥቅም ያስገኛል?

አቶ ሞገስ የኮይሻ ግድብን ጥቅም የተቀራረበ ኃይል የማመንጨት አቅም ካለው ጊቤ ሦስት ጋር አነጻጽረው ይናገራሉ።

እንደ እሳቸው ገለጻ 2800 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም ያለው ጊቤ ሦስት ከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ በሚኖርበት ሰዓት እስከ 40 በመቶ የአገሪቱን የኃይል ፍጆታ ይሸፍናል። ከዚህ ውጪ ባለው ሰዓት ደግሞ እስከ 60 በመቶ ሊደርስ ይችላል።

ይህ ማለት ኮይሻ ከጊቤ ሦስት ጋር ተቀራራቢ የሆነ ኃይል ለአገሪቱ ማመንጨት ይችላል ማለት ነው የሚሉት አቶ ሞገስ፣ ግድቡ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ሽፋን በማሳደግ ከፍተኛ የሆነውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።

ህዳሴ ግድብና ኮይሻ

ሕዳሴ ግድብ እና ኮይሻ

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ኮይሻ በድምሩ 6950 ሜጋዋት ማመንጨት ይችላሉ። ይህ ቁጥር አሁን በአገሪቱ ያለውን የማምረት አቅም የሚበልጥ ነው።

ለንጽጽር ያህል የሁለቱን ግድብ ልዩነት እንመልከት፡

ከ12 ዓመታት በፊት የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ማጠራቀሚያ (reservoir) 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ የሚችል ነው።

ከዚህ ግድብ ግንባታ 5 ዓመታትን በኋላ የተጀመረው ኮይሻ ደግሞ ከሕዳሴው ግድብ 67.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያነሰ ውሃ ይይዛል። የኮይሻ ውሃ ማጠራቀሚያ 6.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን ያቁራል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጅማሮው ላይ 3.6 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚችል ይፋ ሆኖ ነበር። የኮይሻ ግድብ ደግሞ ሲጀመር 2.4 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚያስፈልግ ተገምቷል።

የሕዳሴ ግድብ 16 ተርባይኖች እንደሚኖሩት ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ 13 ዝቅ መደረጋቸው ተነሯል። የሚያመነጨው ኃይልም እንዲሁ መጀመሪያ ከታቀደው 6450 ሜጋ ዋት ወደ 5150 ዝቅ ብሏል።

በተመሳሳይ የኮይሻ ግድብ የሚያመነጨው ኃይል ከመጀመሪያው ዕቅድ በ300 መቶ ሜጋዋት ዝቅ ብሏል። ተርባይኖቹም ከ8 ወደ 6 ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል።

በኢትዮጵያ በግንባታ ላይ ያሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች

በኢትዮጵያ በግንባታ ላይ ያሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች

በኢትዮጵያ አምስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ሲሆን፣ የውኃ ኃይል ማመንጫዎች (ሃይድሮ ፓወር) ሰፊውን ቦታ ሲይዝ ከንፋስ እና ጂኦተርማል (እንፋሎት) ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችም ግንባታ ላይ ናቸው።

ከፕሮጀክቶቹ ቀዳሚው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሲሆን 5150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ግዙፉ ግድብ ነው።

ሌላኛው ከሰባት ዓመታት በፊት የተጀመረው ኮይሻ ነው። ኮይሻ 1800 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል በድምሩ ሁለት 220 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የመጀመሪያው በሶማሊ ክልል አይሻ ወረዳ እየተገነባ ያለው፣ የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ነው። አይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ሲጠናቀቅ 120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።

በኦሮሚያ ክልል አሰላ ውስጥ የሚገኘው የንፋስ ኃይል ማመንጫ 35 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም 100 ሜጋ ዋት ኃይልን ያመነጫል።

ሌላኛው የአሉቶ ጂኦቶርማል ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየተከናወነ ሲሆን በሁለት ዙር የሚገነባ እና 72 ሜጋ ዋት ኃይልን የሚያመነጭ ነው። በመጀመሪያ ዙር ግንባታውም 98 በመቶ ደርሷል።