ደቡብ አፍሪካ የእስራኤል ኤምባሲ እንዲዘጋ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ እንዲቋረጥ ወሰነች

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ

የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት በፕሪቶሪያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ እንዲዘጋ እና ከእስራኤል ጋር ያለ ሁሉም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲቋረጥ ወሰነ።

በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ስታሰማ የነበረችው የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ማክሰኞ ዕለት ባካሄደው ስብሰባ ነው።

በዚህም መሠረት የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የእስራኤል ኤምባሲ ለመዝጋት እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ድምጽ ሰጥቷል።

የፓርላማውን አብላጫ ወንበር የያዘው ገዢው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ አጥብቆ ሲተች ቆይቷል።

አገሪቱ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ እንዲያወጣም ጠይቃ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ትናንት ማክሰኞ በነበረው ውሎ እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ እስክትስማማ ድረስ ኤምባሲዋን ለመዝጋት እና ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማቋረጥ በ248 ድጋፍ እና በ91 ተቃውሞ ወስኗል።

አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት “ፍልሰጤም ነጻ ትውጣ” ሲሉ በምክር ቤቱ ውስጥ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲናገሩ ተሰምተዋል።

ለፍልስጤማውያን ያላትን ድጋፍ ጠንከር ባሉ አቋማ ስታንጸባርቅ የቆየችው ደቡብ አፍሪካ የእስራኤልን የጋዛ ዘመቻ “የጅምላ ቅጣት” ስትል ትተቻለች።

ከደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ጋር ግንኙነቷ የጠለሻባት እስራኤልም ተቀማጭነታቸውን ፕሪቶሪያ አድርገው የነበሩት አምባሳደሯን ወደ ቴል አቪቭ ጠርታለች።

ደቡብ አፍሪካ የሐማስን ጥቃት ተከትሎ አስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደችው ባለውን ከባድ ወታደራዊ ጥቃት በጥብቅ ከተቃወሙ አገራት መካከል ዋነኛዋ ናት።

ደቡብ አፍሪካ ትናንት ሰኞ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ እንዲያወጣ መጠየቋ ይታወቃል።

ከሁምቡዝዶ ናትሻቨሄኒ የተባሉ የደቡብ አፍሪካ ሚኒስትር ፍርድ ቤቱ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ኔታኒያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ የማይቆረጥ ከሆነ “ዓለም አቀፋዊ የአስተዳደር ውድቀት መኖሩን ያመላክታል” ብለዋል።

በዚህ እና ደቡብ አፍሪካ በተለያዩ መድረኮች በአስራኤል ላይ እያሰማችው ባለው ጠንካራ ውግዘት የተነሳ አስራኤል ለምክክር በሚል አምባሳደሯን ከፕሪቶሪያ ጠርታለች።

መስከረም ወር ማብቂያ ላይ በተጀመረው ጦርነት ሐመስ ከ1200 በላይ ሰዎችን አስራኤል ውስጥ በመግደል ከ220 የሚበልጡትን ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ባለው ያልተቋረጠ ጥቃት ከ13 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።