'ሞተዋል' ተብሎ ሊቀበሩ የነበሩት አዛውንት ሬሳ ሳጥን ውስጥ በሕይወት ተገኙ

አዛውንቷ የነበሩበት የሬሳ ሳጥን

የፎቶው ባለመብት, Philippe Lissac/ Godong

ኢኳዶራዊቷ የ76 ዓመት ቤላ ሞንቶያ ሞተዋል ተብሎ ሊቀበሩ ሲሉ እስትንፋሳቸውን አሰምተዋል።

አዛውንቷ የሬሳ ሳጥን ውስጥ ተከተው ሥርዓተ ቀብራቸው ሊፈጸም ሲል ነው በሕይወት እንዳሉ የታወቀው።

ባለፈው ሳምንት በስትሮክ ምክንያት መሞታቸው ተገልጾ ነበር።

በለቅሶው ላይ የነበሩ ሰዎች ቤላ አለመሞታቸውን ሲመለከቱ ተደንቀዋል።

ዘመዶቻቸው ልብሳቸውን ቀይረው ለግብዓተ መሬት እያዘጋጇቸው ነበር። እስትንፋሳቸውን ከሰሙ በኋላ ወደ ሆስፒታል ወስደዋቸዋል።

አሁን በጽኑ ሕሙማን ማቆያ ነው የሚገኙት።

የኢኳዶር ጤና ሚኒስትር ጉዳዩን የሚመረምር ኮሚቴ አዋቅሯል።

ድንገተኛ የልብ መቆምና ትንፋሽ መቋረጥ (cardiorespiratory arrest) ገጥሟቸው ስለነበር ሐኪሞች ሞተዋል ብለው እንደደመደሙ ተገልጿል።

ልጃቸው ጊልበር ሮዶልፎ ባልባርን ሞንቶያ እንደተናገረው እናቱ ሆስፒታል ረፋድ ገብተው ቀትር ላይ መሞታቸው ተገልጾለታል።

ከዚያም ሬሳ ሳጥን ውስጥ ገብተዋል። ከሰዓታት በኋላ ግን ለመተንፈስ ሲጣጣሩ ቤተሰቦቻቸው ተመልክተዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሬሳ ሳጥን ውስጥ ሳሉ ለመተንፈስ ሲሞክሩና በሰዎች ተከበው ያሳያል።

የሕክምና ባለሙያዎች በቦታው ደርሰው አዛውንቷም በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ወስደዋል።

ሞተዋል በተባሉበት ሆስፒታል ውስጥ በጽኑ ሕሙማን ማቆያ ይገኛሉ።

ኤኤፍፒ ልጃቸውን ጠቅሶ እንደዘገበው “ቀስ በቀስ የተፈጠረውን ለመረዳት እየሞከርኩ ነው። የእናቴ ጤና እንዲመለስ እየጸለይኩ ነው። በሕይወት ከጎኔ እንድትቆይ እፈልጋለሁ” ብሏል።