በስዊድን ቁርዓን ያቃጠለው ግለሰብ በጥይት ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በስዊድን ቁርዓን በማቃጠሉ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳው ግለሰብ በጥይት ተመትቶ መገደሉን የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የ38 ዓመቱ ሳልዋን ሞሚካ ረቡዕ ማምሻውን፣ ጥር 21/ 2017 ዓ.ም በስቶክሆልም በሚገኝ አንድ አፓርታማ ውስጥ መገደሉ ተዘግቧል።
ሳልዋን የእስልምና እምነት ቅዱስ መጽሃፍ የሆነውን ቁርዓንን በስቶክሆልም በሚገኝ መስጊድ ውጭ ከሁለት ዓመት በፊት ማቃጠሉን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ ተፈጥሮ ነበር።
የስቶክሆልም ፖሊስ ባወጣው መግለጫ በ40ዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ግለሰብ ሌሊት በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ተከትሎ አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
ሳልዋን በተተኮሰበት ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቀጥታ አንድ ፕሮግራም እያስተላለፈ እንደነበር የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በስዊድን ነዋሪ የነበረው ኢራቃዊው ሳልዋን ከሁለት ዓመት በፊት "በአንድ ቡድን ላይ ትንኮሳ" በማነሳሳት አራት ጊዜ ክስ ቀርቦበት ነበር።
የስቶክሆልም ግዛት ፍርድ ቤት ሐሙስ ሊሰጥ የነበረው ብይን "ከተከሳሾቹ አንዱ [ሳልዋን ሞሚካ] መሞቱ በመረጋገጡ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል" ተብሏል።
ሳልዋን ተከታታይ ጸረ እስልምና ተቃውሞዎችን በማካሄድ በበርካታ ሙስሊም አገራት ቁጣ ቀስቅሷል።
በኢራቅ መዲና ባግዳድ በሚገኘው ስዊድን ኤምባሲ ሁለት ጊዜ ሁከት ተፈጥሯል። ይህንንም ተከትሎ በተነሳው ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ አምባሳደሩ ከሃገሪቱ ተባረዋል።
የስዊድን መንግሥት ሳልዋን ቁርዓንን ያቀጠለበት ተቃውሞ የአገሪቱ በነጻ የመናገር ህጎችን መሰረት ያደረገ ነው በሚል ፈቃድ ሰጥቷል።
ሆኖም የተነሳውን ቁጣና ተቃውሞ ተከትሎ መጽሃፎችን ማቃጠልን የሚያካትቱ ተቃውሞዎችን ለማስወገድ ህጋዊ መንገዶችን ለማየት መንግሥት ቃል ገብቶ ነበር።












