በኢኳዶር በሚገኝ ማረሚያ ቤት በርካታ እስረኞች ተሰቅለው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, LUIS SUAREZ/AFP via Getty Images
በደቡብ ኢኳዶር በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ቢያንስ 31 ታራሚዎች ሞተው ተገኙ። ከታራሚዎቹ መካከል 27 የሚሆኑት ተሰቅለው እንደተገኙ ተገልጿል።
በማቻላ ከተማ፣ ኤል ኦሮ በተባለው ማረሚያ ቤት ውስጥ ትናንት በሁለት ተቀናቃኝ የወንጀል ቡድኖች መካከል በተነሳ ጸብ ምክንያት አራት እስረኞች ሲገደሉ ከ30 በላይ የሚሆኑ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጸቡ በተነሳ በሰዓታት ውስጥ በድጋሚ ሌላ ግጭት ተነስቶ 27 እስረኞች ተሰቅለው ተገኝተዋል።
በፀጥታ ኃይሎች አስከሬናቸው የተገኘው ታራሚዎች በሦስተኛው የእስር ቤቱ ወለል እንደተገኙ ተገልጿል።
በኢኳዶር ማረሚያ ቤቶች የሚነሱ ተቃውሞዎች እና ነውጦች እየተባባሱ የመጡ ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት በወንጀል ቡድኖች መካከል በሚነሳ ጸብ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ተገድለዋል።
ከታራሚዎቹ መካከል የተወሰኑት በቅርቡ ወደተገነባ እስር ቤት እንደሚወሰዱ ከተገለጸ በኋላ በወንጀል ቡድኖች መካከል ግጭቶች መነሳት እንደጀመሩ የአገሪቱ የማረሚያ ቤት አስተዳደር አስታውቋል።
በኤል ኦሮ ማረሚያ ቤት ያለፈው መስከረም አጋማሽ ላይ በወንጀል ቡድኖች መካከል በተነሳ ግጭት ምክንያት እስረኞች እና የማረሚያ ቤት ጠባቂ ተገድለዋል።
የታራሚዎች ቤተሰቦች የእስር ቤቱ ጥበቃ እንዲጠናከር አሳስበዋል። ማረሚያ ቤቱ የሚገኝበት ማቻላ ከተማ ነዋሪዎችም ማረሚያ ቤቱ ከከተማው እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የፕሬዝዳንት ዳንኤል ኖቦአ መንግሥት እአአ በ2025 መባቻ ላይ እንዳስታወቀው፤ ሳንታ ኤሊና በተባለ ከተማ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት ማረሚያ ቤት ተገንብቷል።
ኤል ኢንኩናትሮ የተባለው አዲስ እስር ቤት በዚህ ወር መጨረሻ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
የወንጀል ቡድኖች በኢኳዶር ማረሚያ ቤት ለሚነሱ ነውጦች ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው። በዋነኛነት ሎስ ሎቦስ እና ሎስ ቾነሮስ ቡድኖች በአሜሪካ አሸባሪ ተብለው ተፈርጀዋል።















