የብሪታኒያ ፖሊስ በስህተት የተለቀቁ ሁለት እስረኞችን እያደነ ነው

በስህተት ከእስር የተለቀቁት ራሂም ካዶር ሸሪፍ እና ዊሊያም ስሚዝ

የፎቶው ባለመብት, Met Police

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ በስህተት የተለቀቁትን የ24 ዓመት እና የ35 ዓመት እስረኞች ምስል ይፋ አድርጓል

የብሪታኒያ ፖሊስ ባለፈው ሳምንት በስህተት የተለቀቁ ሁለት እስረኞችን እየፈለገ ነው።

በወሲባዊ ጥቃት ጥፋተኛ የተባለው አልጀሪያዊ ብራሂም ካዶር ሸሪፍ እና በማጭበርበር ወንጀል የታሰረ ዊሊያም ስሚዝ በቀናት ልዩነት ከዊንድወርዝ እስር ቤት በስህተት ተለቅቀዋል።

የእስረኞቹ በስህተት መለቀቅ ዜና የተሰማው ኢትዮጵያዊው የወሲባዊ ጥቃት ወንጀለኛ ሀዱሽ ገ/ሥላሴ ቅባቱ ከኤሴክስ እስር ቤት በስህተት ከተለቀቀ ከሳምንታት በኋላ ነው።

የሀዱሽ በስህተት መለቀቅን ተከትሎ ተመሳሳይ ስክተቶች እንዳይፈጠሩ ተጨማሪ የፍተሻ ስርዓት እንደሚዘረጉ ቃል የገቡት የፍትህ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተዋል።

በምክር ቤት የቀረቡት ሚኒስትሩ ከሀዱሽ በኋላ ከእስር ቤት በስህተት የተለቀቁ ጥገኛ ጠያቂዎች አሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የምክር ቤት ውሎው ሲጠናቀቅ ፖሊስ ስደተኛ የሆነ የ24 ዓመቱ ብራሂም ካዶር ሸሪፍ ባለፈው ረቡዕ በስህተት እንደተለቀቀ አስታውቋል።

እስረኛው በ2019 በሕጋዊ መንገድ በጎብኝዎች ቪዛ ዩናይትድ ኪንግደም ገብቶ ከተፈቀደለት የቪዛ ጊዜ በላይ መቆየቱ ታውቋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ላሚ በኋላ ላይ ባወጡት መግለጫ በሁኔታው መበሳጨታቸውን ገልፀው፤ "ተጎጂዎች ከዚህ በላይ ይገባቸዋል፤ ሕዝቡ መልስ ያስፈልገዋል" ብለዋል።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መንግሥት የውጭ አገር ወንጀለኞችን በስህተት ከእስር ቤት መልቀቁ እንዳስደነገጣቸው እና የመንግሥትን ደካማነት የሚያሳይ ነው በሚል እየወቀሱ ነው።

የገዢው ሌበር ፓርቲ የምክር ቤት አባል እና የምክር ቤቱ የፍትኅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አንድሪው ስላውተር የማረሚያ ቤት ስርዓቱ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት እና ከአቅም በላይ መጨናነቅ እና በሠራተኞች እጥረት አለመረጋጋት እና ቀውስ እንደገጠመው ተናግረዋል።

የአገሪቱ ፖሊስ የአልጀሪያዊው እስረኛ በስህተት መለቀቁን ባሳወቀ በሰዓታት ውስጥ ዊሊያም ስሚዝ የተባለ ሌላ እስረኛም በስህተት መለቀቁን ይፋ አድርጓል።

"በበርካታ የማጭበርበር ወንጀሎች" 45 ወራት እስር ሰኞ ዕለት የተፈረደበት እስረኛው በተመሳሳይ ቀን ከእስር መለቀቁን ፖሊስ አስታውቋል።

ቢቢሲ ዊሊያም ስሚዝ በፍርድ ቤት የብይን ትዕዛስ መሰጠት ሲኖርበት በሰነድ ስህተት የምህረት ትዕዛዝ በመሰጠቱ ከእስር ቤት እንደለቀቀ ለመገንዘብ ችሏል።

ፍርድ ቤት በኋላ ላይ ስህተቱን ቢያርምም የተስተካከለው ትዕዛዝ ለተሳሳተ ሰው መላኩ ታውቋል።

ፖሊስ እስረኞችን ለመያዝ ማኅበረሰቡ መረጃ እንዲሰጠው ጠይቋል።

እስከ መጋቢት 2025 ባለው አንድ ዓመት በእንግሊዝ እና ዌልስ 262 የሚሆኑ እስረኛዎች በስህተት ተለቀዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፃፀር 128 በመቶ ጭማሪ እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ።

እስረኞቹ በስህተት የተለቀቁበት ዊንድወርዝ እስር ቤት ባልደረቦች በድንጋጤ ውስጥ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በ2023 ዳንኤል ካሊፍ የተባለ ለኢራን በመሰለል የተጠረጠረ ግለሰብ ከእስር ቤቱ አምልጧል።