"ሰይጣን አምላኪዎች ልጄን በማኅበራዊ ሚዲያ አጠመዷት፤ እንዳላድናት አቅመቢስ ሆንኩ"

ስልክ የያዘች ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው።

የ14 ዓመቷ ታዳጊ ከዕድሜ እኩዮቿ ጋር በበይነ መረብ ስታወራ እናቷ እምብዛም አላሳሰባትም ነበር። ከሳምንታት በኋላ ግን የታዳጊዋ ባህሪ ተለወጠ።

ለዚህ ጽሑፍ ስንል ክርስቲና የምንላት እናት ጭንቅ ውስጥ ገባች።

ልጇ '764' የተባለ ቀኝ ዘመም ሰይጣን አምላኪ ቡድንን ነበር የተቀላቀለችው።

ቡድኑ ታዳጊ ሴቶችን መጉዳት የሚፈልጉ ወጣት እና አዋቂ ወንዶችን በዋናነት ይዟል።

በዩናይትድ ኪንግደም ከዚህ ቡድን ጋር ትስስር አላቸው በሚል አራት ታዳጊዎች ተይዘዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ ምዕራብ ሰሴክስ የሚኖረው ካሜሩን ፊንገን የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

አካላቸው ላይ ጉዳት ማድረስ የሚፈልጎ ሰዎች በበይነ መረብ ሲነጋገሩ የክርስቲና ልጅም ተቀላቀለቻቸው።

ከዚያም ወደ 764 ቡድን እንድትገባ ተመለመለች።

የቡድኑ አባላት ወሲባዊ ድርጊት እንዲፈጽሙ፣ ራሳቸውን እንዲጎዱ ወይም ራሳቸውን ለማጥፋት እንዲሞክሩ ይገደዳሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ አባላት በቀጥታ ቪድዮ ይመለከታሉ።

እናት ክርስቲና እንደምትለው አንድ የዚህ ቡድን አባል ልጇን አሳምኖ የቡድኑ አባል አድርጓታል።

"እናቴ በደረጃ አራት ካንሰር ምክንያት ስትሰቃይ አይቻለሁ። ልጄ የዚህ ቡድን አባል ስትሆን ያዘንኩትን ያህል የጎዳኝ ነገር ግን የለም" ትላለች።

"በካንሰር የተያዘ ሰው እየተንገላታ ከሚሞተው በባሰ ልጄ ትሰቃይ ነበር።"

ነገር ግን ልጇን 764 ከተባለው ሰይጣን አምላኪ አደገኛ ቡድን ለማስወጣት መሞከር ቀላል አልነበረም።

የሰይጣን አምልኮ ምልክት

ልጇ ሰይጣን አምላኪዎቹን 'ብሎክ' እንድታደርጋቸው ወይም ማዋራት እንድታቆም እናት መወትወት አላቆመችም። ሆኖም ልጇን ማሳመን ቀላል አልሆነም።

አጠቃላይ እንቅስቃሴዋን ከዚህ ቡድን ጋር ፍጹም በማቆራኘት "እነሱ በሕይወቷ ከሌሉ ማንም እና ምንም እንዳልሆነች እንዲሰማት አድርገው ነበር" ትላለች።

ከዚህ አደገኛ ቡድን ልጇን ለማላቀቅ ብዙ ጥረት እና ድካም በኋላ በስተመጨረሻ ተሳክቶላታል።

ክርስቲና እና ልጇ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሕይወታቸው ለመመለስ እየሞከሩ ነው። ቀስ በቀስ ሕይወታቸውን ዳግመኛ እየገነቡ ይገኛሉ።

"ልጄ መመገብ እና መተኛት አቁማ ነበር። እንደ እናት ብቻዬን እንደሆንኩ ተሰማኝ። አቅመ ቢስነት እና ተስፋ ቢስነት ተሰማኝ" ስትል ያሳለፈችውን ጊዜ ታስታውሳለች።

የዩኬ ብሔራዊ የወንጀል ምርመራ ተቋም እንደ 764 ያሉ ቡድኖችን "በበይነ መረብ ዓለም ያሉ ከፍተኛ ስጋቶች" ሲል ይገልጻቸዋል።

የሰይጣን አምልኮ ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Counter Terrorism Policing South East

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በበይነ መረብ ሕጻናት ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት መርማሪ የሆኑት ሮብ ሪቻርድሰን እንደሚሉት፤ እነዚህ ቡድኖች ታዳጊዎችን ያጠምዳሉ። የሚፈጽሙት ወንጀልም በቂ ትኩረት አልተሰጠውም።

"ተጎጂዎቹን ማናገር ቀላል አይደለም። ተጎጂ መሆናቸውንም አያምኑም። በተለይ ሴት ታዳጊዎች ተጋላጭ ናቸው" ይላሉ።

ኢንተርኔት እና ማኅበራዊ ሚዲያ በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ወላጆች ልጆቻቸው በይነ መረብ ላይ ምን እንደሚያደርጉ እንዲሁም ከእነ ማን ጋር እንደሚገናኙ መከታተል እንዳለባቸው መርማሪው ይመክራሉ።

ለዚህም የልጆችን በይነ መረብ የሚያስሷቸውን ነገሮች መገደብ እና ቁጥጥር ማድረግ የሚቻልባቸውም መንገዶች አሉ።

የ14 ዓመቷ ሞሊ ረሰል በማኅበራዊ ሚዲያ የሚረብሽ ይዘት ከተመለከተች በኋላ ራሷን አጥፍታለች። በሞሊ ስም የተቋቋመው 'ሞሊ ሮስ ፋውንዴሽን' መሥራች አንዲ በሮውስ፤ 764 የተባለው ቡድን እየተስፋፋ መምጣቱ ያሰጋቸዋል።

ይህ ቡድን "በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው። ልጆች በሚጠቀሙባቸው ማኅበራዊ ገጾች ላይ በግልጽ ነው የሚንቀሳቀሱት" ይላሉ።

በታዳጊዎች ዘንድ ለሚፈጸም ራስን ማጥፋት እና አካልን መጉዳት በዋናነት ተጠያቂ እነዚህ ቡድኖች መሆናቸውን ያስረዳሉ።

764 የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2020 ነው። አሜሪካዊው ብራድሊ ካድንሄድ በ15 ዓመቱ ነበር ቡድኑን የጀመረው።

ይህ የሰይጣን አምላኪ ስብስብ መለያው ያደረገው የቴክሳስ ግዛት የፖስታ አድራሻ ቁጥርን እንደሆነ ይታመናል።

ዓለም አቀፍ ንቅናቄ የሚያደርጉ ቀኝ ዘመም ቡድኖች ቅጥያ መሆኑን ፖሊስ ይገልጻል። "መሣሪያ መታጠቅን የሚያበረታታ" ሲል ፖሊስ ይገልጻቸዋል።

ካሜሩን ፊንገን ቡድኑን የተቀላቀለው በ18 ዓመቱ ነበር። በፖሊስ ከተያዘ በኋላ በሰጠው ቃል "ቡድኑ ጥቁሮችን እና የአእምሮ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ይበዘብዛል" ብሏል።

ራስን ማጥፋትን በማበረታታት፣ የሽብር ጥቃት ለማድረስ የሚውል ጽሑፍ በማጋራት እና የሕጻናትን እርቃን ምሥል በመለጠፍ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

በፈጸመው ወንጀል ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ እስራት ሲፈረድበት ዐቃቤ ሕግ "ለማኅበረሰብ ትልቅ አደጋ ነው" ብሎ ነበር።

የዩናይትድ ኪንግደም የፀረ ሽብር ተቋም እነዚህ ቡድኖች "ከፍተኛ ስጋት ናቸው" ብሏል።

ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የፀረ ሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።

የተቋሙ ኃላፊ መርማሪ ፖሊስ ክሌር ፊንሊ "የካሜሩን ፊንገን መታሰር እነዚህን ቡድኖች በቅርበት ለመከታተል በር ከፍቷል" ይላሉ።

ወላጆች ልጆቻቸው ላይ የተጋረጠውን አደጋ እንዲረዱ ማድረግ አንዱ የንቅናቄው አካል ነው።

"ታዳጊዎች ምን ውስጥ እየገቡ እንደሆነ እንዲከታተሉ ማድረግ አንዱ ሥራችን ነው" ይላሉ።

አምና የአሜሪካ የአገር ውስጥ የወንጀል መርማሪ ተቋም ኤፍቢአይ 764 ቡድን የተለያዩ ወንጀሎችን በሰለባዎቹ ላይ እንደሚፈጽም ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

ከእነዚህም ውስጥ ቡድኑ "በማስፈራራት እና በማጭበርበር ሰዎች ራሳቸውን ሲጎዱ ወይም ራሳቸውን ሲያጠፉ አልያም ወሲብ ሲፈጽሙ በቀጥታ እንዲያሳዩ ያደርጋሉ" ብሏል።

ኤፍቢአይ ከዚህ ቡድን ጋር ትስስር አላቸው የተባሉ 250 ግለሰቦች ላይ ምርመራ ከፍቷል።

ከዚህ ቡድን ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሕጻናትን በመበዝበዝ፣ በእገታ እና በግድያ በስምንት አገራት ተከስሰዋል።

የካሜሩን ፊንገንን ጉዳይ የመረመሩት ፖሊስ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ታዳጊዎች አስከፊ ወንጀል እንዲፈጽሙ በቡድኑ ይገደዳሉ" ብለዋል።

"ሰዎችን በመበዝበዝ ወይም የውሸት ቦምብ ሊፈነዳ ነው ብለው ስጋት ይፈጥራሉ፣ ለመዝናናት ብለው 764 ቡድንን የተቀላቀሉ ሰዎች በስተመጨሻ ወደ አክራሪነት ተለውጠዋል" ሲሉም አክለዋል።