በአሜሪካ እየተስፋፋ የመጣው በይፋ ሰይጣንን ‘የማምለክ’ እንቅስቃሴ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ ቦስተን የሚገኝ ማሪዮት ሆቴል ውስጥ ሰይጣን አምላኪዎች ተሰብስበዋል።
በእንግሊዝኛው ‘ሳታኒስትስ’ በመባል ነው የሚታወቁት።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተከታዮች በአንድ ቦታ ሲሰበሰቡ ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
የሚጠብቁት መሰናዶ ሊጀመር ጥቂት ቀርቷል። ክፍሉ በሻማ ደምቋል።
የሰይጣን አምልኮ ሥነ ሥርዓት ማከናወኛዎች በቅርብ ርቀት ይታያሉ። ‘ትንሹ ጥቁር መድረክ’ የሚል ጽሑፍ ተሰቅሏል።
ዘለግ ያለ ሻማ ማብሪያ በአንድ በኩል ተቀምጧል። ፊት ለፊቱ አምስት ጎን ያለው የኮከብ ቅርጽ መሬት ላይ ይገኛል።
እየተካሄደ ያለው ሥነ ሥርዓት ሰዎች በሕጻንነታቸው የተካሄደ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን የሚጻረር ነው።
የሚታወቀው ‘unbaptism’ በመባል ነው። ‘ፀረ ጥምቀት’ በሚል ሊተረጎም ይችላል።
ቢቢሲ እዚህ መሰናዶ ላይ እንዲገኝ የፈቀደው ሰይጣን አምላኪ “ስም አንሻም” ሲል ይደመጣል።
ማንነታቸውን ይፋ የማይደረግ ከሆነ ነው ዝግጅቱ ላይ ለመታደም የፈቀደው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስከ መሬት የሚደርስ ሽፍን ልብስ ይለብሳሉ። ጥቁር የፊት መሸፈኛም ያጠልቃሉ።
እጃቸው በገመድ ታስሯል። ከዚያም ነጻነትን በሚወክል ሁኔታ ገመዱ ይፈታላቸዋል።
በክርስትና የተሰጣቸውን ጥምቀት በሚነቅፍ ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾችን ይቀዳሉ።
ይህን ማድረግ አንዳች ከፍታ እንደሚሰጣቸው ያስባሉ።
ከመካከላቸው አንዱ “ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ስትሆን ሐጢአተኛ እንደሆንክ፣ መጥፋት እንዳለብህ ይነገርሃል። ወደ ሰይጣን አምልኮ ስፍራ ከመጣሁ በኋላ ምክንያታዊነት እና ሐዘኔታ ምን እንደሆኑ ገብቶኛል” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK
‘ዘ ሳታኒክ ቴምፕል’ (The Satanic Temple) በመባል የሚታወቀው የአምልኮ ስፍራ በአሜሪካ መንግሥት ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን፣ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አውስትራሊያ የእምነት መሪዎች እና ተከታዮች አሉት።
‘የሰይጣን ኮንፈረንስ’ (SatanCon) የሚል ስያሜ የተሰጠው ጉባኤ ላይ ከ830 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል።
አባላቱ እንደሚሉት፣ በዲያብሎስ ወይም ገሀነም አያምኑም። ሰይጣን የሚለው ቃል የሚወክለው ሥልጣንን መጋፈጥን እንዲሁም በሳይንስ ማመንን ነው ይላሉ።
በዚህ አስተሳሰብ የጋራ እምነት ያላቸው ሰዎች ሲሰባሰቡ ሃይማኖት ይባላል ይላሉ።
ሃይማኖታዊ ክንውን ሲያደርጉ የሚጠቀሙት የሰይጣን ምልክቶችን ነው።
ለምሳሌ ሠርግ ሲካሄድ ወይም አዲስ ስም ሲወጣ የተገለበጠ መስቀል ይዘው ‘ሰይጣን ይመስገን’ ይላሉ።
ይህ ክርስትና እምነት ተከታዮች ክህደት ነው።
የአምልኮ ስፍራው ቃል አቀባይ ዴክስ ዴስጃርዲንስ “ይህ ስህተት አይደለም” ይላል።
“አብዛኛው የምንጠቀምበት ምልክት ክህደት ነው” ሲል ያስረዳል።

“የተገለበጠ መስቀል የሚያደርጉ አባላት አሉን። መክፈቻ ሥነ ሥርዓታትን መጽሐፍ ቅዱስ መቀዳደድ ነው። ይህ የሚወክለው ጭቆናን በተለይም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን፣ ሴቶችን፣ ጥቁሮችን፣ ቀደምት ማኅበረሰቦችን ጭቆና ነው። ማንኛውም በሃይማኖት ምክንያት የደረሰ ጠባሳ ያለባቸውን ሰዎች ጭቆና ይወክላል። እነዚህ ደግሞ አብዛኞቹ አባሎቻችን ናቸው” ይላል።
ሁሉም ሰው እምነቱን የመምረጥ መብት እንዳለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ሰዎችን ማስቆጣት እንደማይፈልጉም ይገልጻሉ።
ተከታዮቹ የተሰበሰቡበት ሆቴል ፊት ለፊት የተለያዩ የክርስትና ዕምነት ቅርንጫፎች አማኝ የሆኑ ሰዎች ተቃውሞ አሰምተዋል።
እርግማን እና ድርጊቱን የሚያወግዙ መፈክሮችም ይዘዋል።
“ተጸጸቱና መጽሐፍ ቅዱስን እመኑ” ይላል አንደኛው መፈክር። “የፕራይድን ልጆች ሰይጣን ይገዛቸዋል” ይላል ሌላኛው።
ፕራይድ (Pride) የሚለው ቃል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብታቸውን ለማስከበር የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ መፈክሩ ላይ ቃሉ የተጻፈው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መለያ በሆነው በቀስተ ደመና ቀለም ነው።
ከተቃዋሚዎቹ አንዱ ማይክል ሺብለር ወግ አጥባቂ ካቶሊክ ነው። “ይህን ክህደት እንደምናወገዝ እግዚአብሔር እንዲያይ ነው የወጣነው። የሕዝብ አደባባይን ለሰይጣን አምላኪዎች እንዳልተውነው ማሳየትም እንፈልጋለን” ይላል።

ተከታዮቹ ተቃዋሚዎቹን በአንክሮ ይመለከታሉ።
“ዕፅ የሚያጨሱ ግለ-ወሲብ ፈጻሚዎች ይሉናል። አሃ፣ ሰማይ ላይ ያለው አባታችን ተናዶብናል ማለት ነው” ይላል ከተከታዮቹ አንዱ።
በማሪዮት አራተኛ ፎቅ ላይ ነው ክንውኑ። ሙሉ አራተኛውን ፎቅ ይዘውታል።
ጥቁር ልብሶች የለበሱ አሉ። እስከ መሬት የሚረዝሙ ቀለማም ልብሶችም ይታያሉ። አንዳንዶቹ በእጅ የተሳለ ቀንድ አድርገዋል። ሰይጣናዊ ምልክት ያላቸው ንቅሳቶች ያሏቸው፣ በልዩ መንገድ ፂም ያሳደጉም ይስተዋላሉ።
አንዳንዶ ዕድሜያቸው ወላጅ ለመሆን የተቃረበ ነው። ልጆች ያሏቸውም አሉ። በዕድሜ ገፍተው በወንበር ድጋፍ የሚጓዙም አሉ።
በአሜሪካ ስላለው የሰይጣን አምልኮ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮችም ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ዕምነቱ የፖለቲካ ንቅናቄን ማዕከል ያደረገ ነው። ሃይማኖት እና አገር አስተዳደር መለያየት አለባቸው ብለው ያምናሉ።
በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት በማጣቀስ በአሜሪካ በተደጋጋሚ ክስ መሥርተዋል።
ጉዳያቸው ቁም ነገር አዘል ቢሆንም፣ ነገሮችን በስላቅ ሲናገሩ ይሰማሉ።
በአንድ ወቅት አሥርቱ ትዕዛዛትን የያዘ ምሥል በኦክላሆማ አደባባይ ሲቆም እነሱ ደግሞ በምላሹ 2.4 ሜትር የሚረዝም የሰይጣን ሐውልት ለማቆም ጠይቀዋል።
ከፍርድ ቤት ክርክር በኋላ አሥርቱ ትዕዛዛት እንዲነሱ ተወስኗል።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የሃይማኖት ልዩነትን የማክበር አንቀጽ አለው።
ሰዎች በራሳቸው ሰውነት ላይ ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል በሚል በኒው ሜክሲኮ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥ የበይነ መረብ ክሊኒክ ከፍተዋል።
ጽንስ ለሚያቋርጡ ደግሞ ጽንስ የማቋረጥ እምነታዊ ሥርዓት አዘጋጅተዋል።
ጽንስ ማቋረጥን የሚያበረታታ ንግግር የሚደረግበት እና ጽንስ ለሚያቋርጡ ምቾት ለመስጠት ያለመ ነው።
የዕምነቱ ተከታዮች በዕምነታተው መሠረት ጽንስ ማቋረጥ ከፈለጉ መከልከል እንደማይቻል ይገልጻሉ።

የካቶሊክ ጋዜጣ ይህን እምነት “የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶችን እና ምልክቶችን ከማጠልሸት ያልዘለለ” ሲል ከሌሎች ጋር በእኩል መታየቱን ነቅፏል።
የሎሃመር አነስተኛ ገቢ ያላቸው የጽንስ ማቋረጥ እንዲያገኙ የሚያስችል ፈንድ ነው።
የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ “ገንዘባችሁን እና እምነታችሁን ለዓመታት ይህን ሥራ ለሥሩ ተቋማት ማዋል አለባችሁ” ይላሉ።
በእምነቱ ተከታዮች ጉባዔ ላይ በጽንስ ማቋረጥ ረገድ የተገኙ ውጤቶች ይቀርባሉ።
ታዳሚዎቹ በጭብጨባ እና የቀንድ ምልክት በማሳየት ድጋፍ ይገልጻሉ።
ሌላው ፕሮጀክታቸው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከመደበኛ ትምህርት በኋላ ልጆችን ስለ እምነቱ ማስተማር ነው።
‘ኤዱኬሽን ውዝ ሳታን’ ይባል። ትምህርትን ከሰይጣን ጋር ብለን ልንተረጉመው እንችላለን።
በትምህርት ቤቶች እምነትን መስበክ ተገቢ እንደሆነ ባያምኑም፣ ሌሎች እምነት ተከታዮች ልጆችን ስለሚያስተምሩ ይህንን ለመቋቋም ትምህርቱ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ትምህርቱ ማኅበራዊ አገልግሎት፣ ሳይንስ፣ የእጅ ሙያ እና የሰላ ዕሳቤ ላይ ያተኮረ ነው። ወላጆች ትምህርቱን ሥጡልን ባሏቸው ቦታዎች ያስተምራሉ።
ተቃዋሚዎቻቸው ትምህርቱ ልጆችን እያስፈራራ ነው ሲሉ ይኮንናሉ።
አማኞቹ ግን ትምህርቱ ከአጋንንት ነጻ ነው ይላሉ።
‘ወዳጄ ሰይጣን’ የሚባል የልጆች መዝሙርም አላቸው።
“ሰይጣን ክፉ አይደለም። እንድትማሩ እና ለምን ብላችሁ እንድትጠይቁ ይፈልጋል። እንድትዝናኑ እና እራሳችሁን እንድትሆኑ ይፈልጋል። በነገራችን ላይ ገሃነም የሚባል ነገር የለም” ሲል መዝሙሩ ውስጥ ያለው የፍየል ገጸ ባህሪ ይዘምራል።
እአአ በ2020 ቲክቶክ ላይ ነው ስለ እምነት ተቋሙ የሰማችው።
“ስለ ነገሩ ለማጥናት ወሰንኩ። ትንሽ ፈርቼ ነበር። ማንኛውም ሰው እንደሚሆነው ማለት ነው። ልጆች መስዋዕት የማያቀርቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረብኝ። ከዚያ አኗኗሩን መማር ጀመርኩ። ስብሰባዎች መካፈል ጀመርኩ” ትላለች።
በ2019 ‘Hail Satan?’ የተባለ ዘጋቢ ፊልም በፔኒ ሌን ተሠርቷል።
በአሜሪካ የሚገኘውን የዕምነት ማዕከል መርሆችና ንቅናቄዎች ለመረዳት ፊልሙ ያግዛል።
በ2019 አባሎቻቸው 10,000 እንደነበሩ እና አሁን 700,000 እንደደረሱ ይናገራሉ።
ቦስተን ከተሰባሰቡት መካከል የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ሐኪሞች፣ መሃንዲሶች፣ አርቲስቶች፣ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭዎች፣ የሰርከስ ትርዒት የሚያሳዩ፣ የፋይናንስ ሠራተኞችም ይገኙበታል።
አብዛኞቹ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ናቸው። ክርስቲያን ወይም የሰይጣን አምልኮ የማይከተል የትዳር አጋር ያላቸውም አሉበት።
በፖለቲካ ግራ ዘመም ናቸው። ግን አባል ለመሆን የፖለቲካ አቋም አይጠየቅም። የፓርቲ አባል መሆንም አያስፈልግም።

ሰይጣንን መነሻ ያደረጉ ቅርጻ ቅርጾች የሚሠሩ አርቲስቶች ብዙ ናቸው።
‘ሰይጣን ይወዳችኋል’ የሚል ጽሑፍ ያላቸው ይገኙበታል። የሰይጣን ምልክት ያለው ባለ ክንፍ የፍየል ቅርጽም አላቸው።
ካናቴራም ይሸጣሉ። አባላት ሲገቡ ገንዘብ አይጠይቁም። የሚተዳደሩት በድጎማ እና ቁሳቁስ በመሸጥ ነው።
በቅርቡም ለልጆች የሚሆን መጽሐፍ አዘጋጅተዋል።
ሰባቱ ሕግጋት የተባሉ መመርያዎች አሏቸው። ቅድሚያ የሚሰጡት ለሐዘኔታ፣ የራስን ሰውነት ለመቆጣጠር፣ የሰዎችን መብት ለማክበር እንዲሁም ቁጣ መቀስቀስ መብት ነው።
ለልጆች በሚጻፉ መዝሙሮች ላይ እነዚህ መርሆች ይገኛሉ።
“የሰዎችን ራሳቸውን የመሆን መብት አክብሩ። በተለይም ከእናንተ የተለዩ ሲሆኑ። ንግግራቸው ካስቆጣችሁ ከማዘን ይልቅ ተዋቸው” ይላሉ መዝሙሮቹ።
አርሴሊ ሮጃስ ወደ ጉባዔው የመጣችው ከካሊፎርኒያ ነው።
“ሁሌም ሰይጣን አምላኪ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። ግን እንደዚያ መሆኔን ቶሎ አላወቅኩም” ትላለች።

የቤተ ዕምነቱ አጋር መሥራች ሉቺያን ግሬቫስ (በቅጽል ስሙ) የሚንቀሳቀሰው ከግል ጠባቂዎቹ ጋር ነው።
ጥቁር ለብሶ ነው በቦታው የተገኘው።
ንቅናቄውን የጀመረው ከአሥርታት በፊት ጄሪ (ቅጽል ስም) ከተባለ ጓደኛው ጋር ነው።
በሃይማኖት ነጻነት ያምናሉ። ክርስትና በሕግጋት ላይ ያሳድራል የሚሉትን ተጽዕኖ ይቃወማሉ።
በአሜሪካ ያሉ መገናኛ ብዙኃን ስለዚህ ቡድን ዘገባ የሚሠሩት አባላቱ ሃይማኖት ያላቸው በመምሰል ትኩረት መሳብ የሚፈልጉ መሳለቂያዎች እንደሆኑ በማድረግ ነው።
ይህንን ምልከታ ሉቺያን ይቃወማል።
“ሰዎች የምንናገረውን እውነት አድርጎ መቀበል ይከብዳቸዋል። የምንናገረው ነገር ሁሉ ቀጥተኛ ነው። ስለራሳችን የተሳሳተ ነገር አንናገርም” ይላል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽንስ ማቋረጥ የሚፈቅደውን ሕግ መቀልበሱን ተከትሎ ያቋቋሙትን የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት መስጫን የሰየሙት ፍርዱን ባስተላለፈው ዳኛ ስም ነው።
ስሙ የስላቅ ነው። የዳኛው ስም ሳሙኤል አሊቶ ሲሆን አገልግሎት መስጫውን የሰየሙት ‘የሳሙኤል አሊቶ እናት ሰይጣናዊ የጽንስ ማቋረጥ ክሊኒክ’ ብለው ነው።
ይህንን የስላቅ መጠሪያ መስጠታቸው ሰዎች በቁም ነገር እንዳይወስዷቸው እንደሚያደርግ በመጥቀስ ከቢቢሲ ለአጋር መሥራቹ ጥያቄ ቀርቧል።
“ሁሉም ነገር ቆፍጣና እና ሳቅ አልባ ነው የሚለውን መቃወም ስለምንፈልግ ነው” ሲል መልሷል።
“የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ ከመክፈት በላይ የቁም ነገር ሥራ የለም። ፈገግታ የምንወድ መሆችንን የሚያጠፋ ነገር ግን የለም” ሲል አክሏል።
አንዳንድ አባላት ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ በዚህ ቡድን እንደሚገኙ በግልጽ አይናገሩም።
በግልጽ የተናገሩት ከሥራ ተባረዋል። ልጆቻቸውን በአጋሮቻቸው የተቀሙ አሉ። አንዳንዶች መኪናቸው ሥር ሐሰተኛ ቦምብ አግኝተዋል።
የእምነት ተቋሙ የወሊድ ነጻነት ንቅናቄ ቃለ አቀባይ ካሊስ ብሊት የበይነ መረብ ስድቦች ይደርሷታል።
በተለይ ‘ሳታን ኮን’ የተባለው መሰናዶ ላይ ሳለች በዕምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ሳለች የሚያሳይ ምሥል ከወጣ በኋላ ብዙዎች እያጥላሏት ነው።
ዛቻ ሲደርሳት የመጀመሪያዋ አይደለም።
2016 ላይ አንድ ዘመዷ ስለሷ በበይነ መረብ መረጃ ለቆ ታጣቂ ቤቷ ድረስ ሄዷል።
“እሷን ለመግደል ነው የመጣሁት” ሲል ነበር ታጣቂው።
ስሟን ለመቀየር የተገደደችውም ለዚያ ነው።
ይህንን ሁሉ ማለፍ ግን እምብዛም አያስጨንቃትም።
“ጠላቶቼ እብዶች እና ኢቫንጃሊካል ምልከታ ያላቸው፣ መብቴን ሊነጥቁኝ የሚፈልጉ ከሆኑ ይሁኑ” ትላለች።
በ30ዎቹ ዕድሜ ያለው ታይፎን ኒክስ ራሱን የሚጠራው “ሳታኒም” በማለት ነው።
ከሃይማኖት አልባነት ነው ወደ ሰይጣን አምልኮ የተሸጋገረው።
“ሰይጣን አምልኮ የማምንበትን ነገር በአጠቃላይ ይወክላል። ይህም ሰውነት ላይ ሥልጣን ያለው ሰው መሆንን፣ ሐዘኔታን፣ አክብሮትን እና ሳይንስን ያካትታል” ይላል።
“ሰይጣን በተለየ ሁኔታ የሚያስቡ እና የተገለሉ ሰዎችን ያከብራል። በክርስትና ውስጥ ጓደኞቼ ዕውቅና ሲሰጣቸው አይቼ አላውቅም። ሰይጣን ደስ የሚለው ነገሩ ተቀባይ ነው። አካታች ነው። ይህም እኔን ይወክላል። ነገር ግን ሰይጣን አለ ብዬ አላምንም” ሲልም ያክላል።












