አዲሱ የሐማስ መሪ ሲመረጥ ከመድረክ ጀርባ ምን ሲካሄድ ነበር?

ሟቹ ኢስማኤል ሃኒያ እና አዲሱ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሟቹ ኢስማኤል ሃኒያ እና አዲሱ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር

በኢስማኤል ሃኒያ ምትክ ሐማስ መሪ ሲመረጥ የቢቢሲው ሩሺዲ አቡአሉፍ ዶሃ ነበር። ከመድረክ ጀርባ የነበሩ ሁኔታዎችን እንዲህ ቃኝቷቸዋል።

**

በዶሃ ከተሰበሰበው የሐማስ ጉባኤ ኢስማኤል ሃኒያ በቴህራን ይገደላል ብሎ ያሰበ ያለ አይመስልም።

ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ዶሃ የተመሙ የሐማስ አባላት ድንጋጤው አብሯቸው አለ።

ሐማስ እና እስራኤል የለየለት ውጊያ ሲያደርጉ ዓመት ሊደፍኑ ሁለት ወራት ነው የቀራቸው። በዚህ ጊዜ ሐማስ እንደሚለው ከ40 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።ከሟቾቹ ውስጥ የሕጻናት ቁጥር ያይላል።

የኢስማኤል ሃኒያ ግድያን ግን ማንም የጠበቀው አይመስልም።

ሃኒያ ከእስራኤል ጋር ይደረጉ የነበሩ ድርድሮችን ሲመራ የነበረ ከፍተኛ የሐማስ ዲፕሎማት ነው።

በተለይ በወታደራዊ ክንፉ በኩል የነበሩ ጫናዎችን በመቋቋም ሚዛናዊ አቋም በመያዝ የሚደረጉ ድርድሮች ሰላም እንዲያመጡ የተጋ ሰው ነበር።

ድርድሩ እንዲቀጥል፤ የሃኒያ ወሳኝ ቦታ በጊዜ መሞላት አለበት።

ለዚህም ነው ተወካዮች እዚህ ጊዜ መቀመጫቸው በሆነችው ዶሃ የተገኙት።

በዶሃ በነበረው የሐዘን ሥነ ሥርዓት በርካታ ሰዎች በነጭ ድንኳን ለቅሶ ተቀምጠው ሟችን ሲሰናበቱ ነበር። የሟች ኢስማኤል ሃኒያ ፎቶዎች በሁሉም አቅጣጫ ተሰቅለው ይታያሉ።

ሁኔታው የኢስማኤል ሃሃኒያ ስንብት ብቻ ሳይሆን የዘመን ሽኝት ይመስል ነበር።አሮጌው ምዕራፍ ተዘግቶ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተ ይመስላል፤ በሐማስ ውስጥ። የጽንፍ ምዕራፍ።

እኔ እንደጋዜጠኛ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተሰብስበው አዲስ መሪ ሲመርጡ ስመለከት የመጀመርያዬ አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 2004 እስራኤል የሐማስ አባት የሚባሉትን ሼክ አሕመድ ያሲንን ከገደለች በኋላ እርሳቸውን ለመተካት ምርጫ ሲካሄድ ነበርኩ።

ትዝ ይለኛል በጋዛ የሟቹ ቤት ውስጥ ነበር ምርጫው የተደረገው። አብዱል አዚዝ አል ራንቲሲ አዲሱ መሪ ተደርጎ ተመረጠ።

በተመረጠ በወሩ ግን እስራኤል እሱንም ገደለችው።

ሐማስ ጋዛን ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ ሲመራ ቆይቷል። በዚህ ጊዜ በርካታ አባላቱ ተገድለው አቅሙ እንዲሽመደመድ ሆኗል።

ከዚህ ሁሉ በላይ የድርጅቱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ “ሁለተኛ ቤቴ” በሚላት ቴህራን መገደሉ በድርጅቱ አባላት ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ሐማስ እንደሚለው መሪው የተገደለው በፀረ ሰው ሚሳኤል ነው። ሲገደል ስልኩን እየተመለከተ ነበር። የኢራን አብዮታዊ ዘብ እንደሚለው ደግሞ እሱን ለመግደል ሰባት ኪሎ ግራም የሚመዝን ጥይት ተሸካሚ ሚሳኤል ነው የተወነጨፈው።

አንዳንድ የምዕራብ አገራት መገናኛ ብዙኃን ግን ሃኒያ የተገደለው ከወራት በፊት የእርሱ ማረፊያ ውስጥ በምሥጢር ገብቶ በተቀመጠ ፈንጂ ነው።

የኢስማኢል ሃኒያ ለቅሶ ሥነ ሥርዓት በዶሃ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኢስማኢል ሃኒያ ለቅሶ ሥነ ሥርዓት በዶሃ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን ምርጫው ሊደረግ ነው።

በነጩ የለቅሶ ድንኳን ውስጥ አንድ ዕድሜያቸው በ60ዎቹ አጋማሽ የሚገኙ፣ ፀጉራቸው በሽበት የተወረረ፣ ፂማቸው በአጭር የተቆረጠ፣ ንቁ ዐይኖች ያሏቸው፣ ትኩረት ላለመሳብ ፈንጠር ብለው የተቀመጡ ሰው አሉ።

የሐማስ ሚዲያ ኃላፊ ጎንተል አደረገኝና፣ “ዐይንህን ከእርሳቸው አትንቀል” አለኝ።

“ማናቸው ደግሞ እርሳቸው?” አልኩት።

“አቡ ኡማር ሐሳን ይባላሉ” አለኝ።

አቡ ኡማር ሐሳን ወይም መሐመድ ዳርዊሽ የከፍተኛው የሐማስ ምክር ቤት (ሹራ) መሪ ናቸው።

በሐማስ ሕገ መንግሥት መሠረት አቡ ኡማር በመጪው ኅዳር ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሐማስ መሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

የለቅሶ ሥነ ሥርዓቱ እንዳበቃ ይህ ካውንስል ስብሰባውን ጀመረ።

አቡ ኡማር ሐሳን እንደሚመረጡ ነው የሚጠበቅ የነበረው።

ከአፍታ በኋላ ያህያ ሲንዋር እንደተመጠረ ሰማን። ለብዙዎች ይህ ውጤት የተጠበቀ አልነበረም።

ያህያ ሲንዋር በእስራኤል እስር ቤት ነው የኖረው። በ2011 (እአአ) እስራኤል ጊላድ ሻሊት በተባለ እስረኛዋ ለውጥ ፈታችው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያህያ ሲንዋር አንድ ቀን ሐማስን እንደሚመራ ያውቅ ነበር።

ሲንዋር ከፖለቲካው ይልቅ ለወታደራዊ ክንፉ ቅርብ ነው። ለምሳሌ ወንድሙ መሐመድ ትልቁን የሐማስ ባታሊዮን ይመራል። ዝነኛው መሐመድ ዴይፍ ደግሞ የሲንዋር ጓደኛው ብቻ ሳይሆን ጎረቤቱና አብሮ አደጉ ነው።

ዴይፍ እስራኤል ከብዙ መከራ እና ሙከራ በኋላ ባለፈው ሳምንት ገደልኩት ያለችው ከፍተኛ የሐማስ ኮማንደር ነው።

ሲንዋር እና ዴይፍ አብረው ነው የተማሩት። ሁለቱም ያደጉት በኻን ዩኒስ መጠለያ ነው።

ይህን ሁሉ ከግምት በማስገባት ሲንዋርን መምረጥ እብደት ነው ያሉ አልጠፉም።

የእስራኤል ባለሥልጣናት በተለይ በደቡባዊ እስራኤል የተፈጸመውን ጥቃት ያቀነባበረው እሱ ነው ብለው ያምናሉ። በጥብቅ ከሚፈልጓቸው የሐማስ ባለሥልጣናት አንዱ ሲንዋር ነው።

“ሐማስ ውስጥ በእሱ መመረጥ ሙሉ ስምምነት የለም” ይላል አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን።

አንዳንዶች ስጋታቸውን በግልጽ በከፍተኛ ጉባኤው (ሹራ) አስተጋብተዋል።

ሌሎች ለዲፕሎማሲ ቀረብ ያለ ሰው ብንመርጥ ይሻላል በሚል ተሟግተዋል። በመጨረሻ ግን የድምጽ ብልጫ በማግኘቱ ተመርጧል።

የጋዛ ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እያካሄደችው ባለው ጥቃት በ10 ወራቱ ውስጥ ጋዛ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች።

ሌላው የሐማስ ባለሥልጣን እንደነገሩኝ ካውንስሉ ትልቅ አቅም እና ጉልበት ያለውን አቡ ኡማር ሐሰንን ሳይመርጥ ቀርቷል።

ኡማር ሐሳን ከመጋረጃ ጀርባ ሥራ የሚሠራ ትልቅ አቅም ያለው የሐማስ ሰው ነው። ይሁንና በሕዝብ ዘንድ እምብዛምም አይታወቅም።

ያህያ ሲንዋር ግን በተቃራኒው ነው። ስሙ በአረቡ ዓለም ከአጽናፍ አጽናፍ ናኝቷል።

በተለይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ ከባድ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የያህያ ሲንዋር ስም በዓለም ዙሪያ ናኝቷል።

“ሲንዋር ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በኋላ በአረቡ እና በሙስሊሙ ዓለም ስመ ገናና ሆኗል” ይላሉ ሌላ የሐማስ ባለሥልጣን።

ሲንዋር ከኢራን ጋር ቅርበት አለው። ከሂዝቦላህ ጋር ቅርበት አለው። ከሁቲዎች ጋር ቅርበት አለው። እሱን መምረጥ ለእስራኤል አንዳች መልዕክት ያስተላልፋል፤ መልዕክቱ ደግሞ “አንንበረከክም” የሚል ነው ይላሉ እኚሁ ባለሥልጣን።

አንዳንድ የአረብ እና የምዕራብ አገራት የሐማስ ከፍተኛው ምክር ቤት ሲንዋርን መሪው አድርጎ እንዳይሰይም ሲጠይቁ ነበር።

ይህም የሆነው የሲንዋር ስም በእስራኤል ላይ ከተፈጸመው ከባድ ጥቃት ጋር ስለተያያዘ ለዲፕሎማሲ ሥራ ማነቆ እንደሚሆን ቀድሞ በመረዳት ነው።

እሱም ሆነ የሚመራው ድርጅት ሐማስ በምዕራብ አገራት አሸባሪ በሚል ተመዝግቦ ይገኛል።

ሌላ የሐማስ ባለሥልጣን ሲነግሩኝ “እሱን የመረጥነው የመስከረም 26ቱን ጥቃት ስለመራ ነው። ክብር ይገባዋል። ይህም ትግሉን ለመምራት ብቁ ያደርገዋል” አሉኝ።

ይህ ሐማስ በእስራኤል ላይ የሰነዘረው መብረቃዊ ጥቃት 10 ወራትን ቢዘልቅም በዲፕሎማሲው ረገድ ፈቀቅ ሊል አልቻለም።

ቢቢሲ ከምርጫው በኋላ ባገኘው መረጃ ከሆነ ኳታር እና ግብፅ አሁን አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ሐሳብ ላይ እየሠሩ ነው።

አዲሱ ሐሳብ የሚተገበረው ኢራን ለሃኒያ ጥቃት ምላሽ እንዳትሰጥ በማግባባት ነው። ያ ከሆነ እስራኤል በጋዛ ጦርነቱን ታቆማለች። በፊላዴልፊ አካባቢ ያሉ ወታደሮቿም ለቀው ይወጣሉ።

ፊላዴልፊ ኮሪደር የሚባለው መቶ ሜትር የሚሰፋ13 ኪሎ ሜትር የሚረዝም በጋዛ እና በግብፅ ድንበር ያለ መተላለፊያ ቦታ ነው። ይህም ሌላው ጋዛ ከእስራኤል ጋር የምትዋሰንበት ስፍራ ነው።

አንድ ከዚህ የሰላም ሐሳብ ጋር ትውውቅ ያላቸው የፍልስጤም ባለሥልጣን በዶሃ እንደነገሩኝ ከሆነ የግብፅ የደኅንነት ሰዎች አንድ ልዩ ልዑክ ወደ ዶሃ ልከዋል።

ኢራን አጸፋ ጥቃት እንዳትሰነዝር ማግባባቱ ተጀምሯል።ያ ከተሳካ ምናልባት የተኩስ አቁሙ ተስፋ ሰጪ ይሆናል።

ለጊዜው የጋዛ ስቃይ ቀጥሏል። የተኩስ ድምጾች አሁንም ይሰማሉ።

በሐማስ ውስጥ አክራሪ አቋም ያለው ሲንዋር እንደ ቀደምቶቹ የእስራኤል ጥቃት ሰለባ ካልሆነ እና በሕይወት ከቆየ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሐማስን ይመራል።