“አክራሪ” የሚባሉት ያህያ ሲንዋር የሐማስ ቡድን ጠቅላይ መሪ ሆነው ተሾሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሐማስ በዶሀ ለሁለት ቀናት ያክል የሚቆይ ስብሰባ ካደረገ በኋላ ያህያ ሲንዋርን የቡድኑ ጠቅላይ መሪ አድርጎ ሾመ።
ያህያ ሲንዋር ባለፈው ሳምንት ቴህራን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የተገደሉት ኢስማኢል ሃኒያ ተክተው ይሠራሉ።
ሲንዋር ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ የቡድኑ መሪ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። አሁን የቡድኑ ፖለቲካዊ ክንፍ ኃላፊም ሆነው ይሰራሉ።
አንድ ነባር የሐማስ መሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሐማስ መሪዎች ያለምንም ተቃውሞ ነው ሲንዋርን መሪ አድርገው የመረጡት።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት እየተካረረ ሲሆን ለግድያው እስራኤልን ተጠያቂ የሚያደርጉት ኢራን እና አጋሮቿ የሃኒያን ግድያ ለመበቀል ዝተዋል።
እስራኤል ስለግድያው እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።
በዶሀ ለሁለት ቀናት የዘለቀው የሐማስ ከበድ ያለ ስብሰባ ቀጣዩ የቡድኑ መሪ ማን ሊሆን ይገባል በሚለው ላይ የመከረ ነበር።
ከብዙ ክርክር እና ውይይት በኋላ ሁለት ሰዎች ዕጩ ሆነው ቀርበዋል። እኒህም ያህያ ሲንዋር እና ሞሐመድ ሐሰን ዳርዊሽ ናቸው። ዳርዊሽ ብዙም መታየት የማይወዱ ነገር ግን ጠቅላይ የሹራ ምክር ቤት የተሰኘው የሐማስ ፖሊት ቢሮ የሚመርጠው ክንፍ ኃላፊ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው።
ምክር ቤቱ በስተመጨረሻም ሲንዋርን ያለምንም ተቃውሞ የቡድኑ ኃላፊ አድርጎ የመረጡ መሆኑን የጠቆሙት አንድ የሐማስ ኃላፊ “እስራኤልን መልዕክት ያስተላለፈ ምርጫ” ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሃኒያን ገደሉት። መፍትሔ ለማምጣት የሚሯሯጥ ለዘብተኛ የሆነ ሰው አንድ እሱ ነበር። አሁን ከሲንዋር እና ከወታደራዊው አመራር ጋር እንዴት እንደሚመክሩ እናያለን” ብለዋል ባለሥልጣኑ።
የቀጣናው የዲፕሎማሲ ሰዎች ሀኒዬህ ከሌሎች የሐማስ መሪዎች ሲነፃፀሩ ለዘብተኛ ናቸው ሲሉ የቡድኑን የቀድሞው የፖለቲካ ኃላፊ ይገልጿቸው ነበር።
በሌላ በኩል ያህያ ሲንዋር እጅግ በጣም አክራሪ የሐማስ መሪ ተደርገው ይቆጠራሉ።
ሲንዋር በአሁኑ ወቅት በእስራኤል እጅግ በጣም ከሚፈለጉ መሪዎች መካከል ቁንጮው ናቸው። የእስራኤል ደኅንነት አባላት ባለፈው ጥቅምት የተፈፀመውን ጥቃት ያቀነባበሩት ሲንዋር ናቸው ብለው ያምናሉ።
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2023 ሐማስ በእስራኤል ምድር ባደረሰው ጥቃት 1200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ደግሞ ታፍነው ተወስደው ነበር።
“ያህያ ሲንዋር የተባሉት አሸባሪ ኢስማኢል ሃኒያን ተክተው የሐማስ መሪ ሆነው መመረጣቸው ቡድኑን ከዚህ ምድር ለማጥፋት ሌላ ምክንያት ነው” ሲሉ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።
“ያህያ ሲንዋር አሸባሪ ነው። በታሪክ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ጥቃት በመፈፀሙ ኃላፊነት ይወስዳል” ሲሉ የእስራኤል ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሀጋሪ ለሳዑዲ አረቢያው አል አራቢያ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሲንዋር ባለፈው ጥቅምት ከደረሰው ጥቃት በኋላ በአደባባይ ታይተው አያውቁም። ጋዛ ውስጥ “ከምድር በታች 10 ወለል” ውስጥ ተደብቀዋል ተብሎ ይታሰባል ሲሉ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ባለፈው ሰኔ መናገራቸው አይዘነጋም።
ሲንዋር በአውሮፓውያኑ 1962 ጋዛ በሚገኘው ኻን ዩኒስ የስደተኞች መጠለያ ነው የተወለዱት።
ሲንዋር በ1980ዎቹ መጨረሻ ማጅድ የተሰኘውን የሐማስ ደኅንነት ቡድን መሠረቱ። ቡድኑ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ከእስራኤል ጋር ያበሩ ፍልስጤማዊያን ዒላማ ማድረግ ነበር።
አብዛኛውን ሕይወታቸው እስራኤል በሚገኝ እስር ቤት ያሳለፉት ያህያ በ1988 ለሶስተኛ ጊዜ ሲታሰሩ አራት ዓመት ተፈርዶባቸው ነበር።
በ2011 እስራኤል በሐማስ ቁጥጥር አምስት ዓመት የቆየው ወታደሯ ጊላድ ሻሊትን ለማስለቀቅ ስትል ከእስር ከፈታቻቸው 1027 ፍልስጤማዊያን መካከል ሲንዋር አንዱ ነበሩ።
የ61 ዓመቱ ሲንዋር በ2017 በጋዛ የሐማስ ፖለቲካዊ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመው አገልግለዋል።
አሜሪካ “ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች” ከምትላቸው ሰዎች ስም ዝርዝር መካከል ያህያ ሲንዋር ይገኙበታል።












