ሙስሊሞች እና ስደተኞች ላይ ያነጣጠረው የዩኬ አመፅ ኢትዮጵያውያንንም አስግቷል

ሁማ ካን
የምስሉ መግለጫ, ሁማ ካን የወትሮ መመላለሻ መንገዷን ለመቀየር ባታስብም ውስጧ ፍርሀት አለ

“ሰዎች ተቃውሞ ነው ሲሉ ይጠሩታል. . . ለእኔ ግን ይህ የሽብር ጥቃት ነው።”

ሁማ ካን በግሬተር ማንቸስተር ግዛት የስቶክፖርት ክፍለ ግዛት ነዋሪ ናት። በአካባቢው ባለ አንድ ትምህርት ቤት የእግሊዝኛ መምህርት ናት።

ምንም እንኳ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የተነሳውን አመፅ ተከትሎ ልቧ ፍርሃት ቢሰማውም ጠንከር ብላ ከመዝለቅ ውጪ አማራጭ የላትም።

“መጀመሪያ በጣም ደንግጬ ነበር። መጀመሪያ አመፅ ነበር፤ ቀጥሎ ተቃውሞ ሆነ። እኔ ግን የሽብር ጥቃት ነው የምለው። ባልተጨበጠ የማኅበራዊ ሚድያ ጭምጭምታ ተነስቶ እዚህ መድረሱ በጣም ያስደነግጣል” ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።

የወትሮ መመላለሻ መንገዷን ለመቀየር ባታስብም ውስጧ ግን በፍርሃት ርዷል።

“ከልጅነቴ ጀምሮ ዒላማ መሆን አዲሴ አይደለም። በሃይማኖታዊ አስተሳሰቤ ምክንያት ተገፍቻለሁ። በሌላ ሳይሆን በአለባበሴ እና በማንነቴ ምክንያት” ትላለች።

“እርግጥ ነው በፍርሃት የማይሆን ነገር አላደርግም። ቢሆንም ሁሌም ከቤቴ ስወጣ ዛሬ አንዳች አደጋ ይደርስብኝ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያቃጭልብኛል።”

“አስደንጋጭ እና ከባድ ነው”

ለበርካታ ዓመታት ብሪታኒያ ውስጥ የኖረው ባሕሩ ሸዋዬ የተባለ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ለቢቢሲ እንደተናገረው ቀኝ አክራሪዎች “ስደተኞች ወደ አገራቸው ይመለሱ፤ ከአገራችን አስወጧቸው” የሚል ፀያፍ የሆነ እንዲሁም ግጭት የሚያበረታታ መልዕክት ይዘው ነበር።

በፈጸሙትም ጥቃት የፖሊስ መኪና መቃጠሉን፣ ቤቶች ላይ ጥቃት ማድረስን እና ከተለያዩ አገራት የመጡ ስደተኞች የከፈቷቸውን ሱቆች ማውደማቸውን እና ነገሩ ከቁጥጥር ውጪ መውጣቱን ገልጿል።

ሦስት ታዳጊዎች በተፈጸመባቸው የስለት ጥቃት ከተገደሉ እና በርካቶች ከቆሰሉ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተሠራጩ የተሳሳቱ ወሬዎች ምክንያት ነጭ አክራሪዎች ስደተኞችን እና ሙስሊሞችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት ሲፈጽሙ እና ተቃውሞ ሲያሰሙ ሳምንት ሆኗቸዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ ስደተኞች ይገኙባቸዋል የሚባሉትን የጥገኝነት ጠያቂዎች የተጠለሉባቸው ሆቴሎችንም ዒላማ አድርገዋል በርካታ ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ሆቴሎች የሚገኙ ሲሆን፣ የብሪታኒያ መንግሥትም ለሆቴሎቹ ጥበቃ እያደረገ ነው።

ባሕሩ እንደሚለው የአንድ ሱዳናዊ ሱቅ መቃጠሉን ከመስማቱ ውጪ በኢትዮጵያውያን ላይ ስለደረሰ ጉዳት የሰማው ነገር የለም። ጨምሮም በአገሪቱ በስደተኞች ላይ ያለው አሉታዊ አመለካከት አዲስ ባይሆንም “አሁን እያየን ያለነው ነገር ግን አስደንጋጭ እና ከባድ ነው” ሲል የተከሰተው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።

የሚያስፈራ ዝምታ

አላ
የምስሉ መግለጫ, አላ ለጊዜው አንገቴን ደፍቼ እየኖርኩ ነው ይላል

ቀኑ ገና በቅጡ ሳይጋመስ ከማንቸስተር ከተማ በስተሰሜን ወጣ ብሎ የሚገኘው ሳልፈርድ የገበያ ማዕከል ያለወትሮው እጅግ በሚያስፈራ ፀጥታ ተውጧል።

እዚህ አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊኖር ይችላል የሚል ወሬ በማኅበራዊ ሚድያ መንሰራፋቱን ተከትሎ በአካባቢው ያሉ ሱቆች መስኮታቸውን ዘግተዋል።

የአስፋልቱን ጥግ ታከው በጥንቃቄ ከሚራመዱ ነዋሪዎች በቀር ምንም አይታይም። በአንዱ አውራ ጎዳና ፖሊስ ጭምብል ያጠለቁ ወጣቶችን እያስቆመ ይፈትሻል። ወጣቶቹ በፖሊስ ድርጊት ባይደሰቱም ተቃውሞ ግን አላሰሙም።

ከማንቸስተር በስተደቡብ ባለው አቅጣጫ ያሉ ሰፈሮችን ግን ፀጥታ እና ሰላም የራቃቸው አይመስልም።

ሞስ ሳይድ የተባለችው መንደር ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከእስያ እና ከአፍሪካ በሚመጡ ሙስሊሞች ዘንድ ተወዳጅነት አላት። ባለፈው ማክሰኞ ምግብ ቤቶችን እና ካፌዎች እስከ አፍጢማቸው ሞልተው ሲስተናግዱ ነበር።

በዚህች መንደር የሚኖሩ እና የሚሠሩ ሰዎች ከማኅበረሰቡ በሚያገኙት ጥበቃ ምክንያት ደኅንነት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ። ነገር ግን ያንተ ቤት ሲንኳኳ ነው እና ጎረቤታቸው ያለው ነገር ያሳስባቸዋል።

“በ2018 [በአውሮፓውያኑ] ነው ከሶሪያ የመጣሁት። ቤተሰቤ እና እኔ እዚህ ሰላም አግኝተናል” ይላል ማንቸስተር ውስጥ የአረቢኛ መፃሕፍት መደብር ያለው አላ።

አብዱል
የምስሉ መግለጫ, አብዱል ሐኪም በሶማሊያ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት በመሸሽ ነው ወደ እንግሊዝ የተሰደደው

“ከሰሞኑ የሆነው ነገር ወደፊት ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን አጠራጣሪ አድርጎታል። ለጊዜው አንገቴን ደፍቼ ነው እየኖርኩ ያለሁት። ድጋሚ መሰደድ ፈፅሞ አልፈልግም” ሲል አላ ለቢቢሲ ይናገራል።

አብዱል ሐኪም ደግሞ ከ20 ዓመታት በፊት ነው በሶማሊያ ያለውን ጦርነት ሸሽቶ በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ያገኘው። ነገር ግን አሁን አክራሪ ቀኝ አክራሪዎች ከሙስሊሞች ጋር እንዳይጋጩ ስጋር ገብቶታል።

“እኒህ ሁሉት ቡድኖች ከተጋጩ አመፅ ብቻ ሳይሆን የእርስ በርስ ጦርነት ሊነሳ ይችላል። የእርስ በርስ ጦርነት ነው ከሶማሊያ ተሰድጄ ማንቸስተር እንድመጣ ያስገደደኝ።”

አላ፤ መስጅዶችን፣ ሱቆችን እና ቤቶችን ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆነ ጉልበት እንጠቀማለን የሚሉ አንዳንድ ሙስሊሞች ጥሪም ያሰጋዋል።

“እኔ በዚህ አልስማም። ይህንን ማድረግ ካለብን ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረን ነው። የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ደኅንነት ለመጠበቅ ቃል ከገባው መንግሥት ጋር ተባብረን ነው መሆን ያለበት።”

“መስጅዳችንን የመጠበቅ መብት እንዳለን አውቃለሁ፤ የእምነት ነፃነትም እንዳለን አምናለሁ። ነገር ግን ይህንን በራሳችን እናድርግ ካልን አሸባሪዎች ናቸው የሚል ስም እንደሚሰጠን ግልፅ ነው” ይላል።

ሁማ ካን ታዳጊው ትውልድ እዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ መግባቱ ያሳዝናታል።

“የ12፣ የ10 እና የ7 ዓመት ዕድሜ ላይ ላሉ የአጎቴ ልጆች በማንቸስተር አውራ ጎዳናዎች ላይ እየሆነ ያለው ነገር ሁሉንም አይወክልም፤ የተሰባጠረ ባሕላችን መገለጫ አይደለም ብሎ ማስረዳት ቀላል አይደለም።”

‘እዚህ ዘረኝነት አጋጥሞኝ አያውቅም’

ጃዋድ
የምስሉ መግለጫ, ጃዋድ፤ የግሬተር ማንቸስተር የሙስሊሙ ማኅበረሰብ 'ሴፍሪ ፎረም' ሊቀመንበር ናቸው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከሶሪያ ወደ ብሪታኒያ ከሦስት ዓመታት በፊት የመጣው ሳይድ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በአህጉረ አውሮፓ በመዘዋወር ነው።

“የስዊድን ፓስፖርት አለኝ። በአውሮፓ ዙሪያ ተዘዋውሪያለሁ። ወደዚህ አገር [ብሪታኒያ] የመጣሁት ሆነ ብዬ ነው። ሁሉም እምነቶች የሚከበሩበት፤ ክርስቲያኑ፣ ሙስሊሙ፣ አይሁዱ - በሕብረት የሚኖርበት ስለሆነ ነው” ይላል።

“ከሰሞኑ የተፈጠረውን ዘረኛ ክስተት ስሰማ እጅግ ደንግጫለሁ። እኔ በግሌ እዚህ ዘረኝነት አጋጥሞኝ አያውቅም። መጀመሪያ ዜና ላይ ስናየው ደንግጠን ነበር፤ ምክንያቱም መሰል ክስተት ሲያጋጥመን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ለሦስት ዓመታት ስኖር ሰዉ እጅግ መልካም መሆኑን ታዝቢያለሁ። ቋንቋ እንኳ ሲያስቸግረኝ ያግዙኛል። ለዚህ ነው የሆነው ነገር ያስደነገጠኝ።”

ባለፈው ሳምንት (በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 29) በሳውዝፖርት ከተማ ሦስት ታዳጊ ሴቶች በቢላ ክፉኛ ከተወጉ በኋላ ነው በእንግሊዝ እና በሰሜን አየርላንድ ባሉ ከተሞች ውስጥ አመፅ የተነሳው።

ይህን አመፅ ተከትሎ በተለይ በማኅበራዊ ሚድያዎች ሐሰተኛ መረጃዎች እየተሰራጩ ሲሆን፣ አክራሪ ቀኝ ዘመም እና ፀረ-ስደተኛ ሐሳቦች እየተንፀባረቁ ይገኛሉ።

በሳውዝፖርት ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሠራጩ ዜናዎች ተጠርጣሪው በጀልባ ወደ ዩኬ የመጣ ጥገኝነት ጠያቂ ነው የሚል ሐሰተኛ ወሬ ተንሰራፋ። ተጠርጣሪው ሙስሊም ነው የሚሉ ያልተጨበጡ ወሬዎችም ተዛምተዋል።

በ2011 ማርክ ዱጋን የተባለው ግለሰብ በፖሊስ ከተገደለ በኋላ በዩናይትድ ኪንግደም ከተነሳው አመፅ በኋላ ይህ እጅግ ከፍተኛው ተቃውሞ እና ረብሻ ነው።

የግሬተር ማንቸስተር ሙስሊም ሴፍቲ ፎረም ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ጃዋድ አሚን ባለፉት 20 ዓመታት እዚያም እዚህም አመፆች አይተናል ይላሉ።

“ይህኛውን አሳሳቢ የሚያደርገው ጥላቻን መንዛት በሚፈልጉ ሰዎች በማኅበራዊ ሚድያ በተሰራጨ ያልተጨበጠ ወሬ መነሳቱ ነው። ተጠርጣሪው ሙስሊም ሆነ አልሆነ ለእንደዚህ ዓይነት አመፅ መንስዔ ሊሆን ባልተገባ ነበር።”