የደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በድጋሚ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት ወታደራዊ አገዛዝን አውጀው አገራቸውን ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ ከመክተታቸው ጋር በተያያዘ በድጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።
ዮን ሱክ ዮልን ከዚሁ አዋጃቸው ጋር በተያያዘ በሚያዝያ ወር ከሥልጣናቸው ተነስተዋል።
የቀድሞው ፕሬዚደንት በዚህ ውሳኔያቸውም በታሕሳስ ወር ለስድስት ሰዓታት ያህል ወታደራዊ አገዛዝን በአገሪቱ ላይ እንዲሰፍን አድርገዋል።
ረቡዕ ዕለት በሴኡል የማዕከላዊ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት አንድ ከፍተኛ ዳኛ ዮን ሱክ ዩል ማስረጃ ሊያጠፉ ይችላል በሚል ፍራቻ የእስር ማዘዣ አውጥተዋል
ዩን ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር ሲውሉ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚደንት ሆነው ወታደራዊ አገዛዝን ለማስፈን በመሞከር እና እርሱን ተከትሎ የተነሳ አመፅን በመምራት ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ረቡዕ ሰባት ሰዓት በፈጀው የችሎት ክርክር ልዩ አማካሪ ቡድን በአምስት ቁልፍ ክሶች ላይ የእስር ማዘዣ ለማውጣት ተከራክረዋል ሲል የደቡብ ኮሪያ የዜና ወኪል ዮንሃፕ ዘግቧል።
ክሱ የዮን የማርሻል ሕግ ከማወጃቸው በፊት የተወሰኑት የካቢኔ አባላት ወደ ስብሰባ ባለመጋበዝ መብታቸውን መጣሳቸውን ያጠቃልላል።
ዩን የእስር ማዘዣ ውሳኔን ለመጠባበቅ ወደ ሴኡል ማቆያ ማዕከል ከመወሰዳቸው በፊት በመጀመርያ ክሱን ለመቃወም ከጠበቆቻቸው ጋር በመሆን በችሎቱ ተገኝተዋል።
በጥር ወር በቁጥጥር ስር ሲውሉ በርካቶች ለቀናት የዘለቀ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በኋላም መርማሪዎች ከሚኖሩበት ማዕከላዊ ሴኡል በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቀመጡ ማገጃዎችን እና ሽቦዎችን ማለፍ አስፈልጓቸው ነበር።
ዩን ከሁለት ወራት እስር በኋላ ፍርድ ቤት በቴክኒካል ምክንያት በቁጥጥር ስር መዋላቸወን ውድቅ በማድረጉ ተለቅቀዋል።
ነገር ግን አሁንም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የዕድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት ሊቀጡ ይችላሉ።
አቃቤ ሕግ ዮን ወታደራዊ አገዛዝ እንዲሰፍን ያወጁትን አዋጅ ትክክለኛነት ለማሳየት በሚል ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዲበሩ ማዘዛቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማግኘቱን ዘገባዎች ጠቁመዋል።
ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖችም ከወታደራዊ አገዛዝ ሕጉ ጋር በተያያዘ አመጽ በማስነሳት እና ሥልጣንን አላግባብ መጠቀምን የሚሉ ክሶች ይጠብቃቸዋል።
አመፅ መቀስቀስ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንቶች ያለመከሰስ መብት ከማያገኙባቸው ጥቂት የወንጀል ክሶች መካከል አንዱ ነው።
አሁን ግን ዩን ፕሬዝዳንት ባለመሆናቸው ሌሎች የወንጀል ክሶችም ይጠብቋቸዋል።
ዩን ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ በተደረገ ፈጣን ምርጫ ሊ ጄ ሚዩንግ በሰኔ ወር የፕሬዚደንትነት ሥልጣኑን ተረክበዋል።
ሊ ቀውሱን ተከትሎ የአገሪቱን ዴሞክራሲ ለማጠናከር ቃል በመግባት ዘመቻ አካሄደዋል።
እንዲሁም ዩን ያወጁትን ወታደራዊ አገዛዝን እንዲሁም ሌሎች የወንጀል ክሶችን የሚያጣራ ልዩ የአማካሪ ቡድን አዋቅረዋል።















