ደንበኞች የሚፈልጉትን አንስተው በታማኝነት ከፍለው የሚገለገሉበት ጠባቂ አልባ ሱቆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእኩለ ሌሊት የሚቀመስ ነገር ለሻተ በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴዑል የሚገኙ ሱቆች በሮቻቸውን ክፍት አድርገው ይጠብቃሉ።
እነዚህ ሱቆች 24 ሰዓት ነው የሚያገለግሉት።
አንደኛው ሱቅ አይስ ክሪም ይሸጣል። የተለያዩ የአይስ ክሪም ዓይነቶችን የያዙ ማቀዝቀዣዎች ተደርድረዋል። ነገር ግን ሱቆችን የሚጠብቅም ሆነ ገንዘብ የሚቀበል ሰው የለም።
ሰዎች ወደ ሱቆቹ ገብተው የፈለጉትን ካነሱ በኋላ በታማኝነት ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ከፍለው ይወጣሉ።
ከአይስ ክሪም ሱቅ በተጨማሪ የጽሕፈት አገልግሎት፣ የቤት እንስሳት ምግብ እንዲሁም ሱሺ የተባለውን ተወዳጅ የሆነ ምግብ የሚያቀርቡ ሱቆች አሉ።
ሁሉም አንድ ሠራተኛ የላቸውም። ሸማቹ ያሻውን አንስቶ ከመውጣቱ በፊት በማሽን ይከፍላል።
በተጨናነቀው የከተማዋ ክፍል ሠራተኛ የሌላቸው መሸታ ቤቶችም አሉ።
"እንዲህ ያለውን መጠጥ ቤት ለማስተዳደር ከ12 እስከ 15 ሰው ያስፈልገኛል። ነገር ግን ሁለት ሠራተኛ ብቻ ነው ያለኝ" ይላል ሱል 24 የተባለ መጠጥ ቤት ያለው ኪም ሱንግ-ሬ።
ኪም 24 ሰዓት የሚያገለግለው መጠጥ ቤት እንዳለ ሆኖ በጎን ሌላ ንግድ ያጧጥፏል።
ከዚህ ቀደም እዚህ ገበያ ማዕከል ሌላ መጠጥ ቤት ነበረው። ነገር ግን ወጪ እና ገቢው አልመጣጠን ሲል ነው ሠራተኛ አልባ 'ባር' የከፈተው።
ጥቂት ሕፃናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ላለፉት አስርት ዓመታት የኮሪያ የውልደት መጠን ማሽቆልቆሉ እና የሠራተኞች ክፍያ መጨመሩ እንደ ምክንያት ይቆጠራል።
ደቡብ ኮሪያ በዓለማችን ዝቅተኛ የውልደት መጠን ካላቸው አገራት መካከል ናት። በአውሮፓውያኑ 2023 የውልደት መጠኑ 0.73 ነበር። ነገር ግን ባለፈው ዓመት ወደ 0.75 ከፍ ብሏል።
የሕዝብ ቁጥሩ የተመጣጠነ ሆኖ እንዲቀጥል የውልደት መጠኑ ወደ 2.1 ከፍ ማለት አለበት። ደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲህ ያለ የውልደት መጠን ያየችው በአውሮፓውያኑ 1982 ነው።
ይህ ማለት ለሥራ ወደ ገበያው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እጅጉን እየቀነሰ መጥቷል ማለት ነው። ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ የደቡብ ኮሪያ ዝቅተኛ ክፍያ በየዓመቱ ጭማሪ አሳይቷል።
እንደ ኪም ያሉ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ለሠራተኞቻቸው በሰዓት 7 ዶላር ይከፍላሉ።
"እኔ ሠራተኛ አልባ ባር የከፈትኩት ዝቅተኛ ክፍያው በመጨመሩ ነው። ይህን መቋቋም የምችለው በሁለት መንገድ ነው። በሮቦት አሊያም ሠራተኛ አልባ ሱቅ በመክፈት" ይላል ኪም።
ሮቦት ማሠማራት ብዙ ገንዘብ እና ቦታ ይጠይቃል። ለዚህ ነው ኪም ሰው አልባ አሊያም አውቶሜሽን የተሰኘውን መንገድ የመረጠው።
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ብዙ ሱቆች ሰው አልባ መሆን ጀምሩ። በዚህም ለሠራተኞች የሚከፍሉት ገንዘብ መቆጠብ ሲችሉ በወረርሽኙ ወቅት የነበረውን አካላዊ መራራቅም ጠበቁ ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንዳንዶች እንደሚሉት አዲሱ ትውልድ በተለምዶ "3ዲ" የተባለውን ሥራ መሥራት አይፈልግም። ይህ ሥራ የሚያቆሽሽ፣ አደገኛ፣ ከባድ እና ብዙ የሚጠይቅ ነው ብሎ ያምናል።
እነዚህ ሥራዎች ፋብሪካዎችን፣ ግብርና እና የሸቀጥ ንግድ ሥራዎችን የሚመለከቱ ናቸው። እነዚህ ሥራዎች ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ መጥቷል።
"ወጣቱ ትውልድ ከተማ መኖር ነው የሚሻው። የራሱን ሥራ መፍጠር እንጂ ተቀጣሪ ሆኖ መኖር አይፈልግም። አሊያም ደህና ደሞዝ የሚከፍል የቴክኖሎጂ ሥራን ይመርጣል" ይላሉ ቾ ጁንግ-ሁን።
ቾ የገዥው ፒፕልስ ፓርቲ አባል ሲሆኑ የትምህርት ቋሚ ኮሚቴ ውስጥም አሉበት።
"እኔ እንደ ሌሎቹ ሕግ አውጪዎች አዲሱን ትውልድ መውቀስ አልፈልግም። የመረጠውን ነው የሚያደርገው። ቁጥሮች እንደሚያሳዩት በሚመጡት ዓመታት የሰው ኃይል እጥረት ይጠብቀናል። ከወዲሁ ውሱን የሆነውን የሰው ኃይል በጥንቃቄ ማከፋፈል አለብን" ይላሉ።
የኮሪያ ምጣኔ ሀብታዊ ጥናት ማዕከል እንደሚለው በሚቀጥሉት 20 ዓመታት 43 በመቶ ሥራዎች በማሽን ይተካሉ።
ኩዎን ሚን-ጃይ ብራውኒ የተባለው የሠው አልባ ሱቆች አስተዳዳሪ የሆነው ድርጅት ኃላፊ ነው። ኩባንያውን ያቋቋመው ኮቪድ ማብቃት ሲጀምር ገደማ ነው።
"ሠራተኛ አልባ የሆኑ የልብስ ማጠቢያ፣ አይስ ክሪም፣ ሸቀጣ ሸቀጥ፣ ካፌ እና ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ሱቆችን እናስተዳድራለን" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
ምንም እንኳ ሱቆቹ ሠራተኛ አልባ ቢሆኑም ዕቃዎች ሲያልቁ መተካት፣ ማፅዳት እና ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቃል። የኩዎችን ኩባንያ እኒህን ሥራዎች ያከናውናል።
"ይህንን ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች አሉን። የሱቆቹ ባለቤት ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ አይፈልጉም። በወር 100 አሊያም 200 ዶላር ቢከፍሉን ይመርጣሉ።"
ኩዎን ሥራውን ሲጀምር ሁለት ሱቆች ነበር የሚያስተዳድረው። አሁን ከ100 በላይ ሱቆችን ያስተዳድራል።
ጥቂት ስርቆት
ደቡብ ኮሪያ በጣም ጥቂት የስርቆት ወንጀል ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል ናት። ለዚህም ነው ሰው አልባ ሱቆች ስኬታማ የሆኑት።
"አንዳንድ ሰዎች ሳይከፍሉ ረስተው ይወጣሉ። ነገር ግን በኋላ ደውለው ይከፍሉኛል። ስለ ሌሎች ሱቆች ባላውቅም ወጣት ደንበኞች ዋሌታቸውን እና ስልካቸውን ጠረጴዛ ላይ ትተው ነው የሚንቀሳቀሱት" ይላል ኪም።
ነገር ግን በስርቆት ምክንያት ኪሳራ ሊመጣ እንደሚችል አይክድም። ቢሆንም ስርቆት የተለመደ ስላልሆነ የሚያሰጋ አይደለም።
የቴክኖሎጂ መራቀቅ እንደ ሹፍርና ያሉ ሥራዎችን ከጥቅም ውጪ እንደሚያደርጋቸው ይታመናል።
ደቡብ ኮሪያ ለረዥም ጊዜ ያቀደችውን የሁለት በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማስቀጠል በአውሮፓውያኑ 2032 ዓመት 890 ሺህ ተጨማሪ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል።
የሠራተኛ ማኅበራት እና ሕግ አውጪዎች ይህ ቢያሰጋቸውም እንደ ኪም ያሉ የሠራተኛ አልባ ሱቆች ባለቤቶች ግን ይህ መልካም አጋጣሚ ነው ይላሉ።















