የአየር ጉዞን ይለውጣል የተባለው በሰማይ የሚንሳፈፈው 'የአየር ላይ መርከብ'

ኤርሺፕ

የፎቶው ባለመብት, HAV

የምስሉ መግለጫ, ኤርሺፕ በአየር ተሞልቶ ሰማይ ላይ ይጓዛል

አውሮፕላን አካባቢን ከሚበክሉ ግንባር ቀደም መጓጓዣዎች አንደኛው ነው።

የአየር ላይ ጉዞን ከብክለት ነጻ በሆነ መንገድ ለማድረግ ይረዳል የተባለው አዲስ የመጓጓዣ መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል።

አየር ላይ የሚንሳፈፍ ፊኛ ነው የሚመስለው። መጓጓዣው በእንግሊዘኛው ኤርሺፕ (የአየር ላይ መርከብ) ይባላል።

በአየር ተሞልቶ ሰማይ ላይ ይጓዛል።

የተጓዦች እና የጉዞ አስተናጋጆች መቀመጫ እንዲሁም ቁሳቁስ መጫኛ አብረውት ይንሳፈፋሉ።

አውሮፕላን ዝነኛ ሳይሆን በፊት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ኤርሺፕ ታዋቂ ነበር።

የአየር መጓጓዣ የካርበን ልቀቱን ዜሮ እንዲያደርስ በሚል ለውጦች ለማድረግ እየተሞከረ ነው።

ቀላል የሆኑ ናይለኖችን ለግንባታ ማዋል አንደኛው የለውጡ አካል ነው።

ተቀጣጣዩን ሀይድሮጅን በሂሊየም መተካትም ይጠቀሳል።

ከዚህ ቀደም ሀይዲንበርግ በሚል የተሠራው ተመሳሳይ የጀርመን ኤርሺፕ በአውሮፓውያኑ 1937 መፈንዳቱ ይታወሳል።

ኤርሺፕ ከዚህ ቀደም ተሠርቶ ከነበረው ሀይዲንበርግ ጋር የሚያመሳስለው ቅርጹ እና ሁለቱም ከጋዝ የቀለለ አየር መጠቀማቸው ነው።

ኤርሺፕ በሰዓት የሚጓዘው ከ100 እስከ 300 ኪሎ ሜትር ነው። ይህንን ከጄት ጋር ማነጻጸር አይቻልም።

ኤርሺፕ እንደ መርከብ ወይም ቀላል ባቡር ያለ ነው።

ፈጣን ባይሆንም ጉዞው ያዝናናል።

ከአውሮፕላን ዝቅ ብለው ነው የሚበሩት።

ተጓዠች መስኮት ከፍተው መመልከት ይችላሉ።

ለመጓዝ የሚወስደው ጉልበት አነስተኛ ሲሆን፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ሊጓዝም ይችላል።

የሚያመነጩት በካይ ካርበን ዜሮ ነው።

የአቪዬሽን ባለሙያ እና በአልቦርግ ዩኒቨርስቲ የሚሠራው ቶማስ ቴሰን "አዳዲስ ፈጠራ መሞከራችን ጥሩ ነው። ዘላቂ የሆነው የወደፊት ዓለም ለመፍጠር የተሻለ መንገድ መፈለግ አለብን" ይላል።

"የሚታየኝ ጉልህ ጥቅሙ በአየር ላይ ለረዥም ሰዓት መቆየቱ እና ወደጎን መጓዙ ነው" ሲልም ያክላል።

ኤርሺፕ

የፎቶው ባለመብት, HAV

የምስሉ መግለጫ, የተጓዦችና የጉዞ አስተናጋጆች መቀመጫ እንዲሁም ቁሳቁስ መጫኛ አብረውት ይንሳፈፋሉ

ኤርሺፕ እንደ አውሮፕላን መንደርደሪያ መንገድ አይፈልግም።

ኤርሺፕ የትኛውም ሰፊ ቦታ ላይ ማረፍም ይችላል።

ተፈጥሯዊ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነቶች ሲቋረጡ ሰዎችን ለማትረፍ ይጠቅማል።

የዓለም ትልቁ አውሮፕላን ኤልቲኤ ፓዝፋይንደር 1 በካሊፎርያ የቴክኖሎጂ መንደር ሲልከን ቫሊ ሙከራ እየተደረገበት ነው።

124.5 ሜትር በ20 ሜትር ከፍታ እና ስፋት አለው።

ከሦስት ቦይንት 737 የሚረዝም ነው።

ኤልቲኤ የሚለው ምህጻረ ቃል 'ላይተር ዛን ኤር' ወይም ከአየር የቀለለ የሚለውን ይወክላል።

ወደ አቪዬሽን ገበያው እንደሚገቡ ከሚጠበቁ አንዱ ነው።

መሥራቹ ሰርጊ ቢርን ነው። የጉግል እናት ድርጅት አልፋቤት ፕሬዝዳንት ነው።

ሂልየምን በመጠቀም የካርበን ልቀትን የሚገድቡ አውሮፕላኖች በቀጣይ እንደሚመረቱ ይታመናል።

ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ካርበን የሚለቅ ሞተር ነበር።

ለሰብአዊ እርዳታ እንዲሁም ከአንድ ሥፍራ ወደሌላው ካርጎ ለማዘዋወር ይውላሉ።

መንገድ እና የአውሮፕላን መንደርደሪያ ባይኖርም ጥቅም ላይ ይውላሉ።

የፈረንሳዩ ድርጅት 'ፍላይኒግ ዌልስ' አካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የኤሌክትሪክ ሞተርን በማዳቀል አዳዲስ ፈጠራዎች እየሞከረ ነው።

ኤርሺፕ

የፎቶው ባለመብት, Ocean Sky Cruises

የምስሉ መግለጫ, ኤርሺፕ እንደ አውሮፕላን መንደርደሪያ መንገድ አይፈልግም።

'ሀይብሪድ ኤር ቪሄክልስ' የተባለው የዩናይትድ ኪንግደም ተቋም የኤሌክትሪክ ሞተር እና ሂልየም ጋዝን ይጠቀማል።

በተለይም ሰዎችን በጅምላ ለማጓጓዝ የሚውል አማራጭ እስከሚገኝ ድረስ የአየር ጉዞ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚያደርገው ጉዞ ረዥም ይሆናል።

የኤሌክትሪክ ሞተር 'ሰስቴነብል አቪዬሽን ፊውል' ወይም ኤስኤኤፍ አንደኛው መንገድ ነው።

የኤችኤቪ የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊ ሀና ካኒንግሀም "ኤርላንደር ያልገናኙ ሰዎችን የሚያስተሳስር ነው" ትላለች።

ኤርላንደር 10 በሂሊየም አማካይነት በመጓዝ ግንባር ቀደሙ ነው።

"አውሮፕላን ማረፊያ እና ሰፊ መሠረተ ልማት አያስፈልግም። ለጥ ካለ ሜዳ ተነስቶ መብረር ይቻላል። እርስ በእርሳቸው ያልተገናኙ አካባቢዎችን ያስተሳስራል። ለምሳሌ በስኮትላንድ ያሉ ተራራማ አካባቢዎችን ማገናኘት ይቻላል" ስትል ታስረዳለች።

ኤርላንደር 10 አራት የኬሮሲን ሞተር አለው። 90 በመቶ የካርበን ልቀትን ይቀንሳል።

በአውሮፓውያን 2030 ኤችኤቪ በሃይድሮጅን የተሞሉና ከካርበን ልቀት ነጻ የሆኑ የኤሌክትሪክ ሞተር የተገጠመላቸው የአየር መጓጓዣዎችን እውን ያደርጋል።

በሰዓት እስከ 130 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ።

እስከ 90 ሰዎች ይጭናሉ።

የተጓዦች አውሮፕላን በሰዓት 770 አስከ 930 ይጓዛል። ሆኖም ግን አካባቢን ይበክላል።

ኤርሺፕ

የፎቶው ባለመብት, HAV

የምስሉ መግለጫ, ኤርሺፕ የትኛውም ሰፊ ቦታ ላይ ማረፍም ይችላል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤችኤቪ ባለፈው ዓመት ከስፔን አውሮፕላን ማረፊያ ኤር ኖስትረም ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

በስምምነቱ መሠረት ኤርላንደር እስከ 2028 ድረስ 20 የመንገደኞች አውሮፕላን ይሠራል።

የስፔን ተራራማ አካባቢዎችን ማዳረስ ዋነኛ ዕቅዳቸው ነው።

በአራት ዓመታት ውስጥ የበረራ ፈቃድ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአቪዬሽን ባለሙያ እና በአልቦርግ ዩኒቨርስቲ የሚሠራው ቶማስ ቴሰን እንደሚለው፣ እንደ አውሮፕላን ያህል አየር የተሞሉ መጓጓዣዎች ገናና ሊሆኑ አይችሉም።

"አውሮፕላንን የምንጠቀመው በዋነኛነት ፈጣን ስለሆነ ነው። ኤርሺፕ የሚጓዘው በመኪና ፍጥነት ነው። እንደ መርከብ ብለን ልንወስዳቸው እንችላለን። አውሮፕላንን ሊተኩም አይችሉም" ሲል ያስረዳል።

መስኮት ከፍቶ መመልከት አስደሳች የጉዞው አካል እንደሚሆን ግን ሳይጠቅስ አላለፈም።

በጀርመን እስከ 500 ዩሮ በመክፈል ለ45 ደቂቃ በኤርሺፕ መጓዝ ይቻላል።

ሌላው በኤርሺፕ ምርት ስሙ የሚጠራው 'ኦሽን ስካይ ክሩዝ' ነው።

ቅንጡ በአየር የተሞሉ መጓጓዣዎች እያቀረበ ይገኛል።

አሁን ላይ ጉዞው ከሳቫልባርድ እስከ ኖርዝ ፖል ሲሆን፣ ሁለት ቀናት የሚወስድ ጉዞ ነው።

በረዷማውን አካባቢ በሰፋፊ መስኮት መቃኘት ይቻላል።

እስከ 200 ሺህ ዶላር የሚጠይቁ ጉዞዎችም አሉ።

በጣም ተፈላጊ ስለሆኑ መቀመጫ ለማግኘት መጠበቅ ያስፈልጋል።

ሌሎች ታዋቂ እየሆኑ ከመጡ ጉዞዎች መካከል ከናሚቢያ ስኬለተን ዳርቻ እስከ ቪክቶሪያ ፏፏቴ ድረስ ያለው ይጠቀሳል።

ኤልቲኤ ቢያንስ ለሰብአዊ አገልግሎት የሚውሉ በአየር የተሞሉ መጓጓዣዎችን ማቅረብ ችሏል።

ወደ መንገደኞች መጓጓዣ እስከሚሸጋገር ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

ኤርሺፕ ለአካባቢ ጥበቃ ሲባል የሚወሰድ ዋነኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

የኤችኤቪ የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊ ሀና ካኒንግሀም "ዓለምን እየዞርን ማየት የምንፈልግ ከሆነ ዓለማችንን ማጥፋት የለብንም" ትላለች።