ልዑል ሃሪ ወንድሜ ልዑል ዊሊያም አካላዊ ጥቃት አድርሶብኛል ማለቱ አነጋጋሪ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደም ንጉሥ ልጅ ልዑል ቻርልስ በቅርቡ ይወጣል በተባለ መጽሐፉ ላይ ታላቅ ወንድሙ ልዑል ዊሊያም አካላዊ ጥቃት አድርሶብኛል ማለቱ አነጋጋሪ ሆነ።
ልዑል ሃሪ በግል ሕይወቱ ዙሪያ የጻፈው ‘ስፔር’ በተሰኘ መጽሐፉ ታላቅ ወንድሙ አካላዊ ጥቃት እንደሰነዘረበት መግለጹን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው መጽሐፍ ሃሪ “አንገቴን ይዞ፤ የአንገት ጌጤን በመበጠስ መሬት ላይ ዘርሮኛል” ስለማለቱ ተዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ወንድማማቾች በሃሪ ባለቤት ሜጋን ዙሪያ ተጨቃጭቀው እንደነበረ በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል ተብሏል።
የልዑል ዊሊያም ይፋዊ መኖሪያ ቤት ኪንግስተን ቤተ-መንግሥትም ሆነ የንጉሥ ቻርልስ መኖሪያ ቤት ባኪንግሃም ፓላስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመሰጠት ተቆጥበዋል።
ንጉሥውያን ቤተሰቡ አወዛጋቢ ነገሮች ሲከሰቱ መልስ ባለመስጠት ነገሮችን የማረጋጋት መንገድን እየመረጡ ነው ተብሎ ይገመታል።
የልዑል ሃሪ መጽሐፍ እስከ ፊታችን ማክሰኞ ለሕትምት የማይበቃ ቢሆንም፤ ዘ ጋርዲያን ግን የመጽሐፉ ቅጂ እጄ ገብቷል ብሏል።
ቢቢሲ ግን ስፔር የተሰኘውን የመጽሐፍ ቅጂን አልተመለከተም።
እንደ ዘ ጋርዲያን ከሆነ በወንድማማቾቹ መካከል አለመግባባቱ የተከሰተው እአአ 2019 ነው።
በዚህ መጽሐፍ ልዑል ዊሊያም ታናሽ ወንድሙ አፍሪካ አሜሪካዊቷ ሜጋንን የማግባቱ ዕቅዱ እንዳልተዋጠለት ሃሪ ጽፏል።
ዊሊያም ሜጋንን ‘አስቸጋሪ’፣ ‘ሥነ-ምግባር የጎደላት’ እና ‘አጸያፊ’ ብሎ ስለመግለጹ ተዘግቧል።
ልዑል ሃሪ ወንድሙ መትቶ ሲጥለው የውሻ መመገቢያ ሳህን ላይ መውደቁን እና ሳህኑ ተሰባብሮ ሰውነቱን እንደወጋው ገልጿል።
“የውሃ ብርጭቆ አስቀመጠ፤ በሌላ ስም ጠራኝ እና ወደ እኔ መጣ። በጣም በፍጥነት ነው የሆነው። አንገቴን ያዘኝ. . . መሬት ላይ ጣለኝ። የውሻ መመገቢያ ሳህን ላይ ወደቅኩ፤ ከጀርባዬ ሆኖ ተሰባበሮ ስብርባሪው ወገኝ። በወደቅኩበት ዞሮብኝ ባለሁበት ቆየው፤ ከዚያ ተነስቼ ቆምኩ እና እንዲወጣ ነገርኩት” ሲል ጽፏል።
ሃሪ በታላቅ ወንድሙ አካላዊ ጥቃት ደርሶበት እንደነበረ መግለጹ በንጉሥውያን ቤተሰቡ መካከል ጥልቅ የሆነ አለመግባባት መኖሩን ያሳየ ነው።
በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል ያጋጠመው ክስተት ‘አካላዊ ጥቃት’ እንጂ ‘ድብድብ’ ተብሎ ያልተገለጸው ሃሪ ጥቃት ሲሰነዘርበት ምላሽ ባለመስጠቱ ነው።
ሃሪ በመጽሐፉ በወቅቱ በብስጭት ውስጥ የነበረው ታላቅ ወንድሙ መልሶ እንዲመታው ቢጠይቀውም ሃሪ ያን ከማድረግ መቆጠቡን ገልጿል።
ከክስተቱ በኋላ ልዑል ዊሊያም መጸጸቱን፤ ይቅርታ መጠየቁንም ልዑል ሃሪ ጽፏል።
የመጽሐፉ አሳታሚ 'ፔንጉይን ራንደም ሐውስ' በሃሪ መጽሐፍ ይህ ስለመገለጹ እስካሁን ባያረጋግጥም፤ ሃሪ ግን ከታላቅ ወንድሙ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት እንደሌለው ከዚህ በፊት ተናግሯል።
ኔትፍሊክስ ላይ እየታየ በሚገኘው የሃሪ እና የሜጋን ዘጋቢ ፊልም ላይ ሃሪ ወንድሙ፣ አባቱ (አሁን ንጉሥ የሆኑት) እና በሞት የተለዩት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ ተሳታፊ የነበሩበትን ስብሰባ ‘አስፈሪ’ ሲል ገልጾታል።
እአአ 2020 ወንድሙ ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲጮህበት እንደነበረ፤ አባቱ ደግሞ ስለ እርሱ እውነት ያልሆኑ ነገሮችን ሲናገሩ ንግሥት ኤልዛቤጥ ምንም ከመናገር ተቆጥበው ሁኔታውን ሲመለከቱ ነበር ብሏል።












