የ6 ወር ሕጻን መግደልን ጨምሮ በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ የኬንያ ፖሊስ አባላት ክስ ተመሰረተባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 በኬንያ በተካሄደው ምርጫ ወቅት የ6 ወር ጨቅላ ሕጻንን መግደልን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች እንደተሳተፉ የተጠረጠሩት 12 የኬንያ ፖሊስ አባላት በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ክስ ቀረበባቸው።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ጠንካራ የድጋፍ መሰረት ባላቸው እና በምዕራብ ኬንያ በምትገኘው ኪሱሙ ግዛት በወቅቱ በተፈጸሙ አስቃቂ ጥቃቶች ከፍተኛ ባለስልጣናት ኃላፊነት እንደሚወስዱ የኬንያ ዋና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገልጸዋል።
የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኃላፊው ኖርዲን ሃጂ፣ በኪሱሙ የተፈጸሙት ጥቃቶች ድንገት የተከሰቱ ሳይሆን ቀደም ብለው የታቀዱ እና ክስ በቀረበባቸው የፖሊስ አባላት የተቀነባበሩ ናቸው ብለዋል።
ኃላፊው የተጠርጣሪዎቹን ማንነት ባይገልጹም የፖሊስ መኮንኖቹ ኃላፊነታቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ግድያ፣ ማሰቃየት እና በመድፈር ወንጀሎች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
የ2017ቱ የኬንያ ምርጫ በቀድሞው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ዋነኛ ተፎካካሪያቸው በነበሩት ራይላ ኦዲንጋ መካከል ብርቱ ትንቅንቅ የታየበት ነበር።
ነሐሴ ወር ላይ በተካሄደው በዚህ ምርጫም ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ተፎካካሪያቸውን አሸንፈው ነበር።
ይሁን እንጂ ያገኙት ድል “ምርጫው ያልተስተካከለ አሰራር ታይቶበታል” በሚል በአገሪቷ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎ ጥቅምት ወር ላይ ድጋሜ ምርጫ ተካሂዷል። በዚህም ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፍ ችለዋል።
ምርጫውን ተከትሎ በአገሪቷ በተፈጠረው አለመረጋጋት በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችም በተፈጠረው ግጭት ላይም ፖሊስ በተቃዋሚ ደጋፊዎች ላይ የተጠቀመው ኃይል ከመጠን ያለፈ ነበር ሲሉ ይወቅሳሉ።












