ኡሁሩ ኬንያታ በአገራቸውና በአካባቢው አገራት እንዴት ይታወሳሉ?

ኡሁሩ ኬንያታ እየሳቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ጋር ተያይዞ በሚነሱ የሰላም ድርድሮች ላይ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሌሎች የአፍሪካ መሪዎች በበለጠ ሲጠቀሱ ይሰማል።

በተለይም የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ወገንተኝነትን አሳይተዋል በሚል በትግራይ ኃይሎች የሚወቀሱ ሲሆን፣ በትግራይ ያለውን ሁኔታ እንደተከታተሉት የተነገራላቸው ኡሁሩም አደራዳሪ ይሁኑ ሲሉም ተሰምተዋል።

ከአምስት ወራት የተኩስ አቁም አዋጅ በኋላ ያገረሸው ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ የተለያዩ ተቋማትና አገራት ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ኡሁሩ ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ምን አይነት ሚና ሊኖራቸው ይችል ይሆን የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተው ነበር።

በአሁኑ ወቅት ይህ ጥያቄ ምላሽ ያገኘ ሲሆን አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ኡሁሩ የሚያከናውትን ተግባር እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል። 

ሩቶ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና (ግሬት ሌክስ) ሰላም ለማምጣት የሚያስመሰግን ተግባር አከናውነዋል ብለዋል።

“በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ለማጠናከር ቁርጠኛ ነኝ” ያሉት አዲሱ ፕሬዝዳንት ሩቶ፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የጀመሩትን ሰላም የማምጣት ጥረት ለመቀጠል ተስማምተዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ያከናወኑት ተግባር እንዳለ ሆኖ በአገራቸው ኬንያስ እንዴት ይታወሳሉ?

ወቅቱ ከአራት ዓመት በፊት ነበር። አንድ ተማሪ የኬንያውን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሥልጣን ሲሰናበቱ እንዴት መታወስ ይፈልጋሉ? ብሎ ጠየቃቸው። ለአሁሩ ያልጠበቁት ነገር ቢሆንም ሁለት ጉዳዮች ላይ አትኩሮት ሰጥተው ተናግረዋል።

“አንደኛ አንድነቱን የጠበቀ፣ የተቀናጀ ማኅበረሰብን ማምጣት ችያለሁ። ሁለተኛ በሙስና ላይ የከፈትነውን ጦርነት ማሸነፍ ችለናል” ሲሉም ከፍተኛ ጭብጨባ ነው የጠበቃቸው።

ከሁለት የሥልጣን ዘመናቸው በኋላ መንበራቸውን ለቀድሞ አጋራቸውና ለአሁኑ ተቃናቃኛቸው ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን ባስረከቡበት ወቅት አሁሩ የጠቀሷቸውን ስኬቶች አሳክተው ይሆን? ሌሎች የሚጠቀሱባቸው ተግባራትስ ምን ይሆኑ?

ኡሁሩ ለአገራዊ አንድነት ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ ወስደዋል ከሚባልላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በአውሮፓውያኑ 2018 ከተቃዋሚ መሪ እና ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ጋር ፖለቲካ እርቅ ማሳያ የተባለው መጨባበጥ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2017 የተደረገው ምርጫ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎ በድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን፣ በዚህም ድጋሚ ምርጫ ኦዲንጋ ሳይሳተፉ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ራሳቸውን የሕዝብ መሪ በማለት የይስሙላ ቃለ ሐላ ሥነ ሥርዓት አካሂደው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ለወራት የዘለቀ አለመረጋጋት የተከተለ ሲሆን፣ የሁለቱ ፖለቲከኞች “የእጅ መጨባበጥ” ይህንን እንዲቋጭ አድርጎታል።

ነገር ግን የኡሁሩ እና የኦዲንጋ ስምምነት በወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩት ዊሊያም ሩቶ በጥሩ መልኩ አልታየም።

ዊሊያም ሩቶ የምግብ ዋስትናን የማሳደግ፣ ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎትን ለማስፈን፣ መኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለማሳደግ የነበራቸውን ትልልቅ አጀንዳዎች እንዳይሳኩ ምክንያት ሆኗል ይላሉ የሁለቱ ፖለቲከኞች ጥምረት።

ይህንንም ተከትሎ የኡሁሩ ኬንያታ እና የዊሊያም ሩቶ ግንኙነት የሻከረ ሲሆን፣ ኡሁሩ ለዊሊያም ሩቶ ያላቸውን ድጋፍ በማቆም በምትኩ ተቀናቃኛቸው የነበሩትን ራይላ ኦዲንጋን በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል።

በኡሁሩ ኬንያታ እና በምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ መካከል ያለው ውጥረት ከምርጫው በኋላም ቀጥሏል። ዊሊያም ሩቶ በመመረጣቸው ደስተኛ አለመሆናቸውን የተናገሩት ኡሁሩ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ያስተላለፉትም ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሰየማቸው አንድ ቀን በፊት ነው።

ኡሁሩ
ኡሁሩ ኬንያታና ራይላ ኦዲንጋ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኡሁሩ ኬንያታ አስበውት የነበረው አንድነት ይህንን ላይሆን ቢችልም፣ በአውሮፓውያኑ 2007 የተከሰተውን የምርጫ ውዝግብ ተከትሎ በነበረ የብሔር ግጭት 1200 ሰዎችን በሞቱባትና እንዲሁም በርካታ ሺዎች በተፈናቀሉባት አገር ወሳኝ ነበር ተብሏል።

በተለይም በቅርቡ የነበረው ምርጫ በሰላም መጠናቀቅ ተንታኞች እንደሚያምኑት ኡሁሩ የራሳቸው ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ ቢሸነፉም አንድነትን ለማምጣት እና የጋራ ማኅበረሰብ ለመገንባት ያደረጉትን ጥረት አሳክቷል።

የሁለቱ ፓለቲከኞች መጨባበጥ ሁሉም የሚሳተፉበት እና የመገለልም ስሜትን ያስወገደ እንደሆነ በማሲንዴ ሙሊሮ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጽሁፍ እና ኮሚዩኒኬሸን ፕሮፌሰር የሆኑት ኤጋሪ ካባጂ ይናገራሉ።

ሆኖም በኡሁሩ እና በራይላ ኦዲንጋ መካከል የተደረገው እርቅ በተቃዋሚ ዘንድ ክፍተትን ፈጥሯል።

የመንግሥትን ኃላፊነት የሚቆጣጠር፣ መንግሥት ያልተገባ ተግባር ሲፈፅም የሚፈትሽ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር ምክንያት ሆኗል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኟ ኔሪማ ዋኮ ኦጂዋ።

ይህም ኡሁሩ ኬንያታ ሙስናን እና የሕዝብ ሃብት ምዝበራን ማስቆም ያለመቻላቸው ሚና ሳይጫወት እንዳልቀረም ተንታኝዋ ያስረዳሉ።

ለራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያካሂዱበት ወቅት ሙሰኞችን ለመቆጣጠር ችላ ብለው እንደነበር አምነዋል።

እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2012 አገሪቱ በየቀኑ 2 ቢሊዮን የኬንያ ሸልንግ (17 ሚሊዮን ዶላር) በሙስና በየቀኑ ታጣለች ብለዋል።

ይህንንም አስመልክቶ “ፕሬዝዳንቱ ካወቁ በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን አንድ ነገር አላደረጉም? በርካታ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ቢሆኑም ፍርድ ማግኘት አልተቻለም” ሲሉ በኮዲ አፍሪካ የግብር ኤክስፐርት የሆኑት ኒኪል ሂራ ይጠይቃሉ።

ቀላል ባቡር

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኡሁሩ አስተዳደር በአገሪቱ ውስጥ ግድቦች እና ስታዲየም በመገንባት፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርጋታ፣ የናይሮቢ ፈጣን የባቡር መንገድን ጨምሮ የባቡር ሃዲዶች ግንባታ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል።

እነዚህ ኢንቨስትመንቶች የተከናወኑት በከፍተኛ ብድር ሲሆን ፈሶባቸዋል የተባለው ወጪም ጥያቄ አስነስቷል።

ለምሳሌ በቻይና የተገነባው ከሞምባሳ እስከ ናይሮቢ የተዘረጋው የባቡር መስመር 3.2 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን፣ ይህም በጎረቤት አገራት ታንዛንያ እና ኢትዮጵያ ከተከናወኑ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ጋር ሲነፃፀሩ ዋጋው እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

በቀጣዮቹ ዓመታት መመለስ ያለባት ብድርም ጣራ እንዲነካ አድርጎታል።

በአውሮፓውያኑ 2021 መገባደጃ ላይ የአገሪቱ እዳ 72.6 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ውስጥ 68 በመቶ ነው። ኡሁሩ በአውሮፓውያኑ 2013 ወደ ሥልጣን ሲመጡ 38 በመቶ ነበር።

የምሥራቅ አፍሪካ ግዙፉን ኢኮኖሚ ለማፋጠን አገሪቱ አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን መገንባት እንደሚያስፈልጋት ታዛቢዎች ቢስማሙም፣ የገንዘብ አያያዝ በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም የሚለው ስጋት ፈጥሯል።

ከፖሊሲዎች ባሻገር የኡሁሩ ቀለል ያለ ስብዕና በርካቶች የሚናፍቁት ነው። ፕሬዚዳንቱ በአደባባይ ላይ በሚታዩበት ሁሉ ከሰዎች ጋር እንደ ጓደኛ ነው የሚያወሩት።

ኡሁሩ ጥበቃዎቻቸው ራቅ ብለው እየተከታተሏቸው በናይሮቢ ጎዳናዎች ላይ በእግራቸው ሲዘዋወሩ ማየት፣ ኛማ ቾማ ብለው ኬንያውን የሚጠሩትን የሥጋ ጥብስ በገበያ ላይ በአካባቢው ሰዎች ተከብቦ መብላት እና የጎልፍ ጨዋታን ከታዳሚዎች ጋር እያወሩ ይከታተሉ ነበር።

ለህፃናት እና ለታዋቂ ሰዎችም ቤተ መንግሥታቸው በመጋበዝና እንዲጎበኙ በማድረግ ሥልጣን ብቻ ያላቸው ብቻ የሚገቡበት የሚለውንና እንደ ብርቅና ድንቅ የነበረውን ሁኔታ ለመሻር ሞክረዋል።

በተጨማሪም ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ከተጻፈው ውጪ በመውጣት ለሕዝብ ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለውን ፍንጭም ይሰጡ ነበር።

ግራፊክስ
ኡሁሩ ኬንያታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምንም እንኳን በአገር አቀፍ ደረጃ ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎትን ለመዘርጋት የነበራቸው ሰፊ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባይሆንም፣ የሆስፒታል አልጋዎች አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል፤ እንዲሁም አዳዲስ ሆስፒታሎች ተገንብተዋል።

ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኬንያ የምትታይበት ሁኔታ ባለፉት አስር አመታት ተሻሽሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተዘዋዋሪ ሊቀ መንበርነቱን የተረከበችው ኬንያ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያደረገችውን ወረራ አውግዛለች።

በተባበሩት መንግሥታት የኬንያ አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ በማኅበራዊ ሚዲያ በሰፊው ባሰራጩት መግለጫቸው፣ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ያሳለፈችውን ታሪክ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ካደረገችው ወረራ ጋር አነጻጽረውታል።

በሩሲያና እና በዩክሬን ግጭት ውስጥ ቀጥታ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት ዝምታን መርጠዋል።

ኡሁሩ ኬንያታ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ሊቀመንበር በመሆን በኢትዮጵያ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭቶችን ለመፍታት አደራዳሪ ሆነውም ሰርተዋል።

በአጠቃላይ ኬንያ በኡሁሩ ኬንያታ የሥልጣን ዘመን ያልተጠበቁ ተግዳሮቶች ገጥሟት ነበር። ከእነዚህም መካከል በናይሮቢ እና በሌሎች ቦታዎች ታጣቂዎች ያደረሱት ጥቃት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም በከፊል በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተከሰተው የኑሮ ውድነት ይጠቀሳሉ።

ኡሁሩ ሥልጣናቸውን በሚያስረክቡበት ወቅት ለቀጣዩ መንግሥት የቤት ሥራዎች የሆኑት በምርጫ ዘመቻ ወቅት ተወዳዳሪዎቹ ቃል የገቡት የዜጎችን አንገብጋቢ ችግሮች መፍታት ነው።

ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ የሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት መጨመርን የሚጠቀስ ሲሆን በነሐሴ ወር የዋጋ ግሽበት ወደ 8.5 በመቶ ከፍ ብሏል።