ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የመረጧቸው ተተኪ ባለማሸነፋቸው እንዳዘኑ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ሥልጣናቸውን ለቀጣዩ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በደስታ እንደሚያስረክቡ ቢናገሩም የመረጧቸው ተተኪ ራይላ ኦዲንጋ አገሪቱን ለመምራት የተሻሉ ነበሩ ብለዋል።
“ሥልጣኔን ፈገግ ብዬ አስረክባለሁ ምክንያቱም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዬ ነው፤ ነገር ግን መሪዬ ባባ ናቸው።" ሲሉ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ራይላ ኦዲንጋን በቅፅል ስማቸው በመጥራት አሞካሽተዋቸዋል።
አክለውም “ አገሪቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የነበረውን ዕድል ነው የተከላከላችሁት እንጂ ራይላን አይደለም የከለከላችሁት” በማለት በምርጫው ውጤት የተሰማቸውን ኃዘን ገልጸዋል።
ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ያቀረቡት ተቃውሞ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል።
በመሆኑም ቀጣዩ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ያረጋገጡት ዊሊያም ሩቶ በመጪው ማክሰኞ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ እስካሁን ለምክትላቸው የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ባያስተላልፉም የሥልጣን ሽግግሩን በተመለከተ በትናንትናው ዕለት ውይይት አድርገዋል።
ሁለቱ መሪዎች ሐሙስ ፓርላማው ከመከፈቱ በፊት ከየፓርቲዎቻቸው ጋር ተገናኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ፣ ራይላ ኦዲንጋን እጩ ፕሬዚዳንት አድርጎ የነበረው የአዚሚዮ ጥምረት ሊቀመንበር ናቸው።
ሁለቱም ወገኖች የሁለቱን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤነት እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ስትራቴጂ እየነደፉ ነው።
ሁለቱም ፓርቲዎች በፓርላማ ውስጥ አብላጫ ድምፅ አላገኙም።
ተመራጩ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ወሳኝ የሆኑ ፖሊሲዎችን ለማሳለፍ፣ የካቢኔ እጩዎችን፣ ዋና ጸሐፊዎችን፣ አምባሳደሮችን እና ከፍተኛ ኮሚሽነሮችን ለመሾም አብላጫ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።












