በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ኬንያታ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ፕሬዝዳንት ሩቶ ተናገሩ

አዲሱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ (ግራ) እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ (ቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ (ግራ) እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ (ቀኝ)

አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚያከናውኑትን ተግባር እንደሚቀጥሉ ተናገሩ።

ዊሊያም ሩቶ ዛሬ የአገሪቱ አምስተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐለ ከፈጸሙ በኋላ የአስተዳደራቸውን ዋና ትኩረቶች በማስመልከት ባደረጉት ንግግር ነው ይህንን የገለጹት።

ሩቶ በዚህ ንግግራቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና (ግሬት ሌክስ) ሰላም ለማምጣት የሚያስመሰግን ተግባር አከናውነዋል ብለዋል።

“በኢትዮጵያ እና በታላለቅ ሐይቆች ቀጠና የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ለማጠናከር ቁርጠኛ ነኝ” ያሉት አዲሱ ፕሬዝዳንት ሩቶ፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የጀመሩትን ሰላም የማምጣት ጥረት ለመቀጠል ተስማምተዋል ብለዋል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ተዋጊ ኃይሎችን ከማደራደር ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ የኡሁሩ ኬንያታ ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

የምሥራቅ አፍሪካዋ የተረጋጋች አገር ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ ኬንያታ በሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸው ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት ደም አፋሳሹ ጦርነት በፖለቲካዊ ውይይት መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ሲዘገብ ቆይቷል።

በተለይ የትግራይ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር በሚደረገው ድርድር ከአፍሪካ ኅብረት ይልቅ ዛሬ ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያሸማግሏቸው በተደጋጋሚ በይፋ ጠይቀው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ለሚካሄደው ጦርነት መፍትሔ በመፈለጉ በኩል የአፍሪካ ኅብረት ቀዳሚው አሸማጋይ ሊሆን እንደሚገባ አቋሙን ማሳወቁ ይታወሳል።

ከቀናት በፊት የትግራይ አመራሮች ቀደም ሲል ሲያቀርቡት የነበረውን የኡሁሩ ኬንያታ የአሸማጋይነት ሚና በመተው በአፍሪካ ኅብርት ጥላ ሥር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ለወራት ጋብ ብሎ ቆይቶ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መልሶ ያገረሸ ሲሆን፣ አሁንም ተፋላሚዎቹ ውይይት እንዲጀምሩ ከተለያዩ ወገኖች ጥሪ እየቀረበላቸው ነው።

ኬንያታ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳን በሚያጠቃልለው የታላላቅ ሐይቆች ቀጠና ላለው የደኅንነት እና የፀጥታ ችግር መፍትሔ በማፈላለግ ሲሳተፉ ቆይተዋል።

በተለይ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሕገ-ወጥ የተፈጥሮ ሐብት ንግድ ጋር በተያያ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው።

በኡጋንዳ እና ሩዋንዳም መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው። ከጥቂት ዓመታት ሩዋንዳ የሙሴቬኒ መንግሥት የፖል ካጋሜን ከሥልጣን ማስወገድ የሚፈልግ ታጣቂ ቡድንን እየደገፈ ነው በማለት ድንበር ዘግታ እንደነበረ ይታወሳል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ዛሬ ለአስር ዓመታት የቆዩበት የፕሬዝዳንትነት መንበራቸውን በይፋ ካስረከቡት ኬንያታ ጋር መወያየታቸውን የገለጹት ሩቶ፣ ኬንያታ በጀመሩት የሰላም ጥረት ለመቀጠል ፈቃደኛ ሆናቸውን እንዳረጋገጡላቸው አመልክተዋል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በዛሬው ንግግራቸው “ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ ሕዝብን በመወከል እነዚህን ንግግሮች ለመምራት ተስማምተዋል። ሊረዱን እና ሊደግፉኝ ፍቃደኛ ስለሆኑ አመስግንዎታለሁ” ብለዋል።

በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሲመተ በዓል ላይ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ የታላላቅ ኃይቆች መሪዎች ተገኝተዋል።

የ55 ዓመቱ አዲሱ ፕሬዝዳንት ባለፉት ዓመታት ኬንያን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲመሩ ቆይተዋል።

ከሳምንታት በፊት በተካሄደው እና ከባድ ፉክክር ታይቶበት በነበረው ምርጫ ሩቶ አሸናፊ የሆኑት ተቀናቃኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን በጠባብ ልዩነት ካሸነፉ በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንት ሩቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጤቱ የጸደቀውን ምርጫ ያሸነፉት 50.5 በመቶ ድምጽ አግኝተው ሲሆን፣ ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ የ48.8 በመቶውን የመራጭ ድጋፍ አግኝተዋል።