ከ19 ዓመታት በኋላ የተፋለመው የዓለማችን ታላቁ ቦክሰኛ ታይሰን ተሸነፈ

ዝነኛው ቦክሰኛ ማይክ ታይሰን እና ዩቲዩበሩ ፖል በፍልሚያ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማይክ ታይሰን በአጠቃላይ በውድድሩ ማሳረፍ የቻለው 18 ቡጢዎችን ብቻ ነበር።

ከ19 ዓመታት በኋላ የተፋለመው የዓለማችን ታላቁ እና የሁለት ጊዜ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮናው የ58 ዓመቱ ማይክ ታይሰን በ27 ዓመቱ ጃክ ፖል ተሸነፈ።

ከዩቲዩበርነት ፊቱን ወደ ቦክስ ውድድር ያዞረው ጃክ ፖል ማይክ ታይሰንን በከፍተኛ ልዩነት ነው ያሸነፈው።

በተጋጣሚዎቹ መካከል 31 ዓመታት የዕድሜ ልዩነት በታየበት በዚህ አወዛጋቢ የቡጢ ፍልሚያ ጃክ ፖል 80-72፣ 79-73 እና 79-73 በሆኑ ነጥቦች ነው ታይሰንን የረታው።

ታይሰን በ70 ሺህ የቦክስ አድናቂዎቹ እና በኔትፍሊክስ በተከታተሉ ሚሊዮን ተመልካቾች ፊት በቴክሳስ በተካሄደው ፍልሚያ በሰፋ የነጥብ ልዩነት በመሸነፍ የቦክስ አሻራው ላይ ጥላ አጥልቷል።

ታይሰን የ58 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ለ19 ዓመታት በሙያው ሳይወዳደር ነበር የቆየው።

የ27 ዓመቱ ፖል ግን የቦክስ ጀማሪ ቢሆንም ወጣት እና ስፖርተኛ ነበር።በዚህም ምክንያት በስምንት ዙር የሁለት ደቂቃ ዙሮች ውድድር ታይሰንን በሰነዘራቸው ከባድ ቡጡዎች በሰፋ ልዩነት አሸንፎታል።

የ58 ዓመቱ ታይሰን በፍልሚያው ወቅት የድሮው ቀልጣፋነቱ ያልታየበት ሲሆን ንቃት የሌለው እና ዘገምተኛ ሆኖ ነበር የተስተዋለው።

ከግጥሚያው በፊት የጀግና አቀባበል የተደረገለት ታይሰን፣ ውድድሩ ወደ ማጠናቀቂያው ሲቃረብ ግን ብዙ ጉምጉምታዎችና ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።

የተወሰኑ ደጋፊዎችም ዳኞች ነጥቡን ይፋ ከማድረጋቸው ቀድመው ነበር የወጡት።

ቀደም ብሎ የውድድሩ ሕጋዊነት እና ሁለቱ ተፋላሚዎች ምን ያህል ውድደሩን ከቁምነገር ይቆጥሩታል የሚሉ ጥያቄዎች የነበሩ ቢሆንም ታይሰን “ለመፋለም ወደ ሥፍራው እንዳመራ” ተናግሯል።

ከፍልሚያው በኋላ በነበረው ለታይሰን ምቹ ባልሆነች ቅፅበት [በስምንተናው ዙር ሲሸነፍ] የፓልን ወንድም ሎጋንን ጠርቶ ድጋሜ ሊገጥመው እንደሚችል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሆኖም በሁሉም ዙር ግጥሚያው ታይሰን በአጠቃላይ ማሳረፍ የቻለው 18 ቡጢዎችን ብቻ ሲሆን ፖል ደግሞ 78 ሰንዝሯል።

ፖል ዝነኛ የሆነው በኦንላይን በሚለቃቸው የፕራንክ ቪዲዮዎች ሲሆን ወደ ቦክሱ ዓለም ከመቀላቀሉ በፊት 70 ሚሊዮን ተከታዮች ነበሩት።

ፖል እስካሁን 11 ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎች ያደረገ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከቶሚይ ፈሪ ጋር በነበረው ፍልሚያ ብቻ ነበር የተሸነፈው።ከሜክሲኳዊው ኮከብ ሳኡል ካኖሎ አልቫዝ ጋር ለመጋጠም ያለውን ፍላጎትም በድጋሜ ገልጿል።

የዓለማችን ዝነኛ ቦክሰኛ ማይክል ጄራርድ ታይሰን በአውሮፓውያኑ ከ1985 እስከ 2005 ባደረጋቸው 56 ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎች ውስጥ በ6ቱ ብቻ ነበር የተሸነፈው።

ማይክ ታይሰን ለመጨረሻ ጊዜ ደንበኛ የቦክስ ግጥሚያ አደረገ የሚባለው እንደ አውሮፓውያኑ በ2005 ነበር። በዚያ ውድድር ላይ በአየርላንዳዊው ተወዳዳሪ ኬቪን ማክብራይድ ክፉኛ ተደብድቦ ነበር።

እስካሁን ታይሰን ካደረጋቸው 57 የቡጢ ፍልሚያዎች የአሁኑ 7ኛው ሽንፈቱ ነው።

ማይክ ታይሰን የዓለም የከባድ ሚዛንን ሻምፒዮና የሆነው ገና በ20 ዓመቱ ነበር።ይህም የሆነው በፈረንጆቹ በ1986 ትሪቨር በርቢክን ማሸነፉን ተከትሎ ነበር።