ለኔልሰን ማንዴላ የተበረከተ ዝነኛ የቦክስ ቀበቶ ተሰረቀ

አሜሪካዊው የቦክስ ሻምፒዮን ሹገር ሬይ ሊዮናርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊው የቦክስ ሻምፒዮን ሹገር ሬይ ሊዮናርድ ለቀድሞው የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ያበረከተው የቦክስ ቀበቶ መሰረቁን ተከትሎ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ፍለጋ መጀመሩን አስታወቀ።

ወደ 3,000 ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ያለው እንደሆነ የተነገረለት የአለም ሻምፒዮን ቀበቶ በሶዌቶ በሚገኘው የማንዴላ ቤት ሙዚየም ለእይታ ቀርቦ ነበር።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዲማካሶ ሴሎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቀበቶውን መሰረቁ ሪፖርት የተደረገውና ፖሊስም ጉዳዩን መከታተል የጀመረው ከሳምንት በፊት መሆኑን ነው።

ከአውሮፖውያኑ 1946 እስከ 1962 ባለው ጊዜ ውስጥ የአፓርታይድን አገዛዝ የታገሉት ኔልሰን ማንዴላ በኖሩበትና በአሁኑ ወቅት ዝነኛ በሆነው ሙዝየም ሰራተኛ ቁልፉ ሆን ተብሎ እንዲበላሽ መደረጉን ማስተዋላቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

ኔልሰን ማንዴላ የቦክስ ስፖርት አድናቂ ነበሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፖሊስ ምርመራ ባደረገበት ወቅት ቀበቶው እንደተወሰደ አረጋግጧል በአሁኑ ወቅት ባለው መረጃ ከቀበቶው በተጨማሪ ሌላ ነገር ተሰርቆ እንደሆነ ግልፅ አይደለም።

አፓርታይድን በመታገል 27 አመታትን በእስር ካሳለፉ በኋላ በአውሮፓውያኑ 1994 በደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ኔልሰን ማንዴላ የቦክስ ስፖርት ቀንደኛ አድናቂ ነበሩ

" ከቦክስ ጋር ተያይዞ ያለውን ጸበኝነትም ሆነ በሳይንሱም ይህን ያህል አያስደስተኝም። ነገር ግን አንድ ሰው እራሱን ለመከላከል ሰውነቱን እንዴት እንደሚያንቀሳቅስ፣ አንድ ሰው ለማጥቃት እና ለማፈግፈግ ስትራቴጂን እንዴት እንደሚጠቀም። ቦክሰኞች ራሳቸውን የሚቆጣጠሩበት መንገድ ሳስበው በጣም ይደንቀኛል” በማለት ማንዴላ በግለ ታሪካቸው ላይ አስፍረዋል።

የማንዴላ ሃውስ ሙዝየም በተገኘው መረጃ መሰረት ለማንዴላ ቀበቶው የተሰጣቸው በደቡብ አፍሪካ ጨቋኝ አፓርታይድ ስርዓት በአውሮፓውያኑ 1990 ከእስር ከተፈቱ ብዙም ሳይቆይ ነበር።

በዚያው አመት ማንዴላ በኒውዮርክ በፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ እገዛ ያደረጉ የአሜሪካ ቦክሰኞችን ያገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ቀበቶውን ያበረከተላቸው ሹገር ሬይ ሊዮናርድ ይገኙበታል።