ማንዴላ ታስረውበት የነበረው ክፍል ቁልፍ ለጨረታ መቅረቡን ደቡብ አፍሪካ ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኔልሰን ማንዴላ ታስረውበት የነበረው ክፍል ቁልፍ ኒው ዮርክ ውስጥ ለጨረታ መቅረቡን ደቡብ አፍሪካ ተቃወመች።
ሮቢን ደሴት ላይ በነበረው እስር ቤት ማንዴላ ታስረው ሳለ የቆዩበት ክፍል ቁልፍ በቀጣዩ ወር በጨረታ ይሸጣል ተብሎ ነበር።
ደቡብ አፍሪካ ግን ጨረታው እንዳይካሄድ ጠይቃለች።
ጉሬንሲስ በተባለ የጨረታ ማካሄጃ ድርጅት አማካይነት ማንዴላ ታስረውበት የነበረውን ክፍል ቁልፍ የሚሸጠው የቀድሞው የእስር ቤቱ ጠባቂ ነው።
ክሪስቶ ብራንድ የተባለው ይህ ግለሰብ ማንዴላ ታስረው በነበረበት ወቅት ጠባቂያቸው ነበር።
የደቡብ አፍሪካ የባህል ሚኒስትር ናቲ ሚታዋ፤ ቁልፉ ለጨረታ ሲቀርብ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አስተያየት አልተጠየቀም።
"ቁልፉ የደቡብ አፍሪካውያን ሀብት ነው። ማንም ሰው የግል ንብረቱ ሊያደርገው አይችልም" ብለዋል።
የጨረታው አስተባባሪዎች እንደሚሉት፤ ከጨረታው የሚገኘው ገቢ በማንዴላ መቃብር አካባቢ መታሰብያ ሙዚየም ለመገንባት ይውላል።
ከቁልፉ በተጨማሪ የማንዴላ 'ዘ ላይትሐውስ' የተባለው ሥዕል እና እስር ቤት ሳሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጉበት የነበረ ሳይክል እና የቴኒስ መጫወቻም ለጨረታ ቀርቧል።
የነጻነት ታጋዩ ማንዴላ ለ27 ዓመታት በእስር አሳልፈዋል። ከእነዚህ ዓመታት 18ቱ በሮበን አይላንድ ነበሩ።
ማንዴላ የታሰሩበትን ክፍል ለጨረታ ያቀረበው ግለሰብ እና ማንዴላ ታስረው በነበረበት ወቅት ሲጠብቃቸው ወዳጆች ሆነው ነበር።
በዓመታት ውስጥ የልብ ጓደኞች እስከመሆንም ደርሰዋል።
እአአ በ1990 ማንዴላ ከእስር ሲለቀቁ ደቡብ አፍሪካ ዘርን መሠረት ካደረገ ሥርዓት ቀስ በቀስ መላቀቅ ጀምራለች።
እአአ በ1994 ለመጀመሪያ ጊዜ ከነጮች ውጪ ያለው የደቡብ አፍሪካ ማኅበረሰብ በምርጫ ተሳትፏል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ጥቁር መሪዋ ማንዴላን የመረጠችውም ያኔ ነው።
በ1999 ማንዴላ መንበረ ሥልጣናቸውን አስረክበዋል።
2013 ላይ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።












