ዘጠኝ ተኩላዎች ካመለጡ በኋላ የፈረንሳዩ መካነ እንስሳት ተዘጋ

ተኩላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዘጠኝ ተኩላዎች ማምለጣቸውን ተከትሎ አንድ የፈረንሳይ መካነ እንስሳት በጊዜያዊነት ተዘጋ።

መካነ እንስሳቱ ለጎብኚዎች ክፍት በነበረበት ሰዓት ዘጠኙ ተኩላዎች ከጥብቅ ማቆያቸው አምልጠዋል።

ትሪዮስ ቫሊስ በተባለውና በደቡባዊ ፈረንሳይ በሚገኘው መካነ እንስሳት ይኖሩ የነበሩት ተኩላዎች ካመለጡ በኋላ ሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም።

ተኩላዎቹ በመካነ እንስሳቱ የተገነባውን የሽቦ አጥር ጥሰው ነበር ያመለጡት። ከመካነ እንስሳቱ ሳይወጡ እዛው ግቢ ውስጥ ነበር የተደበቁት።

ፋቢን ቾልት የተባሉ የአካባቢው ባለሥልጣን እንዳሉት፤ አራቱ ተኩላዎች አደገኛ ባህሪ ስላሳዩ እንዲገደሉ ተወስኗል።

አምስቱ ተኩላዎች ደግሞ ማደንዣ ተወግተው ወደ ማቆያ ተመልሰዋል።

ባለሥልጣኑ እንዳሉት፤ ተኩላዎቹ ሲያመልጡ ብዙ ሰዎች በመካነ እንስሳቱ ውስጥ ስላልነበሩ ለአደጋ አልተጋለጡም።

ሆኖም ግን የተፈጠረው የደኅንነት ስጋት እስከሚቀረፍ ድረስ መካነ እንስሳቱ እንዲዘጋ ተወስኗል።

የመካነ እንስሳቱ ባለቤት ሳቩር ፈራራ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት፤ ተኩላዎቹ በመካነ እንስሳቱ የገቡት በቅርቡ ነው።

60 ሄክታር የሚሸፍነው መካነ እንስሳቱ አንበሳ፣ ጦጣ እና ፍላሚንጎን ጨምሮ 600 የእንስሳ ዝርያዎች አሉት።

ከዚህ ቀደም ከእንስሳት ጤንነት እና ከሠራተኞች ደኅንነት ጋር በተያያዘ መካነ እንስሳቱ በጊዜያዊነት እንዲዘጋ የፈረንሳይ ኢኮሎጂ ሚኒስቴር ወስኖ ነበር።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን መካነ እንስሳቱ እንዲከፈት ፍርድ ቤት ወስኗል።