የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የ3ዲ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ አደረጉ

በእንግሊዝ የ11 ዓመት ታዳጊ የ3ዲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኩላሊት ቀዶ ህክምና ተደረገላት።
በአገሪቷ የ3ዲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኩላሊት ቀዶ ህክምና ሲደረግ የዚች ታዳጊ የመጀመሪያው ነው።
በእንግሊዟ ዋቼት ግዛት ነዋሪ የሆነችው ሊቢ በኩላሊት እና በፊኛ ችግሮች እየተሰቃየች የነበረች ሲሆን ለረዥም ጊዜም በከፋ ህመም ትሰቃይ ነበር።
ከሰሞኑም የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች የ3ዲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትንሽ ቀዳዳ አበጅተው ፈጣን በሆነ እና በተሳካ መንገድ ቀዶ ህክምና በሊቢ ላይ ማድረግ ችለዋል።
በመላ አገሪቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ልጆች በቀጣዩ ፈጣን የቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው እንደሚችል ተነግሯል።
ከ200 ህፃናት መካከል አንዱ ከተለጠጡ ኩላሊቶች ጋር የሚወለዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ቀዶ ህክምና የተደረገላት ሊቢ አደግ እስክትል ድረስ ሁኔታዋ አልታወቀም ነበር።
ኩላሊቷን ከፊኛዋ ጋር የሚያገናኘው የሽንት ቱቦ በመዘጋቱም ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ገብታ ነበር።
ህመሟም እየከፋ በመጣ ቁጥር የሊቢ ሁኔታ ለቤተሰቡ "በጣም አስጨናቂ ነበር" ሲሉ እናቷ ተናግረዋል።
4 ሚሊሜትር ስፋት ያለው እና ለአእምሮ ቀዶ ህክምና በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውለውን የ3ዲ ቴክኖሎጂን መሳሪያ በመጠቀም ያለባት እክል ተስተክሏል።
ቀዶ ህክምናው የተደረገላት በብሪስቶል የህጻናት ሆስፒታል ነው።
ሊቢ ላይ ቀዶ ህክምና ያደረጉላት ዶክተር ማርክ ዉድዋርድ እንደተናገሩት 20 ሺህ ፓውንድ የሚያወጣው የ3ዲ መሳሪያ በቀዶ ጥገናው ወቅት ትክክለኛ ምስል እንዲያገኙና እንዲሁም በተቀላጠፈና በተሳካ መንገድ ቀዶ ህክምናውን ለማካሄድ አስችሎኛል ብለዋል።
ዶክተሩ አክለውም የ3ዲ መሳሪያው በትክክል ቀዶ ህክምና ማድረግ የሚያስችል ሲሆን ሰልጣኝ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችም በፍጥነት እንዲማሩ ያግዛል ብለዋል።
የሊቢ ቀዶ ህክምና በተለምዶ ከሁለት እስከ ሶስት ሰአታት ይወስድ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን 3ዲ መሳሪያዎችን በመጠቀም ዶክተሮች በ 20 በመቶ መቀነስ እንደሚቻልም ተናግረዋል።












