ሩሲያ ጉግል ላይ የ98 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት አስተላለፈች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሞስኮ በሚገኝ ፍርድ ቤት ጉዳዩ የታየው የጉግል ኩባኒያ፣ በተደጋጋሚ ሲሰራጭ የነበረን ሕገ ወጥ ይዘት ለማጥፋት አልቻለም በሚል በቀረበበት ክስ 98 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ መቀጮ ተጣለበት።
የፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት በክሱ ላይ የተጠቀሰው ይዘት ምን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥቧል። ይህም በሩሲያ አንድ የቴክኖሎጂ ግዙፍ ኩባኒያ ላይ በዓመታዊ ገቢው ላይ የተመሰረተ ቅጣት ሲጣል የመጀመሪያው አድርጎታል።
ጉግል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል የችሎቱን ውሳኔ በመመርመር ቀጣይ እርምጃዎቹ ምን ሊሆኑ እንደሚገባ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተናግሯል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት በቴክኖሎጂ ኩባኒያዎች ላይ የሚያደርሱትን ጫና በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት ያጠበቁ ሲሆን፣ ይህም ይዘታቸውን ባግባቡ መቆጣጠር አልቻሉም ከሚል ክስ የመነጨ ነው። በተጨማሪም በሩሲያ የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት የሚሉት ክሶች ይገኙበታል።
ጉግል ላይ ቅጣቱ በተላለፈ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሜታ ኩባኒያ ላይም የሁለት ቢሊዮን ሩብሊ ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ከተመሳሳይ ይዘት ጋር የተገናኘ ክስ ደርሶታል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ትዊተርም በተመሳሳይ የሦስት ሚሊዮን ሩብሊ ቅጣት ደርሶታል።
ጉግል ከሩሲያ ባለሥጣናት ጋር ይዘቶችን ከተመለከቱ ሕጎች ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ ሲገባ ይህ የመጀመሪየው አደለም።
በግንቦት ወር ሩሲያ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ ጉግል ከ26 ሺህ በላይ የሚሆኑ ከአደንዛዥ ዕጽ፣ ከጥቃቶች እና ከአክራሪነት ጋር ይያያዛሉ የተባሉ ሕገ ወጥ ይዘቶችን ካላጠፋ የጉግልን ፍጥነት እንደሚቀንስ ገልጾ ነበር።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው 'ሉአላዊ ኢንተርኔት' ሲሉ የጠሩትንና መንግሥት ዜጎች ማግኘት የሚችሉት መረጃ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችለውን ግልጋሎት እንዲጀመር ግፊት ሲያደርጉ ነበር።
ተቺዎቻቸውም ሩሲያ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ብሎም በበይነ መረብ የሚሰራጩ ተቃውሞዎችን ለመጨቆን የምታደርገው ዘመቻ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪም በርካታ በእስር ላይ ከሚገኘው እና የመንግሥት ደጋፊዎችም እንደ አክራሪ ሲሉ የፈረጁት የተቃዋሚ መሪው አሌክሲ ናቫንሊ ጋር የተያያዙ የበይነ መረብ ገጾችን አግዷል።
ጉግል እና አፕል ለናቫንሊ ስማርት የድምጽ አሰጣጥ ዘመቻ የተባለ መተግበሪያን እንዲዘርጉም ተገደዋል። መተግበሪያው ተጠቃሚዎች ከመንግሥት ጎን የሚቆሙ ፖለቲካኞች እንዳይመረጡ የሚያስችል የምርጫ ስልቶችን ምክር የሚሰጥ ነበር።
እንደ ሊንክድኢን እና ዴይሊሞሽን ያሉ ዌብሳይቶች ከባለሥጣናት ጋር ለመተባበር አልፈቀዱም በሚል እገዳ ተጥሎባቸዋል። እንዲሁም ሦስት ቪፒኤን አገልግሎት አቅራቢዎችም ታግደዋል።
በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይም ሩሲያ በአገሪቱ ገበያ ውስጥ የሚቀርቡ ሁሉም ስማርት ስልኮች፣ ኮምፒውተሮች እንዲሁም ማንኛውም ስማርት መገልገያዎች ከመሸጣቸው በፊት በሩሲያ የተሰሩ ሶፍትዌሮች እንዲሁም መተግበሪያዎች እንዲጫንባቸው የሚያስገድድ ሕግ ወደ ሥራ ገብቷል።
መንግሥት እርምጃው የሩሲያ የቴክኖሎጂ ተቋማት ከውጪ ተፎካካሪዎቻቸው ጋር በሚያደርጉት ውድድር ላይ ለሚያገዝ ነው ሲል ገልጿል።
















