የአሜሪካ መንግሥት ጉግል ኩባንያን ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ መንግሥት የጉግል ኩባንያ ላይ በጠቅልሎ መያዝ የንግድ ሕግ ጥሰት (ሞኖፖሊ) ክስ መሠረተበት።
ጉጉል ተወዳዳሪ ኩባንያዎችን በመጨፍለቅና በዘርፉ ያለውን ተቀባይነት በመጠቀም የማስታወቂያ ሽምያ የበላይነትን በመያዝ ፍትሐዊ ያልሆነ የውድድር ሜዳ ፈጥሯል ሲል ነው መንግሥት የከሰሰው።
ይህ ክስ በቅርብ ታሪክ ውስጥ የአሜሪካ መንግሥት በአንድ ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያ ላይ ያቀረበው ትልቅ የፍርድ ቤት ፋይል ሆኖ ተመዝግቧል።
ክሱ ላለፈው አንድ ዓመት ድረስ በአቃቢ ሕግ በኩል ሲመረመርና ሲጠናቀር የቆየ እንደነበር ተብራርቷል።
ጉግል ክሱን ‹‹ጉድለት ያለበት›› ሲል አጣጥሎታል።
‹‹የውድድር ሜዳው ፉክክር የበዛበት ነው። ለደንበኞቻችንን ፍላጎት ሁሌም ተገዢዎች ነን። ቅድሚያም እንሰጣለን። ሰዎች ጉጉልን የሚጠቀሙት በምርጫ ነው እንጂ ተገደው አይደለም" ብሏል ኩባንያው።
የክስ መዝገቡ የተከፈተው በፌዴራል ፍርድ ቤት ሲሆን ክስ መሥራቾቹ የጀስቲስ ዲፓርትመንት እና 11 የአሜሪካ ግዛቶች ናቸው።
የክሱ ጭብጥ የሚያጠነጥነው ጉጉል ኩባንያ ኢንተርኔት ማሰሻ መተግበሪያዎች (ብራውዘርስ) እና ለስልክ አምራቾች ከሚፈጽማቸው ክፍያዎች ጋር የሚያያዝ ነው። ጉጉል ለነዚህ ድርጅቶች በዋናነት ክፍያ የሚፈጽመው ‹‹ጉግል›› ኢንተርኔት ማሰሻ በአማራጭነት ዝርዝር ቅድሚያ ተመራጭ ሆኖ እንዲመጣ እንዲያደርጉለት ነው።
ጉጉል በአሜሪካ ብቻ የበይነ መረብ ማሰሻዎች ላይ የ80 በመቶ ቁጥጥር አለው። በዚህም የተነሳ ጉጉል የበይነመረብ ንጉሥ እየሆነ ነው እየተባለ ይተቻል።
በንግድ ፍትሐዊ ውድድር እንዳይኖርም ሁለንተናዊ ቁጥጥር እያደረገ ነው በሚል ይወቀሳል።
የጉግል ማሰሻ የገበያ ድርሻ ከሚገባው በላይ በማበጡ ሌሎች የበይነ መረብ ማሰሻዎች ከገበያ በነው እንዲጠፉ ሆነዋል። ይህ ሁኔታ የመረጃ ፍሰት በአግባቡ እንዳይኖር፣ የሰዎች መረጃ በአንድ ኩባንያ ብቻ ተጠቃሎ እንዲቀበር የሚያደርግ ነው በሚል ወቀሳ ይሰነዘራል።
የጉጉል ኩባንያ ሁለተንተና ቁጥጥር (ሞኖፖሊ) ከመብዛቱ የተነሳ ቃሉ ራሱ የኩባንያ ስም ከመሆን አልፎ መረጃን ማሰስ የሚል ግስ ሆኖ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመግባት በቅቷል ይላሉ ተቺዎቹ።
ጉጉል ይህ የገበያ ውድድር ጨፍላቂነቱን ተከትሎ ክስ ሲመሰረትበት የመጀመርያው አይደለም። ተመሳሳይ ክስ በአውሮጳ ኅብረት ተከፍቶበታል። የአውሮጳ ኮሚሽን ጉግል ላደረሰው የገበያ ተወዳዳሪነት ጥሰት 10 ቢሊዮን ዶላር ይቀጣልኝ ብሏል።
ክሶቹ በሦስት የተለያዩ ዓመታት ውስጥ ለፈጸማቸው ተግባራት የተቃጡ ናቸው። ጉጉል በ2018 አንድሮይድ ሶፍትዌር ፍትሐዊ ባልሆነ ሁኔታ ማሰሻውን እንዲያስተዋውቅለት መጠኑ ያልታወቀ ክፍያን መፈጸሙ እንዲሁም በ2019 ሌሎች የበይነ መረብ ማሰሻዎች ማስታወቂያ እንዳያገኙ በማድረጉ በቢሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
ጉጉል በአውሮጳ ኮሚሽን ለተከፈቱበት ክሶችና ለተወሰነቡት የገንዘብ ቅጣቶች ይግባኝ ብሏል።












