የፖለቲካ ተንታኙ ቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ ብልቱን ሲነካካ በመታየቱ ይቅርታ ጠየቀ

የፖለቲካ ተንታኙ ጄፍሪ ቱቢን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፖለቲካ ተንታኙ ጄፍሪ ቱቢን

በአሜሪካ ፖለቲካ አሉ ከሚባሉ የሕግ ተንታኞች አንዱ ነው። ለዝነኛው የኒውዮርከር መጽሔት ይሰራል።

በሲኤንኤን ቴሌቪዥን በመቅረብም ጥልቅ የሕግና ፖለቲካ ትንታኔዎችን በመስጠት ይታወቃል።

ጄፍሪ ቱቢን 60 ዓመቱ ሲሆን መቼ ለታ ዙም በተሰኘ የኢንተርኔት ቪዲዮ ጥሪ ላይ እያለ ነው ስህተት የፈጸመው።

ድርጊቱ ያበሳጨው ኒውዮርከር መጽሔት ከሥራ አግዶታል።

የአሜሪካ ምርጫ 15 ቀናት በቀረበት በአሁኑ ወቅት ጄፍሪ በሚዲያዎች ላይ እጅግ ተፈላጊው ተንታኝ ነበር።

ጄፍሪ ካሜራ የጠፋ መስሎት ነው ድርጊቱን የፈጸመው።

ድርጊቱን በቅድምያ ላጋለጠው ቫይስ ኒውስ ጄፍሪ እንደተናዘዘው ‹‹ድርጊቱን ያደረኩት ካሜራ የጠፋ መስሎኝ ነው፤ ቀሽም ሥራ ነው የሰራሁት፤ አፍሪያለሁ›› ብሏል።

ጄፍሪ ለቤተሰቡ ለጓደኞቹና ለባልደረቦቹ ከፍ ያለ ይቅርታን ጠይቋል።

የዙም ቪዲዮ ማብሪያና ማጥፊያውን እንደተዘጋ የገመተው ጄፍሪ በዚህ የሥርጭት ልምምድ ወቅት ብልቱን ሲነካካ ነበር።

ቫይስ ኒውስ ጄፍሪ ድርጊቱን ሲፈጽሙ ያዩትን እማኞቹን ጠቅሶ ነው ዜናው ለአደባባይ ያበቃው።

ነገሩን እስክንመረምር ድረስ ጄፍሪን ከሥራ አግደናዋል ብሏል ኒውዮርከር።

ጄፍሪ ለታዋቂው ሲኤንኤን ጣቢያም ዋና የሕግ ተንታኝ ነው። ሲኤንኤን በበኩሉ ጄፍሪ ትንሽ ለራሴ ጊዜ እፈልጋለሁ ብሎናል፤ በሥርጭቶቻችን ላይ ተመልሶ ለመቅረብ ጊዜ ይፈልጋል። ይህንንም ፈቅደንለታል ሲል መግለጫ አውጥቷል።

ጄፍሪ በሕግና ፖለቲካ ዙርያ በተለይም ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በተያያዘ በርካታ መጻሕፍትን ለኅትመት አብቅቷል።