ዩናይትድ ኪንግደም ጤነኛ ሰዎችን በኮቪድ ተህዋሲ 'ልትለክፋቸው' ነው

መርፌ የሚወጋ የጤና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮቪድ ክትባትን በማግኘት ጥረት ውስጥ ከፊት ከሆኑ አገራት አንዷ የሆነችው ዩናይትድ ኪንግደም የተለየ አይነት የክትባት ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚዋ አገር ልትሆን ነው።

በጥር ወር ላይ 90 ጤነኛ ሰዎች ሆን ተብለው ለኮቪድ ተህዋሲ እንዲጋለጡ በማድረግ ነው አዲሱ ሙከራ የሚደረገው።

ይህም ቶሎ ክትባት ለማግኘት ይረዳል ተብሏል።

መንግሥት ከወዲሁ 33.6 ሚሊዮን ፓውንድ ለዚሁ ሙከራ መድቧል።

ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግበታል የተባለው ይህ አዲስ የሙከራ ዘዴ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከአገሪቱ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ይሁንታን ማግኘት ይኖርበታል።

በመድኃኒት ቅመማ ሂደት ‹ሂዩማን ቻሌንጅ› በሚል የሚታወቀው ይህ ጤነኞች ላይ በሽታ አምጪ ተህዋስን ሆን ብሎ በማጋባት ሙከራ ማድረግ ብዙም የተለመደ አይደለም።

ነገር ግን ከዚህ ቀደም በወባና በኢንፍሉዌዛ የመድኃኒት ግኝቶች ሂደት ውስጥ ተሞክሮ ውጤት ማስገኘቱን ኔቸር መጽሔት ዘግቧል።

ሳይንቲስቶች በጥር ወር መጀመርያ ተግባራዊ ያደርጉታል በተባለው በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉት ሰዎች ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 የሚሆን ፍጹም ጤነኛ የሆኑ በጎ ፈቃደኞች ብቻ ናቸው።

ሙከራው አንድን ሰው ምን ያህል የተህዋሲው መጠን ነው ለበሽታ የሚያጋልጠው የሚለውንም ለማወቅ ይረዳል ተብሏል።

ለበጎ ፈቃደኞቹ በቅድሚያ ተህዋሲው በትንሽ መጠን ይሰጣቸዋል።

ፍጹም ጤነኛ ሰዎችን እንደ አይጥ መሞከርያ ማድረግ ቶሎ ውጤት ለማግኘት አስፈላጊ ነው የሚሉ በርካታ ቢሆንም መድኃኒት በሌለው በሽታ ሰዎችን ሆን ብሎ መበከል ከሕክምና ሥነ ምግባር አንጻር ተገቢ አይደለም ሲሉ ነገሩን የሚተቹትም በርካታ ናቸው።

ተህዋሲው ለበጎ ፈቃደኞቹ የሚሰጣቸው በአፍንጫቸው በኩል ይሆናል ተብሏል።

ለ24 ሰዓታትም ጥብቅ ክትትል ይደረግላቸዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ ለከፋ አደጋ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ጤነኞችና ወጣቶች በመሆናቸውና በጥንቃቄ ስለሚመረጡ ነው ይላሉ ተመራማሪዎች።

ቅድመ ጥንቃቄው አስተማማኝ በሚባል ደረጃ ላይ ሲደርስ በበጎ ፈቃደኞቹ በአንዳንዶቹ ላይ ሙከራ ላይ የሚገኙ ክትባቶች ይሰጧቸዋል።

ለኮቪድ ተህዋሲው ከመገላጣቸው በፊትም ክትባት እንዲወስዱ የሚደረጉ ይኖራሉ። ክትባቱን የወሰዱት ለተህዋሲው ተጋልጠው ተህዋሲው ይይዛቸዋል ወይስ አይዛቸውም የሚለውም ምላሽ ያገኛል።

የዚህ ምርምር መሪ የኢምፔሪያል ኮሌጁ ዶ/ር ክሪስ ቺዩ ሰዎች ያን ያህልም ሐሳብ ሊገባቸው አይገባም ይላሉ።

‹‹እኔና ባልደረቦቼ በዚህ መንገድ ላለፉት 10 ዓመታት በርካታ ጤነኛ ሰዎች ላይ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ ቫይረሶችን በመስጠት ስንሰራ ቆይተናል። እርግጥ ነው የትኛውም ጥናት ቢሆን የራሱ አደጋ የለውም አይባልም። ነገር ግን አደጋውን ለመቀነስ እንታገላለን›› ብለዋል።

ረዳታቸው ፕሮፌሰር ፒተር ኦፔን ሻው በበኩላቸው ጤነኛ ሰዎችን በተህዋሲ ሆን ብሎ በመበከል ምርምር ማካሄድ በቀላሉ የሚታይ ነገር ባይሆንም ውጤት ለማግኘት ግን ወሳኝ ነው፤ ያግዛል ብለዋል።

በአሁን ሰዓት በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮቪድ ክትባቶች በመጨረሻ ምዕራፍ ሙከራ ላይ ሲሆኑ ውጤት ያስገኛሉ ተብለው በጉጉት እየተጠበቁ ካሉት መካከል የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው ተጠቃሽ ነው።

በጥር ወር ጤነኛ ሰዎችን በተህዋሲው በመበከል የሚደረገው ምርምር ሌላ ፍቱን መድኃኒት ቀድሞ ቢገኝም የሚቋረጥ አይሆንም።

ክትባቶች ከተገኙ በኋላ የትኛው ክትባት እጅግ ውጤታማ ነው የሚለው ጥናት ይቀጥላል።

ተህዋሲውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመውሰድ የፈቀዱ የታላቋ ብሪታኒያ ዜጎች ለጊዜያቸውና ለደፋር ውሳኔያቸው የሚመጥን ነው የሚባል ገንዘብ ይከፈላቸዋል።

ሙከራው ከተደረገባቸው በኋላም ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያለማቋረጥ የቅርብ ክትትል ይደረግባቸዋል።