ጋዜጠኛዋን ገድሎ መነጋገሪያ የነበረው ከእስር ቤት ሊያመልጥ ሲል ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, RITZAU SCANPIX/NILS MEILVANG
የስዊድን ዜጋ የነበረችውን ጋዜጠኛ ኪም ዎልን ከገደለ በኋላ መነጋገርያ የነበረው ፒተር ማደሰን ከእስር ቤት ሊያመልጥ ሲል በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ፖሊስ ከኮፐንሀገን አቅራቢያ ከእስር ቤት ሊያመልጥ የነበረውን ሰው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ከሳወቀ በኋላ ማንነቱ ሳይገልጽ ቆይቶ ነበር.
በኋላ ላይ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሲል በቁጥጥር ሥር የዋለው ሰርጓጅ መርከብ ሰሪው ፒተር ማደሰን መሆኑን አረጋግጧል።
ዴንማርካዊው ማደሰን ከእስር ቤት ሊያመልጥ በሞከረበት ወቅት በታጠቁ ፖሊስ አባላት ተከቦ የሚያሳይ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተሰራጭቷል።
በስፍራው የነበረ አንድ ፎቶ አንሺ ማደሰን ወገቡ ላይ ቀበቶ ታጥቆ እና ግድግዳ ተደግፎ የሚያሳይ ምሥል በድረ-ገጹ ላይ አትሟል።
ማደሰን ፖሊሶች እየቀረቡት ሲመጡ ቦምብ ታጥቂያለሁና አትጠጉኝ እያለ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው ነበር።
ፖሊስ ቦምብ አምካኝ ባለሙያዎችን ወደስፋራው ያሰማራ ሲሆን ኋላ ላይ የማደሰን ማስፈራሪያ የሐሰት መሆኑ ሲረጋገጥ ወደ እስር ቤት ወስዶታል፡፡
ማደሰን በጋዜጠኛዋ ኪም ዎል ግድያ ጥፋተኛ መባሉን ተከትሎ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ነበር።
ጋዜጠኛዋ የገባችባት ሳይታወቅ ቆይቶ ከጠፋች ከ11 ቀናት በኋላ አካሏ ተቆራርጦ ከባህር ዳርቻ አቅራቢያ ተገኝቶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, TOM WALL
ኪም ዎል ማን ነበረች?
የስዊድን ዜጋ የነበረችው ኪም ዎል በመላው ዓለም በመዘዋወር በምትሰራቸው ዘገባዎች እውቅናን አትርፋለች።
ከዚያ በኋላ ግን ድንገት ተሰውራ ቆይታ ነበር፡፡
በመጨረሻም እአአ 2017 ላይ የፒተር ማደሰንን ሰርጓጅ መርከብ ከተሳፈረች ከ11 ቀናት በኋላ የሰውነት አካሏ ተቆራርጦ ተገኝቷል።
በወቅቱ ማድሰን ጋዜጠኛዋ የሞተችው ባጋጠመ አደጋ ነው ቢልም ፍርድ ቤቱ መከራከሪያውን ውድቅ አድርጎበታል።
ማድሰን የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላ ለአንድ ሚዲያ በሰጠው ቃል ለጋዜጠኛዋ ሞት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ተናግሮ ነበር፡፡።












