ትራምፕ ሱዳንን ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ሊሰርዟት ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሱዳን"የሽብር ተጠቂና በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካውያን 335 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከከፈለች አሸባሪነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደምትሰርዛት ተናግረዋል።
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በበኩላቸው የካሳው ገንዘብ ቢተላለፍም ከአሜሪካ በኩል የተፋጠነ ምላሸ አላየንም ብለዋል።
በዝርዝሩ መካተት አገራቸውን ከፍተኛ ክፍያ እንዳስከፈላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ገንዘቡ መከፈሉም ከዝርዝሩ ለመውጣት የመጨረሻ ዋስትናችን ነው" ማለታቸውን የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።
የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ሱዳንን ለተወሰነ ጊዜ ኖሮባታል፤ እንዲሁም መቀመጫው ነበረች በማለት አሜሪካ ሱዳንን የምትወነጅላት ሲሆን ከጎሮጎሳውያኑ 1993ም ጀምሮ ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ውስጥ አካትታለች።
ካሳውም አልቃይዳ በ1998 በኬንያና በታንዛንያ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ቦምብ ፍንዳታዎች መፈፀሙ ጋር የተያያዘ ነው።
በኬንያና በታንዛንያ በደረሰው ጥቃት 220 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የካሳው ገንዘብ ለተጠቂዎችና በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካውያን እንደሚከፈልም ትራምፕተናግረዋል።
ሱዳን ከሶስት አስርት አመታት በላይ የገዙዋት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መወገድ ተከትሎ የአሜሪካና የሱዳን ግንኙነት መሻሻሉም እየተናገረ ነው።
"መልካም ዜና ነው። አዲሱ የሱዳን መንግሥት በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገ ነው። አሁን ደግሞ ለሽብር ተጠቂና በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካውያን 335 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል" በማለትም ነው ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገፃቸው ያሰፈሩት።
"ገንዘቡ ከተሰጠ በኋላ ሱዳንን ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ አወጣታለሁ። በመጨረሻም ፍትህ ለአሜሪካ ህዝብ ፤ ለሱዳንም ትልቅ ደረጃ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ የማውጣት ስልጣን ያላቸው ሲሆን ምክር ቤቱ ደግሞ ለመቃወም 45 ቀናት አሉት።
አሜሪካ በጥቁር መዝገብ ውስጥ ካካተቻቸው አገራት መካከል አንዷ ሱዳን ስትሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያና ሶሪያ ይገኙበታል።












