በገላን አካባቢ የአንድ ታዳጊ በጅብ መበላትን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ጅቦችን እያደኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, SM
በአዲስ አበባ ዙርያ ሸገር ከተማ ገላን አካባቢ፣ ዳለቲ ወረዳ ትናንት አንድ ሕጻን በጅብ መበላቱን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች በወሰዱት የበቀል እርምጃ 14 ጅቦች መገደላቸውን የዳለቲ ወረዳ ሰራተኛ የሆኑት አቶ ባጫ ተረፈ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኃላፊው ጨምረው እንዳሉት ሕጻኑ የተበላበትና 5 ሄክታር የሚሸፍነውን የጅቦች መደበቂያ ቦታ ለማጽዳት ከዚህ ቀደም 2 ግሬደሮች መገዛታቸውን ተናግረዋል። “በጆቦቹ ላይ የሚወሰደው እርምጃም ይቀጥላል” ብለዋል።
በስፍራው ከ100 በላይ ጅቦች እንዳሉ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ቀርሳ የሚባል ቦታ ነው። እዚያ አካባቢ ጅብ አልፎ አልፎ ይታያል። ትናንት ረፋድ 4፡30 አካባቢ የሰፈሩ ልጆች ወጣ ብለው ሲጫወቱ ነበር። ከነሱ መሀል አንድ የ2 ዓመት ሕጻን ነው ድንገት ጅብ ወደ ጫካ ይዞት የሄደው። ቦታው የሙስሊም መቃብር ነው። በዚያ አቅራቢያ አንድ ባለሃብት ቤት ሠርቶ ቤቱን እንዲጠብቅለት የመደበው ሰው ልጅ ነው በጅብ የተበላው። ቀን ስለሆነ ልጆቹ ጨዋታ ላይ ነበሩ። በአጋጣሚ ጅቦች በዚያ ይመላለሱ ነበር። በእርግጥ ከዚህ ቀደም ጅብ በስፍራው ብዙም ሰው አይተናኮልም ነበር።”
የሟቹ አባት እንደነገሩን ከሆነ በተለይ ጅብ ከሌላ አካባቢ ሰው ከመጣ የመቆጣት ባህሪው አለው። ጅብ ሕጻኑን ወደ ጫካ ይዞት ሲሄድ ከጓደኞቹ አንደኛው ለእናቱ ሄዶ “ውሻ ልጃቸውን ወደ ጫካ ይዞት እንደሄደ ይነግራቸዋል።
እናት ለእርዳታ ስትጮኽ ሕዝብ ወጥቶ ነው 14 የሚሆኑ ጅቦች ላይ እርምጃ የወሰደው። የተገደሉትን ጅቦች ሰብስበን አቃጥለናቸዋል ብለዋል ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ።
ሌሊት የተረፉት ጅቦች ቢወጡም ጉዳት ሳያደርሱ ተመልሰዋል። ዛሬም ሕዝብ ወጥቶ ጅቦችን እያደነ ነው ያለው። ለሟቹ ልጅ አባት መኖርያ እንዲሆናቸው ደግሞ የቀበሌ ቤት እየተሠራላቸው ነው።
በጅብ የተበላው ልጅን በተመለከተ የተጠየቁት ኃላፊው ሕጻኑ በጅብ ወደ ጫካ ከተወሰደ በኋላ ሕዝቡ እስኪደርስ ድረስ አጥንቶቹ ብቻ ቀርተው እንደነበረ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት አደጋ በአካባቢው ደርሶ ከሆነ በሚል የተጠየቁት ኃላፊው፣ አንድ ጠጥቶ ሰክሮ ያመሸ ሰው ከ2 ዓመት በፊት በጅብ መበላቱን እንደሚያውቁና ከዚህ ቀደምም 2 አዋቂዎች በተመሳሳይ እንደተበሉ አስታውሰዋል።












