ትራምፕ፤ ዝቅተኛ የስራ እድል መፈጠሩን የሚያሳይ ሪፖርት ያወጡትን ባለስልጣን አባረሩ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከተጠበቀው በላይ ዝቅተኛ የስራ እድል እንደተፈጠረ የሚያሳየውን እና የፕሬዝዳንቱን የታሪፍ ፖሊሲ በተመለከተ የሚነሱ ስጋቶች እንዲጨምር ምክንያት የሆነውን ሪፖሪት ያወጣውን ቢሮ የሚመሩትን ኢኮኖሚስት አባረሩ።

የምጣኔ ኃብት ባለሙያዋ ኤሪካ ማክኤንታርፈር፤ በርካቶች በቅርበት የሚከታተሉትን ኢኮኖሚያዊ ዳታ የሚያወጣው የአሜሪካ የሰራተኛ ስታትስቲክስ ቢሮ ኮሚሽነር ናቸው።

ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ ኮሚሽነሯ ለፖለቲካዊ ምክንያቶች ሲሉ የስራ ፈጠራ ቁጥሮችን አጭበርብረዋል ሲሉ ያለ ምንም ማስረጃ ከስሰዋል።

የትራምፕ ውሳኔ የፋይንስ ገበያ ማዕከል የሆነውን ዎል ስትሪት ያስደነገጠ ሲሆን በዋይት ሀውስ የኢኮኖሚ መረጃዎች ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በተመለከተ ስጋት ፈጥሯል።

ኃላፊዋ ማክኤንታርፈር በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፤ የኮሚሽነርነት ጊዜያቸውን "የህይወቴ ክብር" በማለት ጠርተውታል። ይመሩት የነበረውን የተቋም ተግባርን "ጠቃሚ እና አስፈላጊ" በማለት ገልጸዋል።

ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፉት ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ከፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአክስዮን ገበያዎች በአለመረጋጋት እየተናጡ ባሉበት በዚህ ጊዜ ነው።

በርካታ ባለሙያዎች የትራምፕ ታሪፍ ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳ ትንበያቸውን አስቀምጠዋል።

የበርካታ ግዙፍ ኩባንያዎችን አክስዮኖች አንድ ላይ በማድረግ ለገበያ የሚያቀርቡት አሜሪካ ሶስት ዋና ዋና ኢንዴክሶች ዋጋቸው ቀንሷል።

ከእነዚህ አንዱ የሆነው ኤስ ኤንድ ፒ የንግድ ቀኑን ያጠናቀቀው በአውሮፓ እና እስያ ገበያዎች ከነበረው ዋጋ በ1.6 በመቶ ዝቅ ብሎ ነው።

በኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ፤ የአሜሪካ ዋና ኢኮኖሚስት የሆኑት ራያን ስዊት፤ የሰራተኛ ስታትስቲክስ ቢሮ ኮሚሽነርን ለማሰናበት የተላለፈው ውሳኔ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ጥራት ያለው ኢኮኖሚያዊ መረጃ ለንግዶች እንቅስቃሴ አስፈላጊ መሆኑን እና በቀላሉ በግል ኩባንያዎች በሚገኝ ዳታ ሊተካ እንደማይችል አስረድተዋል።

"ይህ በጣም መጥፎ ወደሆነ አቅጣጫ የተወሰደ ግልፅ እርምጃ ነው" ብለዋል። "በመረጃው ታማኝነት ዙሪያ ጥያቄዎች የሚነሱ ከሆነ... ብዙ ችግሮችን ይፈጥራል" ሲሉም የሚያስከትለውን ችግር ጠቅሰዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ትራምፕ በበኩላቸው፤ አሜሪካ ውስጥ የሚኖረውን ማኑፋክቸሪንግን ከፍ የሚያደርግ እና የዓለም አቀፍ ንግድን እንደገና ሚዛናዊ የሚያደርግ በማለት የሚገልጹትን የታሪፍ ፖሊሲያቸውን በተመለከቱ የሚነሱ ስጋቶችን ውድቅ አድርገዋል።

በዚህ ሳምንት የወጡ አዳዲስ ዳታዎች እና ከኩባንያዎች የቀረቡ የታሪፍ ወጪ መረጃዎች ግን የዚህን ፖሊሲ ጉዳት የሚያመላክቱ ትንበያዎችን ችላ ማለት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርገዋል።

የሰራተኛ ስታቲስቲክስ ቢሮ አርብ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ሀምሌ ውስጥ የተፈጠሩ ተጨማሪ የስራ እድሎች 73,000 እንደሆኑ አስታውቋል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ያወጣውን የግንቦት እና ሰኔ የስራ ፈጠራ እድገት ግምታዊ ቁጥርን በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል፤ በእነዚህ ወራት የተፈጠረው የስራ እድል ቁጥር በ250,000 ቀንሷል።

ትራምፕ፤ ኮሚሽነር ማክኤንታርፈር ለማባረር መወሰናቸውን ይፋ ሲያደርጉ ይህንን የቁጥር ክለሳ ጠቅሰዋል።

ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ "ትክክለኛ የስራ ቁጥሮች ያስፈልገናል። ቡድኔ፤ እቺን የባይደን የፖለቲካ ተሿሚ ወዲያውኑ እንዲያባርር መመሪያ ሰጥቻለሁ" ብለዋል።

ለኮሚሽነሯ ተተኪ እስከሚገኝ ድረስ የቢሮው ምክትል ኮሚሽነር ዊሊያም ዊያትሮውስኪ ኃላፊነቱን እንደሚወጡ ተገልጿል።

ቢሮው ቀድሞውንም በሚከተለው አሰራር መሰረት አዳዲስ መረጃዎች ሲገኙ ከዚህ ቀደም የወጡ ዳታዎች ክለሳ ይደረግባቸውም። ይህ ክለሳም ከዚህ ቀደም የወጣ ቁጥር እንዲጨምር ወይም እንዲቀነስ ሊያደርግ ይችላል።

በዚህ ወር የተደረገው ክለሳ ከዚህ ቀደም ከተለመደው አንጻር ከፍተኛ ቢሆንም፤ ተንታኞች ማሻሻያው ሌሎች ዳታዎች ከሚያሳዩት ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል።