ትራምፕ ካናዳ ላይ የጣሉትን የንግድ ታሪፍ ወደ 35 በመቶ ከፍ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋነኛ የንግድ አጋራቸው በሆነችው ካናዳ ላይ የጣሉትን የንግድ ታሪፍ ወደ 35 በመቶ ከፍ አደረጉ።
ውሳኔው የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ ያካተተ ሲሆን እአአ ከአርብ ነሐሴ 1 ጀምሮ ከ25 በመቶ ወደ 35 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል።
ትራምፕ ካናዳ የፌንታኒል እና ሌሎች መድሃኒቶችን ፍሰት ለመግታት "መተባበር ተስኖታል" ሲሉ የወነጀሉ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ግን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አገራቸው "ከፍተኛ መሻሻል" እያሳየች መሆኗን ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ዓለም አቀፋዊ የንግድ እንቅስቃሴን ለመዘወር ጥረታቸውን በመቀጠል በርካታ አገራት ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ትራምፕ የንግድ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ሊያበቃ ጥቂት ሰዓታት ቀርተው እያለ ከሜክሲኮ የሚመጡ እቃዎች አሁን ባለው ዋጋ ለተጨማሪ 90 ቀናት እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በዚህም የተነሳ ሜክሲኮ ላይ ይጣላል ተብሎ ተሰግቶ የነበረው የ35 በመቶ ታሪፍ ለጊዜው ቀርቷል።
ነገር ግን ከፍተኛ የዋይት ሐውስ ባለስልጣናት የካናዳ አቻዎቻቸው በንግድ ድርድሩ ላይ የነበራቸው ሚና እምብዛም ገንቢ አንዳልነበር በመጥቀስ በኦታዋ ላይ የ35 በመቶ ታሪፍ እንዲጣል አድርገዋል።
ይህ የንግድ ታሪፍ ከአርብ እኩለ ለሊት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ቢሆንም፣ "የአፀፋ" ታሪፍ የተጣለባቸው አገራት ውሳኔው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የሰባት ቀናት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
እስከ ነሐሴ 7 ድረስ በመርከቦች ላይ የሚጫኑ እቃዎች እና በመጓጓዣ ላይ ያሉት ከጥቅምት 5 በፊት አሜሪካ የሚደርሱ ከሆነ በዋጋው ላይ የታሪፍ ጭማሪ አይደረግም።
በዋይት ሐውስ ይፋ የሆነው የአገራት ዝርዝር ወደ አሜሪካ የሚገቡት አብዛኛዎቹ እቃዎች ከ10 በመቶ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ አዲስ ታሪፍ እንዲገጥማቸው ያሳያል።
ከአዲሱ ታሪፍ የተረፉት ጥቂት አገራት ብቻ ናቸው።
በእስያ ፓሲፊክ ክልል ውስጥ የሚገኙት እና አነስተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደ ቫኑዋቱ እና ፓፑዋ ኒው ጊኒ ያሉ አገራት15 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
በዝርዝሩ ውስጥ ያልተጠቀሱ አገራት የ10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
አሜሪካ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለችው ታሪፉ የእስያ አገራትን ክፉኛ ጎድቷል።
የአሜሪካ የንግድ አካር የሆኑት ሕንድ እና ታይዋን የ25 በመቶ እና 20 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
የታይዋን ፕሬዝዳንት ላ ቺንግቴ ታሪፉ "ጊዜያዊ" ነው በማለት ከዋሽንግተን ጋር የሚያደርጉትን ድርድር በቅርቡ እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል።
ወደብ አልባዋ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር ላኦስ እንዲሁ በዚህ ዙር ከፍተኛው ታሪፍ ተጥሎባታል።
ላኦስ ከሶሪያ (41 በመቶ) በመቀጠል 40 በመቶ የተጣለባት አገር ሆናለች።
ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ስምምነት ላይ የደረሰችው ደቡብ ኮሪያ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶቿ ላይ 15 በመቶ ታሪፍ እንዲጣል ተስማምታለች።
ምንም እንኳ የትራምፕ አስተዳደር ውድቅ ቢያደርገውም የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች እና የፋይናንሺያል ተንታኞች አዲሱ ታሪፍ ለንግዶች እና ሸማቾች በአሜሪካ የዋጋ ጭማሪን በማምጣት ኢኮኖሚውን ይጫነዋል ሲሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።
የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ትራምፕ "የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚባሉትን በሁሉም አቅጣጫ ስህተት መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው" ብለዋል።
"እየተመለከትን ያለነው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዓለም ታሪክ ታላቁን ኢኮኖሚ መልሶ እየገነቡ መሆኑን ነው" ብላዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራምፕ በሚያዝያ ወር ላይ የአፀፋ ታሪፎችን ይፋ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካ ቁልፍ የንግድ አጋሮች ተመሳሳይ ታሪፍ በመጣል ምላሽ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ይህ እርምጃቸው የዓለም አቀፍ የንግድ ፍሰትን እንደሚያስተካክልና የአሜሪካን የንግድ ጉድለት እንደሚቀንስ ይገልጻሉ።
እንደ ብረት፣ አሉሚኒየም እና መኪኖች ባሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ያነጣጠሩ ታሪፎች በልዩ ሁኔታ ታይተዋል።
በፋይናንሺያል ገበያዎች ውስጥ አለመረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ፣ አገራቱ እንዲደራደሩ በመጋበዝ፣ አብዛኞቹን ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ በመጣል ሁኔታዎችን ለማለሳለስ ሞክረዋል።
እንደ የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣናት ከሆነ ከ200 በላይ አገራት ወደ ዋይት ሐውስ ቀርበው የንግድ ድርድር ለማድረግ የሞከሩ ቢሆንም አንዳንዶች ትኩረት ተነፍጓቸዋል።
የትራምፕ ባለስልጣናት ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና፣ ጃፓን እና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ከስምንት የንግድ አጋሮች ጋር ጠንከር ያለ የንግድ "ማዕቀፍ" ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።
ነገር ግን የእነዚህ ስምምነቶች ቁልፍ ነጥቦች አሁንም አልተፈቱም።
እንደ ሕንድ ካሉ ሌሎች አገሮች ጋር የተደረገው ውይይት ያለ ስምምነት ተጠናቋል።
ትራምፕ ሕንድ በእቃዎቿ ላይ 25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጣልባት እና ከሩሲያ ጋር ባላት ግንኙነት ላይም ምንነቱ ያልተገለጸ "ቅጣት" እንደሚጠብቃት ተናግረዋል።
ብዙ አገሮች እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ የትራምፕ አስተዳደር ምን ዓይነት አዲስ የታሪፍ ተመን እንዳስቀመጠ አለማወቅ እየጠበቁ ነበር።
የስዊዘርላንድ ፕሬዝዳንት ካሪን ኬለር ሱተር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ከትራምፕ ጋር በስልክ ቢወያዩም ያለስምምነት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
"የንግድ ጉድለቱ የእርሱ ዋና ጉዳይ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
ስዊዘርላንድ 39 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባታል።















