ወንጀል እንድፈፅም ያበረታታኝ ፖሊስ ነው የሚለው ጥቁሮችን እያደነ የሚገድለው ግለሰብ

የጅምላ ነብሰ ገዳዩ ሉዊስ ቫን ሹር
የምስሉ መግለጫ, የጅምላ ነብሰ ገዳዩ ሉዊስ ቫን ሹር

በአፓርታይድ ጊዜ በደርዘን የሚቆጠሩ ጥቁሮችን ተኩሶ የገደለው ግለሰብ ፖሊስ እንዳበረታታው ለቢቢሲ ይናገራል። ሉዊስ ቫን ሹር፤ የጥበቃ ሠራተኛ ሳለ ለፈፀመው ግድያ ሌሎችም ተጠያቂ መሆን አለባቸው ይላል።

ላለፉት አራት ዓመታት ለቢቢሲ አፍሪካ ቃሉን የሰጠው ግለሰብ በጣም አሰቃቂ የሆኑ ድርጊቶችን የተረከ ሲሆን ከእሥር ቤት በጊዜ መለቀቁ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

የቫን ሹር መኝታ ቤት በተለየ ሁኔታ ፅዱ ነው። የአልጋ ልብሱ በካውያ ተተኩሶ የተነጠፈ ይመስላል። ነገር ግን መኝታ ቤቱ በትምባሆ ሽታ የታመቀ ነው። የሲጋር ቁሪ መተርኮሻውን ሞልቶታል። ኮርኒሱ ላይ የተለጠፈው ወረቀት እንደመቀዳድ ብሏል። የሞቱ ትንኞች ተጣብቀውበታል።

“አፓርታይድ ኪለር” አሊያም የአፓርታይድ ነብሰ ገዳይ የተባለ ስም የተሰጠው ግለሰብ ጥርሰ ወላቃ ነው። ጤናውም እየተቃወሰ ይመስላል። በቅርቡ ያጋጠመውን የልብ ድካም ተከትሎ ሁለት እግሮቹ እንዲቆረጡ ግድ ሆኗል። የሚንቀሳቀሰው በዊልቼር ነው። ሰውነቱን ጠባሳ ሞልቶታል።

የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች እግሩን ሲቆርጡት እንደተለመደው ራስ የሚያስት ማደንዘዣ ሳይሆን ኢፒዱራል የተባለ ማደንዘዣ እንዲሰጠው ነው የጠየቀው። ይህን ያደረገው እግሮቹ ሲቆረጡ ለማየት በሚል ነው።

“የሚሆነው ማየት ፈልጌ ነው” ይላል ፈገግ እያለ። “ሲቆርጡት አየኋቸው። አጥንቴን እየቦረቦሩ ነው የገቡት።”

ቫን ሹር ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በተደጋጋሚ የሚያነሳው ነገር “ሰዎች እንደሚያስቡኝ ሰይጣናዊ አይደለሁም” የሚለውን ጉዳይ ነው።

የ1980ዎቹ የደቡብ አፍሪካው ዘረኛ የአፓርታይድ ሥርዓት በግልፅ ነጮችን የበላይ አድርጎ ይወስድ ነበር። በዚህ ወቅት ነው ቫን ሹር በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 39 ሰዎች የገደለው።

ሁሉም ሰለባዎቹ ጥቁሮች ናቸው። በዕድሜ ትንሹ 12 ዓመቱ ነበር። ግድያውን የፈፀመው ኢስት ለንደን በሚባል በደቡብ አፍሪካዋ ኢስተርን ኬፕ በሚገኝ ሥፍራ ነው።

ቫን ሹር በወቅቱ የጥበቃ ሠራተኛ ነበር። የሚጠብቀው 70 በመቶ በነጮች የተያዙ ሬስቶራንቶችን፣ ሱቆች፣ ፋብሪካዎች እና ትምህር ቤቶችን ነበር።

ለረዥም ጊዜ ያክል የገደላቸው ሰዎች “ወንጀለኞች” ናቸው የሚል አቋም አራምዷል። ወደ ሕንፃዎቹ ሲገቡ የያዝኳቸው ናቸው ይላል።

ቫን ሹር አንዳንድ ጊዜ በአንድ ለሊት በርካታ ሰዎች ይገድል ነበር። ይህ ደግሞ በኢስት ለንደን ነዋሪዎች ዘንድ ሽብር ይለቃል። በሥፍራው አንድ ፂማም በቅፀል ስሙ “ዊስከርስ” የሚባል ሰው በምሽት ሰዎችን ይሰውራል እየተባለ ይወራ ነበር። ነገር ግን ሰዎችን ተኩሶ የሚገድለው ተደብቆ አልነበረም።

ቫን ሹር በ1986 እና 1989 መካከል የፈፀማቸውን ግድያዎች በተለመከተ ለፖሊስ ራሱ ሄዶ ቃል ይሰጥ ነበር። ነገር ግን በ1990 ኔልሰን ማንዴላ ከእሥር ቤት ሲለቀቁ የቫን ሹር ያለመከሰስ መብት ተገፈፈ። የማንዴላን መለቀቅ ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የለውጥ ፋና በራ። ከከጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች የመጣውን ጫና ተከትሎ ቫን ሹር በ1991 በቁጥጥር ሥር ዋለ።

የቫን ሹር የፍርድ ሂደት በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ትላልቅ ከሚባሉ የግድያ ችሎቶች አንዱ ሲሆን በደርዘን የሚቆጠሩ ምስክሮች እና በሺህ የሚቆጠር ገፅ ያላቸው ማስረጃዎች ቀርበዋል።

ነገር ግን በወቅቱ አፓርታይድ የዘረጋው የሕግ ተርጓሚ ሥርዓት ሙሉ በመሉ ባለመነሳቱ ምክንያት 39 ሰዎችን ቢገድልም በሰባቱ ብቻ ነው ፍርድ የተሰጠው። ግለሰቡ ለ12 ዓመታት ብቻ ነው እሥር ቤት የከረመው።

ሰውዬው የፈፀማቸው ሌሎች 32 ግድያዎች አሁንም ድረስ “የማያስጠይቁ ግድያዎች” ተብለው በፖሊስ ተይዘዋል። በአፓርታይድ ጊዜ የነበረው ሕግ ጥሰው የገቡ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋልን ከተቃወሙ አሊያም ካመለጡ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ኃይል መጠቀምን ይፈቅዳል።

ቫን ሹር ከወንጀሉ ነፃ መሆኑን ለማመላከት ይህንን የአፓርታይድ ዘመን ሕግ ነበር የተጠቀመው። የግድያ ሰለባዎቹ አምልጠው ሊሄዱ ሲሉ እንደገደላቸው ነው የሚናገረው።

ጋዜጠኛ ኢሳ ጃኮብሰን
የምስሉ መግለጫ, የምርመራ ቡድኑን የመራችው ጋዜጠኛ ኢሳ ጃኮብሰን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቢቢሲ የምርመራ ቡድን ቫን ሹር “የማያስጠይቁ ግድያዎች” ያላቸውን ወንጀለኞች ለማጣራት የተረሱ የፖሊስ ሪፖርቶችን፣ የሬሳ ምርመራ ውጤቶችን እና የእማኞችን ቃል አገላብጦ ተመልክቷል።

ዓመታትን የፈጀው ይህ ምረመራ በኢስተርን ኬፕ ባሉ በርካታ ከተማዎች ያሉ ቤተ-መዘክሮችን ያዳረሰ ነበር። በጣም አስፈላጊ የሚባሉ ዶኪዩመንቶች በሳጥን ታሽገው ተከማችተው ተገኝተዋል።

የምርመራ ቡድኑን የመራችው ጋዜጠኛ ኢሳ ጃኮብሰን “ሁሉም ነገር በጣም የሚደንቅ ነው። ፍርድ ቤት ይህንን እያየ ማለፉ በጣም የሚገርም ነው” ትላለች።

ኢሳን በጣም ያስደነቃት ጉዳይ በቫን ሹር ተተኩሶባቸው የቆሰሉ ነገር ግን ያመለጡ እማኞች የሰጡት ቃል ነው። እኒህ የምስክርነት ቃሎች የሚሉት ነገር ሲሮጡ ነው የተኮስኩት ከሚለው የቫን ሹር ቃል ጋር የሚጣረሱ ናቸው።

የጥበቃ ሠራተኛው በወቅቱ 9 ሚሊሜትር ከፊል አውቶማቲክ መሣሪያ ታጥቆ ነበር የሚንቀሳቀሰው። ይህ የጦር መሣሪያ የሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ይታወቃል። በአንድ ወቅት ምንም ያልታጠቀ ሰው ላይ ዘጠኝ ጥይቶች መልቀቁን ማስረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 11/1988 ቫን ሹር ዝርዝር ሳንቲም ፈልጎ የገባ የ14 ዓመት ታዳጊ ላይ መተኮሱ የግለሰቡን ጭካኔ የሚያሳይ ነው።

ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው ታዳጊ በወቅቱ ቫን ሹር መሣሪያ ይዙ ሲመጣበት ሽንት ቤት ገብቶ እንደተደበቀ ይናገራል። የጥበቃ ሠራተኛው ታዳጊውን ከተደበቀበት ካስወጣው በኋላ ግድግዳ አስደግፎ በተደጋጋሚ እንደተኮሰበት በምስክርነት ቃሉ ላይ ገልጧል።

ምንም እንኳ ታዳጊው ከሞት ቢተርፍም የሚያምነው ሰው ግን አላገኘም። ታዳጊው ወደ ሕንፃው ጥሶ በመግባት ወንጀል ተከሷል። በርካታ ጥቁር ታዳጊ እና ወጣት ደቡብ አፍሪካዊያን በቫን ሹር ቢተኮስባቸውም ዕጣ ፈንታቸው ከላይ ከተጠቀሰው ታዳጊው የተለየ አልነበረም።

የግለሰቡ ፍርድ ሂደት ሲደረግ በርካታ ወጣቶች ቀርበው ምስክርነታቸውን ቢሰጡም የወቅቱ ዳኛ ምስክርነታቸው “ውሀ የሚያነሳ አይደለም” በሚል ውድቅ አድርገውባቸዋል።

የቫን ሹር ፍርድ ሂደት ሲደረግ ኢስት ለንደን የሚገኙ በርካታ ነጮች ለግለሰቡ ያላቸውን ድጋፍ ገልጠዋል። አንድ ነጋዴ “ሉዊስን እወደዋለሁ” የሚል ወረቀት ይዞ ታይቶ ነበር።

በደቡብ አፍሪካ “ስታቹ ኦፍ ሊሚቴሽን” [አንድ ወንጀል ከተፈፀመ በኋላ ወደኋላ ተመልሶ አለመጠየቅ] የለም። ይህ ማለት ፖሊስ አሁንም የቫን ሹርን መዝገብ ከፍቶ በ1980ዎቹ በተፈፀሙ ወንጀሎች ሊጠይቀው ይችላል።

የቢቢሲ ምርመራ ቡድን ከደረሰባቸው አሰቃቂ የሚባሉ ግድያዎች መካከል ከቫን ሹር ጋር ከተደረገው ቃለ-ምልልስ የተገኙት ቀላል የሚባሉ አይደሉም።

ቫን ሹር
የምስሉ መግለጫ, በአፓርታይድ ጊዜ በደርዘን የሚቆጠሩ ጥቁሮችን ተኩሶ የገደለው ቫን ሹር

አብዛኛዎቹ ንብረቶች የሚጠብቅላቸው ነጋዴዎች ድምፅ-አልባ “አላርም” ያላቸው ሲሆን አንድ ሰው ጥሶ ሲገባ ለቫን ሹር መልዕክት የሚልኩ ናቸው።

“ባዶ እግሬን ነው የምንቀሳቀሰው። ፀጥ ያለ ነው። ጫማ ስለማላደርግ ምንም ዓይነት ድምፅ አይወጣም ነበር” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

መብራት አያበራም። በምትኩ እያሸተተ ነው ሰለባዎቹን የሚያገኛቸው። “አንድ ሰው ሰብሮ ከገባ የሆነ ዓይነት ሽታ ይመጣል። እሱን ተከትለህ መሄድ ትችላለህ” ሲል ያክላል።

ቫን ሹር፤ አንድም ቀን “ጥቁሮችን እገድላለሁ ብዬ አስቤ ያደረግኩት ነገር የለም” ይላል፤ ዘረኛ እንዳልሆነም ያክላል። ነገር ግን በጨለማ ጥቁሮችን አድኖ መግደል “አስደሳች ነው” ይላል።

ግለሰቡ የጥበቃ ሠራተኛ ሆኖ ከመቀጠሩ በፊት ለ12 ዓመታት የኢስት ለንደን ፖሊስ መኮንን ሆኖ አገልግሏል። “አጥቂ ውሾችን” ይዞ በመንቀሳቀስ የሚታወቀው ቫን ሹር ተቃዋሚዎችንና ወንጀለኞችን በውሻ ያሳድዳል። ፖሊስ ሳለ ሰለባዎቹ ሁሉም በሚባል ደረጃ ጥቁሮች ነበሩ።

በፍፁም “ጅምላ ገዳይ” አይደለሁም የሚለው ግለሰቡ ያደረገው ነገር በሙሉ “ሕጉን ተከትሎ እንደሆነ” ነው የሚያምነው። በግድያው ምክንያት የተቀየሙት ሰዎች ካሉ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስን እንዲወቅሱ ይናገራል።

እሱ እንደሚለው ፖሊስ አንድም ቀን ተችቶት አሊያም አስጠንቅቆት አያውቅም። እንዲያው ድርጊቱን በተደጋጋሚ ያበረታታው እንደነበር ያወሳል።

“ሁሉም የኢስት ለንደን ፖሊሶች ምን እንደሚከናወን ያውቃሉ። . . . ሁሉም የፖሊስ መኮንኖች ያውቁ ነበር” ይላል።

ጃኮብሰን ለሕዝብ ይፋ ከሆኑ ዶኪዩመንቶች ባገኘችው ማስረጃ መሠረት በአንዳንድ ግድያዎች ወቅት ፖሊሶች በሥፍራው የነበሩ ቢሆንም አንድም ቀን ቫን ሹርንም ተጠርጣሪ አድርገውት አያውቁም። አልፎም በበርካታ ጊዜያት ፖሊስ ከግድያው በኋላ ለማስረጃ የሚሆን ፎቶ አሊያም ምርመራ አድርጎ አያውቅም።

“ቫን ሹር ጅምላ ገዳይ የሆነበት ምክንያት በአቅራቢ ያለው ማኅበረሰብ ስላበረታታው ነው” ትላለች ጃኮብሰን።

ለቫን ሹር ግድያ ሰለባ ቤተሰቦች ግለሰቡ በነፃነት መንቀሳቀሱ እንዲሁም ፍርድ ቤት ግድያውን በደንቡ አለመመርመሩ ትልቅ ስቃይ ነው። አንዳንድ ቤተሰቦች እስካሁን የሟቾችን ሬሳ አግኝተው መቅበር አልቻሉም።

ምንም እንኳ ቫን ሹር ፍርድ ሲሰጠው ለፈፀመው የግድያ ወንጀል 90 ዓመታት እሥር ቤት እንዲቆይ ቢፈረድበትም ዳኛው ሁሉንም ቅጣቶች በአንድ ጊዜ እንዲቀጣ ስለፈቀዱለት በአውሮፓውያኑ 2004 ተለቋል።

በአፓርታይድ ጊዜ በፈፀሙት ወንጀል የተቀጡ ሰዎች ከታሰበው ጊዜ በታች እሥር ቤት ቆይተው የመለቀቃቸው ጉዳይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እጅግ አከራካሪ የሆነ ርዕስ ነው።

በርካታ ግለሰቦች ከእሥር ቤት መለቀቃቸውን ተከትሎ በ2022 በደቡብ አፍሪካዋ ጆሀንስበርግ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዶ እንደነበር አይዘነጋም።

ቫን ሹር አሁንም አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው የራግቢ ጨዋታ በመመልከት፣ ትምባሆ በመማግ እና ብሩተስ ከተባለው ውሻው ጋር በመጫወት ነው። የፈፀማቸውን አብዛኛዎቹን ግድያዎች እንደማያስታውስ ይናገራል።

ምንም እንኳ ማጣራት ባይቻልም አንዳንድ ሪፖርቶች ግለሰቡ በቁጥር 100 ገደማ የሚደርሱ ሰዎችን ገድሏል ይላሉ። ቫን ሹር ይህ ቁጥር ትክክል አይደለም ቢልም ቁጥሩ ከ39 ሊበልጥ እንደሚችል ያምናል።

“እውነት ለመናገር ስንት ሰው እንደገደልኩ አላስታውስም። አንዳንዶች 100 ይላሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ 40. . . እንደው ለወሬ እንዲያመች 50 ነው እንበለው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማኝም። ምንም ዓይነት ቁጭት ውስጤ የለም።”

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።