“ከሰው በታች አድርገው ነው የሚቆጥሩን”- ‘የሦስተኛ አገር ዜጋ’ የተባሉት ከዩክሬን የሸሹ አፍሪካውያን ተማሪዎች

 ሃይፋ ጁማ

የፎቶው ባለመብት, HAIFA JUMA

የምስሉ መግለጫ, ሃይፋ ጁማ

እንዳይመለሱበት ጦርነት ይጠብቃቸዋል። ይቅርብን እንዳይሉ ስንት ዓመት የደከሙበት ሁሉ መና ሊቀር ነው።

ይህ በዩክሬን የነበሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ፈታኝ ምርጫ ሆኗል።

‘ልሂድ ወይስ ልቅር?’ ምላሽ ያላገኙለት ጥያቄ ነው።

ይህ ጥያቄ ላለፉት ወራት ሲያብሰለስላቸው ከቆዩት መካከል ታንዛኒያዊቷ ሃይፋ ጁማ ትገኝበታለች።

የተሻለ ያለችውን ወሰነች። ወደ ዩክሬን ተመልሳ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ማጠናቀቅ።

“ምርጫ አልነበረኝም። ጦርነቱ መቀጠሉን ብንከታተለም. . . ብዙ ስጋቶች ነበሩኝ። ምን ከፊቴ እንዳለ እርግጠኛ አልነበርኩም።”

ሩሲያ ዩክሬንን በወረረች ማግስት ነው የውጭ አገር ተማሪዎች ጓዛቸውን ጠቅለለው ከአገሪቱ የወጡት።

አፍሪካውያን ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ጦርነቱ ከጀመረ ወራት ወራትን ወልደው ሁለት ዓመታት ተቆጠሩ። ጦርነቱ 30 ሺህ ሲቪሎችን መቀጠፉ ተነግሯል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩክሬን ሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪ አሃዙ ከዚህም በላይ ነው ይላል።

ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከተሞች እና መንደሮች ወድመዋል።

ይህ እንደሚመጣ የሰጋችው ሃይፋ ጦርነቱ ሲጀምር ነው ከዩክሬን ወደ ሃንጋሪ ያቀናችው። በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ይህንን መንገድ መርጠዋል።

ከዚህ በኋላ ወደ ዩክሬን ለመመለስ ስትወስን ማሳመን የነበረባት ራሷን ብቻ አልነበረም። ወላጆቿን ለማሳመን ወራትን ፈጅቶባታል።

“ዕድሜ ለበይነ መረብ የንድፈ ሃሳብ ትምህረቱን ታንዛንያ ሆኜ ተከታተልኩ። ለመመረቅ ግን ትምህርት ቤቴ በመገኘት የተግባር ትምህረቱን ማጠናቀቅ ይገባኛል።”

“ቤተሰቦቼ ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት ተገደዋል። ስለዚህ ጦርነቱ እስኪያልቅ እጄን አጣጥፌ መጠበቅ የለብኝም።”

ሃይፋ ጁማ በዩክሬን ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ናት። ዩኒቨርሲቲው በሰሜን-ምሥራቅ ዩክሬን የሚገኝ ነው። በ2027 ዶክተር ሆና ትመረቃለች። ያውም በጽንስና በማህጸን ህክምና (ጋይኖኮሎጂ) ስፔሻላይዝ ያደረገች ዶከተር ትሆናለች።

የዩክሬን ዓለም አቀፍ ትምህርት ማዕከል ለትምህርት የተመለሱ አፍሪካውያን ተማሪዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በትክልል አያውቅም።

ከጦርነቱ በፊት 16 ሺህ ገደማ አፍሪካዊያን ለትምህርት ዩክሬን ደርሰው ነበር።

አፍሪካውያን ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

አሁን ለትምህርት የተመዘገቡ 5500 አፍሪካዊያን ተማሪዎች አሉ። ይህንን መረጃ ይፋ ያደረገው የአገሪቱ የትምህርት መረጃ ማዕከል ነው።

ከእነዚህ መካከል 3 ሺህ 950 የሞሮኮ እና የናይጄሪያ ተማሪዎች ይገኙባቸዋል። ከሃይፋ አገር ታንዛንያ 49 ተማሪዎች በጦርነቱ መካከል ለመማር ተመዝግበዋል።

“ወደ ትምህርት ለመመለስ የሚደረገው ውሳኔ በእያንዳንዱ ተማሪ የተወሰነ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች መማሪያ እና ማደሪያ ክፍሎች ቦምብ የመከላከል አቅም እንዳላቸው ለማረጋገጥ ሞክረዋል። በበየን መረብ የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱ ከፍ እንዲልም ቁጥጥር በማድርግ ላይ ይገኛሉ” ሲል የዩክሬን ዓለም አቀፍ ትምህርት ማዕከል ለቢቢሲ በላከው መግለጫ ጠቅሷል።

ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ለተማሪዎቹ ትምህርት የሚሰጥበት መንገድ እንደሚቀያየርም ይጠቅሳል። የትኛው የተሻለ አካሄድ ነው የሚለውን የሚመርጡት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ እና ተማሪዎቹ ይሆናሉ ብሏል።

“ሁሉም ከፍተኛ ተቋማት በጊዜያዊነት በቁጥጥር ስር ከዋሉ አካባቢዎች የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ ወዳላቸው የመካከለኛ እና ምዕራብ ዩክሬን አካባቢዎች ተዘዋውረዋል” ሲሉ የተቋሙ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

እንደሃይፋ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት ወደ አገራቸው ተመለሱ ተማሪዎች በሙሉ ግን ለትምህርት ወደ ዩክሬን ለመመለስ አልወሰኑም።

አፍሪካውያን ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በወቅቱ 16 ሺህ ገደማ ከነበሩት እና በዩክሬን ትምህርታቸው ሲከታታሉ ከነበሩ አፍሪካዊያን ተማሪዎች መካከል 10 ሺህ ያህሉ አገሪቱን ጥለው ወጥተዋል። ብዙዎቹም ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም።

አንዳንዶች ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ፣ የተወሰኑት ደግሞ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት አቅንተዋል። ኔዘርላንድስ፣ ፖርቹጋል እና ፊንላንድ የደረሱ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን በማቅረብ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

በጊዜያዊነት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያደረገው የአውሮፓ ኅብረት ጊዜያዊ የጥበቃ መመሪያ ነው። መመሪያው ለሁለት ዓመት እንዲያገለግል የወጣ ሲሆን፣ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።

በዚህ ሕግ ኔዘርላንድስ የደረሱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበት ቀን ከተጠናቀቀ በኋላ የተማሪ ቪዛ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል ሲል የኔዘርላንድስ የፍትህ እና የደኅንነት ሚኒስቴር አስታውቋል።

አይሻ ከዩክሬን ጦርነት ሸሽታ በኔዘርላንድስ ትምህርቷን መከታተል ጀምራለች። ለዚህ ያበቃት የአውሮፓ ኅብረት መመሪያ እሷን ጨምሮ 17 “የሦስተኛ አገር ዜጎችን” በኔዘርላንድስ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ዕድል ከፍቶ ነበር።

አፍሪካውያን ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የ25 ዓመቷ አይሻ የሕክምና ተማሪ ናት። ለደኅንነቷ ሲባል ሙሉ ስሟ እንዳይጠቀስ ጠይቃለች። ትምህርቷን ለማጠናቀቅ የመጨረሻ ሴሚስተር ላይ ደርሳለች።

በጦርነት ውስጥ ወደ ምትገኘው ዩክሬን ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለችም። በዚህም ለመመረቅ አንድ ሴሚስተር የቀራትን ትምህርት መስዋዕት ለማደረግ ወስናለች።

“ወደየት እንድንሄድ ነው የምትፈልጉት? መቼም ሰዎች በየዕለቱ ወደሚሞቱባት ዩክሬን አይደለም ተመለሺ የምትሉኝ” ስትል አይሻ አጥብቃ ትጠይቃለች።

“የዩክሬንን ውሎ እና አዳር እከታተላለሁ።”

“ይህ ግዴታዬ ነው። ብዙ የለፋሁባቸው የትምህርት ማስረጃቼ እዚያ ናቸው። ለዩክሬናውያን አዝናለሁ። ለእኛ ‘ለሦስተኛ አገር ዜጎች’ ደግሞ በጣም አዝናለሁ። ኔዘርላንዶች ሸክም እንደሆንባቸው ቢሰማቸውም እየሠራን ግብርም እየከፈልን ነው።”

“ከሰው በታች አድርገው ነው የሚቆጥሩን። በተመሳሳይ ጦርነት ውስጥ አልፈን ለምን እንደዚህ ይመለከቱናል?” ስትል ትጠይቃለች።

እንደ ኔዘርላንድስ የፍትህ እና የደኅንነት ሚኒስቴር ገለጻ ከሆነ እንደ አይሻ ያሉ ተማሪዎች ፈቃዳቸው በጥቂት ቀናት ካበቃ በኋላ በ28 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቀው መውጣት ይጠበቅባቸዋል።

“አብዛኞቹ በጦርነቱ ወቅት ከዩክሬን ሸሽተው የመጡ ‘የሦስተኛ አገር ዜጎች’ ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ አለባቸው። እነዚህ ተማሪዎች ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ ከሆነ ጥገኝነት መጠየቅ ይችላሉ” ብሏል በመግለጫው።

ኔዘርላንድስን መልቀቅ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ‘የሦስተኛ አገር ዜጎች’ የትምህርት መረጃዎቻቸውን ወደሚሄዱባቸው አገራት ያዘዋውራሉ።

‘የሦስተኛ አገር ዜጎችን’ መብት ለማስጠበቅ ዴርዴላንደረስ የተሰኘ የኔዘርላንድስ ቡድን ተቋቁሟል። ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ በአገሪቱ አንዲቆዩ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የዴርዴላንድስ ቡድን መሪ የሆኑት አይዛክ አዎዶላ “የሰብአዊ ድጋፍ እና ርህራሄ ማሳየት ይገባል። እነዚህ ሰዎች ምንም ይሁን ማን ሰዎች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል” ብሏል።

“ከአፍሪካ የመጡ ቢሆኑም ከዩክሬን ሲለቁ ብዙ መከራ ያጋጠማቸው ሰዎች ናቸው።”

የሦስተኛ አገር ዜጎቹን ጉዳይ እስከ መጋቢት 2025 ድረስ በኔዘርላንድስ እንዲቆዩ ከተደረጉ ወደ 400 የሚጠጉ የዩክሬን ተማሪዎች ጋር ያነጻጽራል።

አፍሪካውያን ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, ISAAC AWODOLA

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ተማሪዎቻቸው ከዩክሬን ውጭ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ችግሩን ቀርፈዋል። ጋና የሕክምና ተማሪዎቿን ትምህርታቸው እንዲጨርሱ ወደ ግሬናዳ እንዲዘዋወሩ ተስማምታለች።

200 ተማሪዎችን የሚመለከተው ስምምነት ጦርነቱ በተቀሰቀሰ ማግስት ይፋ ተደርጓል። ሃንጋሪም በዩክሬን ይማሩ የነበሩ የጋና ተማሪዎችን ለመመቀበል ተመሳሳይ ሐሳብ አቅርባለች።

ከዩክሬን የወጡ በርካታ የአፍሪካ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመጨረስ አማራጭ መንገዶችን ለመፈለግ ተገደዋል። ከፊሎቹም ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው በመመለስ ሥራ መፈለግ ነበረባቸው።

ሃይፋ በምትማርበት ከተማ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ ቢሆንም፤ ውጊያው እሷን እና ሌሎች ተማሪዎችን እንደገና እንዲሰደዱ ሊያደርግ ይችላል የሚል ያለማቋረጥ ጭንቀት ፈጥሮባትል።

“የካቲት ላይ ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ ወደ ኪዬቭ ተጉዘን ነበር። እዚያ እያለን ከህንጻችን ፊት ለፊት ፍንዳታ ደረሰ።”

“ሁኔታው እየተሻሻለ እንደመጣ በማሰብ ዘና ማለት ጀምሬ ነበር” ትላለች።

“ነገር ግን አስፈሪውን ፍንዳታ ካየሁ በኋላ ሁኔታው ምናልባትም ትንሽ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። በቅርቡ እንደሚያበቃ ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች።